May 29, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ
በውጭ ሀገር ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከተው አዋጅ፤ ከአራት ዓመት በኋላ በድጋሚ ማሻሻያ ተደረገበት። የአዋጅ ማሻሻያው በውጭ ሀገር ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች “መብታቸው፣ ደህንነታቸው እና ክብራቸው በዘላቂነት መጠበቁን ለማረጋገጥ” “እንዲያስችል ሆኖ የተዘጋጀ ነው” ተብሏል።
በ2008 ዓ.ም የወጣው “የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ስምሪት አዋጅ” ሰራተኛን በውጭ ሀገር ለስራ ማሰማራት የሚቻለው፤ “በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተቀባይ ሀገር መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ሲኖር ብቻ እንደሆነ” የሚገድብ ድንጋጌ ነበረው። በ2013 ዓ.ም. የጸደቀው የዚህ አዋጅ ማሻሻያ በበኩሉ፤ በውጭ ሀገራት “የሰለጠነ የሰው ኃይል” ለሚፈለግበት ስራ ተጨማሪ ሁለት የስምምነት አማራጮችን አካትቷል።
የመጀመሪያው አማራጭ፤ ጉዳዩ በሚመለከተው የኢትዮጵያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እና በተቀባይ ሀገር ከሚገኘው አቻ ስልጣን ካለው የመንግስት ተቋም ጋር “የሁለትዮሽ ስምምነት” ወይም “መግባቢያ ሰነድ” ሲኖር ሰራተኛን ማሰማራት እንደሚቻል ይፈቅዳል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተመሳሳይ ስምምነት በውጭ ሀገር ከሚገኝ “እውቅና ካለው አሰሪ ኩባንያ” ጋር ከፈጸመም፤ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን መላክ እንደሚቻል በአዋጁ ማሻሻያው ተደንግጓል።

ከአራት ዓመት በፊት የተደረገው የአዋጅ ማሻሻያ ያቀረበው ሁለተኛ አማራጭ የግል ስራ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲን የሚመለከት ነው። “የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚሰማራበት ስራ አፈላልጎ ያገኘ ኤጀንሲ፤ በተቀባይ ሀገር መንግስት እውቅና ካለው ቀጣሪ አሰሪ ኩባንያ ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት እንዲፈጽም” ጉዳዩ የሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሊፈቅድ እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ፈቃድ የሚሰጠው “የተቀጣሪ ዜጎች መብት እና ደህንነት የሚጠበቅ መሆኑን በማረጋገጥ” እንደሆነ በ2013ቱ የአዋጅ ማሻሻያ ላይ ሰፍሯል። ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 21፤ 2017 በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያም፤ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን “መብት፣ ደህንነት እና ክብር” “በዘላቂነት መጠበቁን ለማረጋገጥ” እንዲያስችል ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
ለፓርላማ የተመራው አዲሱ አዋጅ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ “ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ” በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያሰራጨው መረጃ ያመለክታል። የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በበላይነት የመከታተል ኃላፊነት የተጣለበት የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በውጭ ሀገር ስምሪቶች ከተሰጡ አገልግሎቶች 113 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ አስታውቆ ነበር።

ይህ አሃዝ ይፋ በተደረገበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 344,790 እንደሆነ ገልጸዋል። ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ዜጎቿ ለስራ እንዲሰማሩ በሀገር ደረጃ ስምምነት ያደረገችባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ኩዌት እንደሆኑም በዚሁ ማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከሊባኖስ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ብትፈራረምም፤ በሀገሪቱ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ህጋዊ የስራ ስምሪት እንዳልተጀመረም ሙፈሪያት በወቅቱ ተናግረው ነበር። ሁለቱ ሀገራት በሚያዝያ 2015 ዓ.ም የተፈራረሙት የስራ ስምሪት ስምምነት በታህሳስ 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ አይዘነጋም።
በስምምነቱ ላይ ለኢትዮጵያውያን የሚከፈለው “ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል” በግልጽ አለመካተቱ፤ የቤት ሰራተኞች መብት እንዲከበር በሚሟገቱ ግለሰቦች እና ተቋማት በኩል ትችት እንዲቀርብበት ምክንያት ሆኗል። በሊባኖስ እስከ 400 ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው እንደሚሰሩ በጉዳዩ ላይ የተጠናቀሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በመብት ተሟጋቾች የተተቸው የሊባኖስ እና የኢትዮጵያ መንግስታት የስራ ስምሪት ስምምነት ለፓርላማ
ቀረበ። በስምምነቱ ላይ ለኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች የሚከፈለው ዝቅተኛ ደመወዝ አለመካተቱ ጥያቄ
ተነስቶበታል።
ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/12026/
Translate post
2 3
ኢትዮጵያ ከሌላኛዋ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ባህሬን ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኗን ሙፈሪያት በሚያዝያው የፓርላማ ቆይታቸው ተናግረው ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ተመሳሳይ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ከጃፓን፣ ስዊድን፣ ኮሪያ እና ጀርመን ሀገራት ለማድረግ በንግግር ላይ መሆኑንም ሙፈሪያት በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል።
በጀርመን ከሚገኝ ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት የተወሰኑ መሀንዲሶች ለስራ መላካቸውን በፓርላማ ማብራሪያቸው ያነሱት ሙፈሪያት፤ በስዊድን ከሚገኝ ኩባንያ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ላይ መድረሱንም አክለዋል። ከውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት በተያያዘ ከሚሰጡ አገልግሎቶች፤ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 472.5 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው፤ ሚኒስቴሩ ለውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የወጣ ደንብን በተጨማሪነት አጽድቋል። ደንቡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለእነዚህ አገልግሎቶች “የሚያወጣውን ወጪ ሸፍኖ የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ እንዲችል” የሚያደርግ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በደንቡ የተካተቱት የአገልግሎት ክፍያዎች የተዘጋጁት፤ “የተገልጋዩን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ” እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቡ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ “በሙሉ ድምጽ” መወሰኑንም አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር )