May 29, 2025

በዳኞች ስራ ማቆም ምክንያት ለአንድ ሳምንት ያህል ተዘግተው የነበሩ በመቐለ ከተማ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች፤ ዛሬ ሐሙስ ስራ ጀመሩ። “የደህንነት ስጋት አለብን” በሚል ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙት በከተማይቱ የሚገኙ ዳኞች ወደ ስራ የተመለሱት፤ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ከተካሄደ በኋላ መሆኑን የትግራይ ዳኞች ማህበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

በመቐለ ከተማ የሚገኙ ዳኞች ባቀረቧቸው ጥያቄዎች ላይ ውይይት የተደረገው ባለፈው ሰኞ ግንቦት 18፤ 2017 ነበር። ጉዳዩን በተመለከተ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ውይይት ያደረጉት፤ ከክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሓዱሽ ተስፋ እና ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት አቶ መንግስቱ ተክላይ ጋር ነው። 

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በዛሬው ዕለት ተዘዋውሮ በተመለከታቸው በመቐለ ከተማ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች መግቢያዎች ላይ የተለጠፉ ማስታወቂያዎች፤ ይህንኑ ውይይት መጠቅሳቸውን ታዝቧል። “በዳኞች ላይ ባጋጠመ የደህንነት ስጋት ምክንያት የተቋረጠው አገልግሎት እንዲጀመር ከሚመለከተው አካል ጋራ ውይይት ተካሂዷል” የሚለው ማስታወቂያው፤ “በውሱን መልኩ ጥያቄዎቻችን መፈታት ስለጀመሩ ከዛሬ 21/9/2017 ጀምሮ የዳኝነት አገልግሎት ጀምረናል” ይላል። 

የትግራይ ክልል ዳኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ሃይለስላሴ “በውይይቱ ለዳኞች ስራ ማቆም ምክንያት የሆኑ ጥያቄዎች እንደሚፈቱ ስለተነገረን ነን ወደ ስራ የተመለስነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ማህበሩ ከዳኞች ደህንነት ጋር የተያያዙ አምስት ጥያቄዎችን፤ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቅረቡን ባለፈው ሳምንት ገልጾ ነበር። 

የዳኞቹ የመጀመሪያ ጥያቄ በችሎት የሚመደቡ የጸጥታ አስከባሪዎችን የሚመለከት ነው። “በችሎት ጊዜ ሁለት ፖሊሶች ብቻ ናቸው ፍርድ ቤቱን የሚጠብቁት” የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በአሁኑ ጊዜ በመቐለ ከተማ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ቁጥራቸው “በቂ እንዳልሆነ” ይናገራሉ። 

በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው ከፍ ያለ “የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች” ፍርድ ቤቶችን እንዲጠብቁ እንዲደረግ ኧእርሳቸው የሚመሩት ማህበር ጥያቄን ማቅረቡን አስረድተዋል። “ይህ ጥያቄ ተፈትቶ፣ ችሎት የሚጠብቁ የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች ተመድበዋል። ስራም ተጀምሯል” ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት የዛሬውን ሁኔታ ገልጸዋል። 

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በዛሬው ዕለት በተመለከታቸው የመቐለ ከተማ ፍርድ ቤቶች ውስጥ መሳሪያ የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች ችሎቶችን ሲጠብቁ አስተውሏል። በከተማይቱ በዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት የሚያገለግሉ አንድ ሰራተኛ “ከአሁን በፊት ተጠርጣሪዎችን ይዘው የሚመጡ ፖሊሶች ብቻ ነበር ችሎቱን የሚጠብቁት። በዛሬው እለት ግን ሶስት የታጠቁ የጸጥታ አባላት ችሎት እየጠበቁ ናቸው” ሲሉ ቀድሞ የነበረውን ከአሁኑ ሁኔታ ጋር አነጻጽረዋል።

እንደ ጸጥታ ጥበቃው ሁሉ ለዳኞች ደህንነት ራሱን የቻለ የመጓጓዣ ትራንስፖርት እንዲዘጋጅ በትግራይ ዳኞች ማህበር የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል። ማህበሩ ይህን ጥያቄ ያቀረበው፤ ዳኞች በህዝብ ትራንስፖርት በሚመላለሱበት ጊዜ “ማስፈራራት እና ድብደባ እየደረሰባቸው” በመሆኑ ምክንያት እንደነበር ጠቅሰዋል።  

ከጥያቄው በኋላ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ለዳኞች ትራንስፖርት በማዘጋጀቱ “ችግሩ መፈታቱንም” አቶ ዳዊት ተናግረዋል። በዳኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች በከፊል ምላሽ ያገኘው፤ “ችሎት የደፈሩ የመንግስት ከፍተኛ ስልጣን የያዙ” ኃላፊዎች ለህግ ይቅረቡ” የሚለው እንደሆነም አመልክተዋል።  

ግለሰቦቹ “በህግ እንዲጠየቁ” ማህበሩ ያቀረበውን ጥሪ፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር “እውቅና ሰጥቶ እያጣራው መሆኑን በይፋ መግለጫ ሰጥቷል” ሲሉ ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ አቶ ዳዊት አብራርተዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ በችሎት ውስጥ የሚፈጠር ረብሻ “በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም” ሲል ኮንኗል። 

የትግራይ ዳኞች ማህበር ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል፤ ዳኞች በነጻነት ስራቸውን ለማከናወን እንዲችሉ “ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉበት ሁኔታ ይመቻች” የሚለው ይገኝበታል። ዳኞች ለደህንነታቸው ሲባል “የመኖሪያ ቤት አቅርቦት” እንዲመቻችላቸውም ማህበሩ በተጨማሪነት ጠይቆ ነበር።

እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ገና ምላሽ አለማግኘታቸውን አቶ ዳዊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የዳኞች ጥያቄን ለመመለስ የተላለፉ ውሳኔዎችን በተመለከተ ከትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)