
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል በኃይል በያዘችው የፍልስጤሟ ግዛት ዌስት ባንክ በአስር ዓመታት ውስጥ ታላቅ የተባለውን ሰፈራ እያስፋፋች መሆኑን አስታወቀች።
የእስራኤል ሚኒስትሮች 22 አዳዲስ የአይሁድ ሰፈራዎች እንዲመሰረቱ አጽድቀናል ብለዋል።
ከባለስልጣናቱ ፈቃድ ውጭ ከዚህ ቀደም የተገነቡ ሰፈሮች በእስራኤል ህግ መሰረት ህጋዊ ይሆናሉ።
ሌሎቹ ሰፈራዎች ግን አዲስ እንደሚሆኑ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እና የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ገልጸዋል።
ሰፈራ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ህገወጥ ቢሆንም እስራኤል ይህንን ባለመቀበል በኃይል በያዘችው የፍልስጤሟ ዌስት ባንክ አይሁዳውያንን እያሰፈረች ትገኛለች።
ካትዝ ይህ እርምጃ “እስራኤልን አደጋ ላይ የሚጥለው የፍልስጤም በአገርነት መመስረትን ይከላከላል” ብለዋል።
የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ሁኔታውን “አደገኛ” ሲሉ ጠርተውታል።
የእስራኤል ጸረ-ሰፈራ ድርጅት የሆነው ዋችዶግ ፒስ እርምጃውን በ30 ዓመታት ከፍተኛው እንደሆነ ገልጾ “ዌስትባንክን ግዛት እንደሚቀይረው እና ወረራውን የበለጠ ያጠናክረዋል” ብሏል።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም የተቆጣጠረችው።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
አብዛኛው የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል እያደረገችውን ሰፈራ በአለም አቀፉ ህግ መሰረት ህገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።
እስራኤል ይህንን አትቀበልም።
በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ከሶስት ዓመት ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል።
በዌስት ባንክ የእስራኤል መንግሥት ፖሊሲን የሚተገብረው የሲቪል አስተዳደር ከፍተኛ እቅድ ኮሚቴ ኃላፊዎች እና አክራሪ የሚባሉት ሁለቱ የእስራኤል ሚኒስትሮች እስራኤል ካትዝ እና ቤዛሌል ስሞትሪች ከሁለት ሳምንት በፊት በፊት በመንግሥት ጸድቋል ተብሎ የሚታመነውን የሰፈራ ውሳኔ በይፋ አረጋግጠዋል።
የሲቪል አስተዳደሩን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የቀኝ አክራሪው ፖለቲከኞች መግለጫ 22 አዳደዲስ ሰፈራዎች ማጽደቃቸውን ጠቅሶ፣ “በሰሜናዊ ምዕራብ ባንክ፣ ሰማርያ ሰፈራውን እንደገና ማሳለጥ እና እንዲሁም በምስራቃዊ ግዛት በኩልም የእስራኤልን ግዛት ማጠናከር” ይላል።
አዳዲሶቹ ሰፈራዎች ትክክለኛ ቦታ ባይጠቀሱም ነገር ግን የተሰራጩ ካርታዎች የዌስት ባንክን ግዛት ሙሉ በሙሉ ሊነኩ እንደሚችሉ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2005 እስራኤል ወታደሮቿን እና ሰፋሪዎቿን ከጋዛ ስታስወጣ በተመሳሳይ ጊዜ በሰሜናዊ ዌስት ባንክ የሚገኙት ሆሜሽ እና ሳ ኑር ተመሳሳይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሁለቱ ሚኒስትሮች እነዚህ ስፍራዎች “ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ” ተመልሰዋል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት “እስራኤል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች መቀጠሏ ህገወጥ ነው” ብሏል።
አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በተጨማሪም የእስራኤል ሰፈራዎች “አለም አቀፍ ህግን በመጣስ የተቋቋሙ እና አሁንም እየጣሱ ያሉ ናቸው” እንዲሁም እስራኤል “ሰፋሪዎቿን በሙሉ ማስወጣት” አለባት የሚል ውሳኔን አስተላልፏል።
ኔታንያሁ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ “ሐሰተኛ ውሳኔ” እንዳስተላለፈና “የአይሁድ ህዝብ በገዛ መሬታቸው ላይ ወራሪዎች አይደሉም” ብለዋል።