
ከ 5 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ ሠራተኞች መደራጀት፣ የተሻለ ደመወዝ፥ የሥራ እና የኑሮ ሁኔታዎችን እንዲመቻቹላቸው መጠየቅ ከጀመሩ ስድስት አስርት ዓመታትን አስቆጥረዋል።
በእነዚህ ዓመታት ጥያቄዎቻቸው ጆሮ እንዲያገኙ ከሥራ ማቆም አድማ ጀምሮ የአደባባይ ተቃውሞ እስከ ማድረግ የደረሱ የትግል ስልቶችን ተጠቅመዋል።
በየጊዜው የተቀያየሩት ገዢዎችም የሠራተኞችን ጥያቄ ለመመለስ አሊያም አድበስብሶ ለማለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል።
የሠራተኞች ጥያቄ ጀመረው በአጼ ኃይለሥላሴ ወቅት ነው። ፋብሪካዎች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ የሠራተኞችም ጥያቄ አብሮ መነሳት ጀመረ።
ከቀዳሚዎቹ የሠራተኞች ጥያቄዎች መካከል የሥራ ሁኔታ እና መደራጀትን የተመለከቱ ነበሩ።
በጊዜው ሠራተኞች አንድ ላይ ማኅበር ሊጠጡ ይችላሉ እንጂ በማኅበር ተደራጅተው ደመወዝ መጠየቅ የማይታሰብ ነበር።
ሠራተኞች ይህ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው እና በየመሥሪያ ቤታቸው ማኅበራትን መመሥረት እና ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት ከጥያቄዎቻቸው ቀዳሚው ነበር።
ባለፉት ስልሳ ዓመታት እነዚህ ጥያቄዎች በቁጥርም በይዘትም አድገዋል። ሠራተኞችም ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ካላገኙ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያድረጉ ይዝታሉ። የአሠሪዎቻቸውን እጅ ጠምዝዘው ወደ ጠረንጴዛ ይስባሉ።
አምስተርዳም በሚገኘው ኢንትርናሽናል ኢኒስቲቲዩት ኦፍ ሶሻል ሂስትሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል አንድሪያስ አድማሴ፤ ሠራተኞች የደመወዝ፣ የኑሮ እና የሥራ ሁኔታ ጥያቄዎችን ለማስመለስ የሥራ ማቆም አድማዎች በተደጋጋሚ ያደርጉ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በተለይም ማኅበራት በኅብረት ለመደራደር ሲፈልጉ፣ ወይም ኩባንያዎች በድርድሮቹ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ የተለመደ” እንደሆነ ያነሳሉ።
ነገር ግን እነዚህ የሥራ ማቆም አድማዎች በጊዜ ሂደት ተመሳሳይ ይዘት እና ግዝፈት እንዳልነበራቸው የሚናገሩት ዶ/ር ሳሙኤል፤ በኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ የተደረጉ የሥራ ማቆም አድማዎችን በጊዜ ማዕቀፍ ለያይተው ይመለከቷቸዋል።
“[በኢትዮጵያ] የሠራተኞች እንቅስቃሴ በመጀመሪያዎቹ አስርት ዓመታት ውስጥ፤ ከ1950 ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት እስከ 1970ዎቹ ድረስ፣ በደመወዝ ኢኮኖሚ ውስጥ የማያቋርጥ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ማቆም አድማ ነበር” ይላሉ።
“አብዛኞቹ ሠራተኞችም የአንዳንድ አድማዎች አካል ነበሩ” ሲሉም ያክላሉ።
ቀዳሚዎቹ የሥራ ማቆም አድማዎች
አቶ ተፈራ ኃይለ ሥላሴ “የኢንዱስትሪ እና የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ዕድገት” በተሰኘው መጣጥፋቸው በመንግሥት ደረጃ ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ሕግ ባለመውጣቱ “አሠሪው በመሰለው ደሞዝ እና የሥራ ሁኔታ ሠራተኛ የሚያስተዳድርበት አካሄድ ነበር የሰፈነው” ይላሉ።
በ1950ዎቹ አጋማሽ ግን የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ድንጋጌ ወጥቷል።
ዶ/ር አዳነ ካሴ “Trade Unions and the State in Ethiopia, 1946-1991” በሚል ርዕስ በሠሩት የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት፤ “አሰሪዎች አዋጁ የወጣው ለሠራተኞች ብቻ ነው ብለው በማመን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይጥሱት” እንደነበር አስፍረዋል።
በተጨማሪም አሰሪዎች “በየድርጅቶቻቸው ውስጥ የሠራተኛ ማኅበራት ምሥረታን አጨናግፈውታል።” የኢንተርፕራይዞች ባለቤት የሆኑ የውጭ ባለሀብቶች ሕግ እና አሠራርን በመጣስ ከሥራ እስከማባረር የደረሰ እርምጃዎችን ወስደዋል።
ይህም በአንዳንድ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ዶ/ር አዳነ በጥናታቸው ላይ ጠቅሰዋል።
አሠሪዎች የሠራተኞችን ፍላጎት ለማሟላት ገና ዝግጁ ባይሆኑም በርካታ ጉዳዮች አዲስ ወደተቋቋመው የሠራተኛ ቦርድ ቀርበዋል። የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች በበኩላቸው በአሠሪዎች ማስፈራሪያ ይደርሳባቸው ነበር።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር (ኢሰአማ) ጉዳዩ እንዲፈታ ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተከትሎ፤ የሠራተኛው ጥያቄዎች በ60 ቀናት ምላሽ ካላገኙ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚጠራ አስጠነቀቀ።
መንግሥት ማስጠንቀቂያውን እና ቁጣውን ተቀብሎ በይዘቱ እንዲሁም በኢሠአማ አመራሮች ላይ ሊወሰድ ስለሚችለው እርምጃ ሲወያይ ለሁለት ሳምንታት ያህል ዝም አለ።
ከማስጠንቀቂያው አንድ ወር በኋላ የኢሠአማ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አብርሃም መኮንን በመንግሥት ባለሥልጣናን የሥራ ማቆም አድማ እንዳያድረጉ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።
ከቀናት የቤተ መንግሥት እና የባለሥልጣናት ምልልስ በኋላ ኢሠአማ የጠራውን የሥራ ማቆም አድማ መሰረዙን አስታወቀ። ፕሬዝዳንቱ አቶ አብርሃምም ከሥልጣን እንዲለቁ ተደረገ። ሌላው የማኅበሩ አመራር የነበሩት አበራ ገሙ ደግሞ ራሳቸውን አጠፉ ተባለ።
ዶ/ር አዳነ ኢሠአማ አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ መጥራቱ “ያለጊዜው የተደረገ እና ጥበብ የጎደለው” መሆኑን የማኅበሩን አመራሮች ጠቅሰው ጽፈዋል።
“አቶ አብርሃም እና መላው አመራሩ የኢሠአማን ጥንካሬ እና ድርጊቱ የሚያስከትለውን መዘዝ በቅጡ አልተረዱትም” ይላሉ።
የሥራ ማቆም አድማ በአብዮቱ ጊዜ
ከከሸፈው የሥራ ማቆም አድማ በኋላ ኢሠአማ ጥርስ አውጥቶ ጠንካራ ድርጅት ለመሆን አስር ዓመታት ገደማ ፈጅቶበታል።
በ1960ዎቹ አጋማሽ በተለይም ከአብዮቱ አንድ እና ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ በሠራተኛ ማኅበራት በኩል “ከፍተኛ መነቃቃት” መፈጠሩን ዶ/ር ሳሙኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል፤ እ.አ.አ በ2019 ‘Dynamics of Assertive Labour Movementism in Ethiopia’ በሚል ርዕስ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ በሠሩት ጥናት ከአብዮቱ መባቻ እስከ አብዮቱ ማግሥት 56 የሥራ ማቆም አድማዎች መካሄዳቸውን ሰንደዋል።
ከተደጋጋሚ የሥራ ማቆም አድማዎች በተጨማሪ የሠራተኛ ማኅበራት ጠንካራ እና አክራሪ ወደ መሆን ተሸጋግረዋል።
‘Trade Union Resurgence in Ethiopia’ በሚለው ሌላ ጽሁፋቸው፤ “በ1966 ዓ.ም እየከረረ የነበረው ውጥረት ገሃድ ወጣ፤ የአብዮቱን ጅማሬ ባበሰረው የየካቲት ግርግር ዓውድ ውስጥ በኢሠአማ ውስጥ ያሉ ግራ ዘመም አባላት የበላይ ሆኑ” ይላሉ።
ዶ/ር ሳሙኤል ከሰነዷቸው የሥራ ማቆም አድማዎች መካከል ምናልባትም ግዙፉ ሊባል የሚችለው በ1966 መጋቢት ላይ የተካሄደው አገር አቀፍ አድማ ነው።
የየካቲቱ የኢትዮጵያ አብዮት ኢሠአማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቁን አገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ እንዲጠራ ገፊ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር አዳነ በዶክትሬት ጥናታቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ዶ/ር አዳነ በዶክትሬት ጥናታቸው፤ “የ1966ቱ አብዮት መፈንዳት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ከነበሩበት አስከፊ ሰቆቃ አውጥቶ፣ አጠቃላይ የአብዮቱን ጉዞ የበለጠ የሚያፋጥን የሥራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ አበረታቷል” ይላሉ።
የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ኢሠአማ ከዚህ በፊት ውጤታማ የሆነ ሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ባለማቻሉ የየካቲት 66ቱን ጥያቄ እና ማስጠንቀቂያ ከቁብ ሳይቆጥሩ ችላ አሉት።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 1/1966 ዓ.ም. ድረስ የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ።
የፋብሪካ ማሽኖች ቆሙ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በራቸውን ከረቸሙ፤ አውሮፕላን ማረፊያው ተዘጋ።
አንዳርጋቸው አሰግድ ‘በአጭር የተቀጨ ረዥም ጉዞ’ በሚለው መጽሐፋቸው “ወደ 120 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች ለአንድ ሳምንት ያህል ሥራ በማቆም አገሪቱን ቀጥ አደረጓት” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል።
የሥራ ማቆም አድማው ለአራት ቀናት ከቆየ በኋላ መጋቢት 1/1966 ዓ.ም. የሠራተኞችን ጥያቄ ቸል ብለው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ እንዳልካቸው እና ኢሠአማ ስምምነት ላይ ደረሱ።
ሆኖም ጫና የበረታባቸው አጼ ኃይለ ሥላሴ ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት ቃል ከመግባት ውጪ ይኼ ነው የሚባል ተጨባጭ ምላሽ ለኢሠአማ አልሰጡም።

ንጉሡ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት ቢፈልጉም ጊዜው ረፍዶ ነበር። ከየካቲት 1966 እስከ መስከረም 1967 የረባ ሥልጣን አልነበራቸውም። ወዝ-አደሩም፣ ወታደሩም የንጉሡ ፀሐይ ማዘቅዘቅ መጀመሯን እርግጠኛ ነበሩ። ንጉሡ እና ባለሟሎቻቸው ራሱ ይህ ሳይዘልቃቸው ይቀራል?
በተማሪዎቹ የተነቃነቀው የንጉሡ ዙፋን፤ በሠራተኞች፣ በታክሲ ነጂዎች እና በመምህራን ርብርብ በወታደሮቹ እስከ ወዲያኛው ተገረሰሰ።
ዶ/ር ሳሙኤል ሠራተኞቹ በቀጥታ ባይሆንም ለንጉሣዊው አገዛዝ መውደቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።
“የየካቲት እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አዲሱ ዓመት ድረስ፣ ሲደረጉ የነበሩት አድማዎች ለአገዛዙ ውድቀት አስተዋፅዖ አድርገዋል፤ ነገር ግን ሠራተኞች አድማ ሲያደርጉ የነበሩት የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ለመጣል አልነበረም። ለዚያ አይደለም ማኅበራት አባሎቻቸውን ለአድማ ሲጠሩ የነበሩት” ሲሉ ያብራራሉ።
ከንጉሡ መውደቅ በኋላ የሠራተኛ ማኅበራት ጥያቄያቸውም ፍላጎታቸውም ተቀየረ።
ደርግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጥቂት ቀናት በኋላ ኢሠአማ በማኅበሩ ጉዳይ ላይ ለመወያያት በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ በስብሰባው ላይ “[ኢሠአማ] በራሱ ጉዳይ ላይ ማተኮሩን በመተው ሠራተኛው በአገራዊ ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር ስምምነት ላይ ይደርሳል” ሲሉ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢሠአማ ከዚህ ስብሰባው በኋላ “ወታደራዊ አገዛዝ ለዚች አገር አይበጃትም፤ ስለዚህም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም” የሚሉ ጥያቄዎችን አቀረበ።
ዶ/ር ሳሙኤል “የሠራተኛ ማኅበራቱ አገዛዙን ለመጣል ግልጽ ዓላማ ይዘው የተነሱት በደርግ የአገዛዝ ዘመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሠራተኞች ከደርግ ጋር ሲጋጩ ነበር። በእርግጥ አልተሳካም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም “የኢትዮጵያ ችግር የሥርዓት ችግር ነው፤ ሕዝባዊ የሆነ መንግሥት ሳይቋቋም ለወታደራዊው መንግሥት መሠረት ለመጣል ተማሪዎች መዝመት የለባቸውም” በሚል የደርግን የዕድገት በኅብረት ዘመቻ ተቃወመ።
ከዚህ በተጨማሪም የሥራ ማቆም አድማ ለማደረግ ውሳኔ ያሳልፋል።
ደርግ የሥራ ማቆም አድማው እንዲሰረዝ የኢሠአማን አመራሮች ለማግባባት ቢሞክርም አመራሮቹ አሻፈረን በማለታቸው፤ በወቅቱ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ በየነ ሰለሞንን ጨምሮ አራት አመራሮች በደርግ ታሰሩ።
ከዚያ በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት ኢሠአማ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የደርግ ምላሽ ግን የከፋ ነበር።
መስከረም 1968 ዓ.ም. ተጠርቶ በነበረው የሥራ ማቆም አድማ ምላሽ ብቻ አንድ መቶ ገደማ ሰዎች መገደላቸውን ዶ/ር ሳሙኤል በአንድ ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመስከረም 16/1968 ዓ.ም. ዕትሙ “በቦሌው ሁከት የሞቱት ሰዎች ብዛት ሰባት ደረሰ” በሚል ርዕስ በጊዜው የተገደሉ የአየር መንገድ ሠራተኞችን ጉዳይ ዘግቦ ነበር።
በኃይለ ሥላሴ ባለሟሎች ጠመንጃቸውን ያሟሹት ደርጎች ለሠራተኞቹም አልተመለሱም። መንግሥቱ አብዮት አደባባይ ደም ረጭተው ቀይ ሽብርን አሽጀመሩ። ዶ/ር ሳሙኤል “ከቀይ ሽብር በኋላ በእርግጥ የሥራመ ማቆም አድማ ማድረግ አደገኛ ሆነ” ይላሉ።
በድኅረ-አብዮት የሥራ ማቆም አድማ
ዶ/ር ሳሙኤል የቀይ ሽብርን ተከትሎ የሥራ ማቆም አድማዎች “እስከ መጨረሻዎቹ የደርግ አገዛዝ ዓመታት ድረስ በጣም ዝቅተኛ ነበሩ” ይላሉ።
የደርግ መንግሥት የመጨረሻ ዓመታት እና የኢህአዴግ የመጀመሪያ ዓመታት የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ እንደገና ማንሰራራቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኢህአዴግ የመጀመሪያ ዓመታት “በአንፃራዊነት የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ ተብለው በሚገመቱት” በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ሁለት ትልልቅ አድማዎች መደረጋቸውን በዶክትሬት ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።
የኢህአዴግ መሪዎች በአራት ኪሎ መንበራቸውን ሳይደላደሉ፤ “ነፃ የሠራተኞች እንቅስቃሴ እንደገና እንቅፋት” እንደገጠመው ዶ/ር ሳሙኤል ያስታውሳሉ።
በደርግ ወቅት የነበረው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር (ኢሠማ) “የደርግ ተለጣፊ ነው” ተብሎ እንዲፈርስ ተደረገ።
በ1986 የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈዴሬሽን (ኢሠማኮ) ከመንግሥት ጋር ለመጋጨት አፍታም አልፈጀበትም።
ኢሠማኮ ከተመሠረተ ዘጠኝ ወራት በኋላ የኢህአዴግ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም (Structrural Adjustment Program) ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲያሰማ የቅራኔው ጅማሮ ሆነ።
ዶ/ር ሳሙኤል “ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው ኃይሎች ኮንፌዴሬሽኑን ጨምሮ ብዙ የሠራተኛ ማኅበራትን ተቆጣጠሩ። እናም አድማዎች ተቀዛቀዙ” ሲሉ ያስታውሳሉ።
የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የሥራ ማቆም አድማዎች እንደገና በተደጋጋሚ መደረግ መጀመራቸውን እና በዚህ ወቅትም የነበሩት የሥራ ማቆም አድማዎች ከ1960ዎቹ ጋር ሊስተካከሉ የሚችሉ መሆናቸውን ዶ/ር ሳሙኤል ይናገራሉ።
ባለፉት አስርት ዓመታት የሥራ ማቆም አድማዎች በጣም ተደጋጋሚ እንደነበሩ ያክላሉ።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽን እና በትግራይ ጦርነት ወቅት የሥራ ማቆም አድማዎች መቀነሳቸውን የሚያነሱት ዶ/ር ሳሙኤል፤ “አሁን እንደገና ከወረርሽኙ በፊት ወደነበረበት ደረጃ እንደተመለሰ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ” ይላሉ።
በሌላ ጽሁፋቸውም ከ10 ዓመታት በፊት የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት “እየተካሄደ ያለው የማኅበራዊ ትርምስ ሌላው ገጽታ ከሞላ ጎደል ችላ ተብሏል” ይላሉ።
ከ2017 የመጸው ወራት ጀምሮ “ከ12 ያላነሱ የሥራ ማቆም አድማዎች ተመዝግበዋል” ሲሉም ያክላሉ።
ከ1966ቱ አብዮት ወዲህ ያልተደገመው የሥራ ማቆም አድማ በኢህአዴግ የመጨረሻ ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እያስጨነቀው እንደነበር ዚሁ ጽሁፋቸው ጠቅሰዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ከጠቀሷቸው የሥራ ማቆም አድማዎች መካከል የተወሰኑት አመጽ የተቀላቀለባቸው ነበሩ።
የኔዘርላንድስ ዜግነት ባላቸው ሰዎች ባለቤትነት በተያዘው በሼር ኢትዮጵያ የአትክልት እና ፍራፍሬ እርሻ 4,000 ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በመስኮቶች ላይ ድንጋይ በመወርወር የእርሻ ንብረት ማውደማቸውን ለዚህ ማሳያ ነው።
የፈረንሳውያን ንብረት በሆነው የካስቴል ወይን መጥመቂያ ውስጥ የነበሩ 1200 ሠራተኞች የሥራ ቁሳቁሶቻቸውን አስቀምጠው አድማ መትተዋል፤ አስተዳደሩንም ከግቢው አባርረዋል።
ከአድማው በኋላ ካስቴል ለሠራተኞቹ 70 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ መስመማቱን ዶ/ር ሳሙአል ይጠቅሳሉ።
በጥቅምት 2010 ዓ.ም. የተሻሻለው የሠራተኛ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅርብ በሠራተኛ ማኅበራት በኩል ትልቅ ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ረቂቅ ሕጉ የሠራተኞችን መብት የሚጥስ፣ የሙከራ ጊዜን በእጥፍ የሚጨምር፣ የዕረፍት ቀናትን የሚቀንስ እና በሥራ ቦታ ለሚደርሱ አደጋዎች አነስተኛ የግዴታ ማካካሻ ሀሳብ የሚያቀርብ በመሆኑ ተቃውሞ ገጥሞታል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ማሻሻያ አዋጁን ተቃውሞ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚጠራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ይህ ከ1967 ወዲህ የሥራ ማቆም አድማን እንደ መሳሪያ የመጠቀም የመጀመሪያው ሙከራ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ጽፈዋል።
ይህ የኢሠማኮ ማስጠንቀቂያ “መንግሥት ያረቀቀውን የሠራተኛ አዋጅ በመተው እንዲደራደር አስገድዶታል” ይላሉ።

ለሥራ ማቆም አድማዎች እና የመንግሥታት ምላሽ
በግል ኮርፖሬሽኖች እና በመንግሥት ተቋማት የሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማዎች ውጤታማ የመሆን ዕድላቸው እኩል አይደለም።
ዶ/ር ሳሙኤል “በግል ኮርፖሬሽኖች ላይ የሚደረጉ አድማዎች በጣም ከፍተኛ የስኬት ደረጃ አላቸው። ምክንያቱም ሠራተኞቹ የአሰሪዎቻቸው ትርፍ ላይ ማነጣጠር ይችላሉ” ይላሉ።
በተጨማሪም ሌሎች ተመራማሪዎችን ጠቅሰው በውጭ አገር ዜጎች በተያዙ ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ አድማዎች የተሻለ ውጤት የሚያገኙበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ለዚህም ምክንያቶቹ አንደኛው ባለቤቶቹ በሥራ ማቆም አድማዎቹ ሳቢያ ስማቸው ሊጠፋ መቻሉ ስለሚያሳስባቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከፍተኛ የትርፍ ህዳግ ስላላቸው የሠራተኞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት መቻል ነው።
በሌላ በኩል መንግሥት አትራፊ ድርጅት ባለመሆኑ ምክንያት በተቋማቱ የሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማዎች የመንግሥትን የትርፍ ህዳግ ማጥቃት ይቸገራሉ።
በዚህ ሳቢያ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ውጤታማ የመሆን ዕድላቸው አነስተኛ ነው።
ዶ/ር ሳሙኤል “ሁሉም የኢትዮጵያ መንግሥታት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማዎችን በዓይነ ቁራኛ ነው የሚመለከቱት” ይህ የሁሉም መንግሥታት ባህሪ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
“በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ በዝመታ የሚታለፈው በተለይ በውጭ አገር ድርጅቶች እና አንዳንድ የግል ድርጅቶች ውስጥ ሲካሄድ እንጂ የመንግሥት ሠራተኞች መካከል ሲደረጉ አይደለም” ይላሉ።
በዚያን ጊዜ የነበረው ገዢ መደብ ገቢው ግብርና ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑ በግብርና ዘርፉ ላይ የሚካሄዱ የሥራ ማቆም አድማዎችንም አይታገሱም ነበር።
ደርግም የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ እንደማይፈልግ የሚጠቅሱት ዶ/ር ሳሙኤል፤ ሠራተኞችን በጠመንጃ ነበር የተቀበላቸው ይላሉ።
“ኢህአዴግም ሥልጣን በያዘ በመጀመሪያዎቹ አንድ እና ሁለት ዓመታት በግል ኩባንያዎች ለሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማዎች ያን ያህል ጠላትነት አልነበራቸውም” ሲሉ ያስታውሳሉ።
“ሠራተኞቹ የሥራ ማቆም አድማ የሚያደረጉት ደርግን በመቃወም እንጂ ለሠራተኞች ጥቅም የሚደረጉ አልመሰላቸውም” የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል፤ “ነገር ግን ሠራተኞቹ በመንግሥት ባለቤትነት በተያዙ ኮርፖሬሽኖች በተለይም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ሲጀምሩ ፍፁም የተለየ አመለካከት ነበራቸው” ሲሉ ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም “የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማ በመንግሥት በኩል የከፋ ጥላቻ አልፎ ተርፎም ጭካኔ ይደርስባቸዋል” ይላሉ።
“መንግሥት የጭቆና መንገዶችን ይቆጣጠራል” የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል የግል ድርጅቶች መንግሥት አንዲረዳቸው ሊማጸኑ ይችላሉ እንጂ አርምጃ መውሰድ የሚችሉበት አቅም እንደሌላቸው ይገልጻሉ።
“ነገር ግን መንግሥት፣ አሁን እየተካሄደ ያለው የጤና ባለሙያዎች አድማ እንደሚያሳየው ሰዎችን ማሰር ይችላል” ሲሉ ያክላሉ።
የፌደራል ፖሊስ ባለፈው ሳምንት 47 የጤና ባለሙያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቆ ነበር። ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የጤና ባለሙያዎች “የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ”፤ በአገሪቱ ውስጥ “ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ያበሩ” የሚል ውንጀላ አቅርቦባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች የጤና ባለሙያዎች ያነሱት “የፖለቲካ ጥያቄ ነው” የሚሉ ትችቶችንም ያቅርባሉ።
ዶ/ር ሳሙኤል የሥራ ማቆም አድማ “ኢኮኖሚያዊ ነው ወይስ ፖለቲካዊ? [ጥያቄ]” የሚለው ክርክር ከ1966ቱ የሥራ ማቆም አድማ ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚነሳ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
“ለደሞዝ ጭማሪ ወይም ለዝቅተኛ የደሞዝ ወለል የሥራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ፣ እነዚያ በዋነኛነት የትርፍ ክፍፍልን በተመለከተ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ናቸው። በጣም የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው” ሲሉ ያስረዳሉ።
በተጨማሪም “ሠራተኞች ወጥተው ተገቢው ደመወዝ እንዲከፈላቸው በመጠየቅ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ራሱ ፖለቲካዊ ጥያቄ ነው። ቀጣሪው መንግስት ሲሆን ደግሞ ሌላ ገጽታ ይሰጠዋል፤ ስለዚህ ከፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ሊነጣጠል አይችልም” ይላሉ።