ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከውጪ የሚገቡትን ታክስ መሰብሰቡን መቀጠል እንደሚችሉ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው የትራምፕ የአለም አቀፍ ታሪፍ በንግድ ፍርድ ቤት ህገ ወጥ ነው ከተባለ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት ትራምፕ ቀረጦችን በመጣል ሥልጣናቸውን አልፈዋል ሲል ያስተላለፈው ትዕዛዝ ለጊዜው እንዲታገድ ከዋይት ሀውስ የቀረበለትን ይግባኝ ተቀብሎታል።

የረቡዕ የአሜሪካ አለምአቀፍ ንግድ ፍርድ ቤት ውሳኔ የትራምፕ ባለስልጣናትን አስቆጥቷል ቀስቅሷል።

ትናንሽ ንግዶች እና የተወሰኑ የአሜሪካ ግዛቶች የትራምፕ አጀንዳ ዋና አካል የሆኑትን እና የአለምን ኢኮኖሚ ስርዓት ያናወጠውን እርምጃ ተቃውመዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ይግባኝ ባቀረበበት ወቅት በንግዱ ፍርድ ቤት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተላለፈው ውሳኔ ፕሬዚዳንቱን ያለአግባብ በመገመት ለወራት ትግል የተደረገበትን የንግድ ድርድር ለመፍታት ያሰጋል ብሏል።

“የውጭ ፖሊሲ የሚያወጡት እና የኢኮኖሚ ፖሊሲን የሚያዘጋጁት የፖለቲካ ቅርንጫፎቹ እንጂ ፍርድ ቤቶች አይደሉም” ሲል በይግባኝ አቤቱታው ላይ ገልጿል።

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት የሃሙስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከመስጠቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወይም ሌላ ማንኛውም ፕሬዝዳንት ዲፕሎማሲያዊ ወይም የንግድ ድርድሮቻቸው በአክቲቪስቶች ዳኞች የሚዘወሩ ከሆነ አሜሪካ መሥራት አትችልም” ብለዋል ።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በማህበራዊ ድረ-ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት “ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን አስከፊና አገርን የሚያሰጋ ውሳኔ በፍጥነት እና በቆራጥነት ይቀለበሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ነቅፈዋል።

በኒውዮርክ የሚገኘው እምብዛም የማይታወቀው የንግድ ፍርድ ቤት የረቡዕ ውሳኔ ትራምፕ በየካቲት ወር ከቻይና፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በመጡ ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ውድቅ አድርጎታል።

የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ትራምፕ ባለፈው ወር ይፋ ያደረጉትን 10 በመቶ ከአለም ዙሪያ በአጠቃላይ ወደ አገሪቱ በሚገኙ ሸቀጦች ላይ ይፋ ያደረጉትን የገቢ ታሪፍ ውድቅ የሚያደርግ ነው።

ፍርድ ቤቱ ትራምፕ ታሪፎችን ለመጣል እየተጠቀሙበት ያለው እ.አ.አ በ1977 የወጣው የአደጋ ጊዜ የኢኮኖሚ ኃይሎች ህግ ከኮንግረስ ምንም ግብአት ሳይኖር እንደዚህ ያሉ ቀረጦች እንዲጣሉ አይፈቅድም ብሏል።

ነገር ግን ውሳኔው ትራምፕ በሌላ ህግ በሚተገበሩት የመኪና፣ የብረታብረት እና የአሉሚኒየም ታሪፍ ላይ ለውጥ አያመጣም።

ነገር ግን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ እያለ ታሪፎቹን ለአሁኑ ጥቅም ላይ እንዲውል ይፈቅዳል።

ቀጣዩ የችሎት ቀጠሮ በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ግንቦት 28 ነው።

ሐሙስ ቀን የተለየ የታሪፍ ጉዳይን የሚመለከተው ሌላ የፌዴራል ፍርድ ቤት ለንግድ ፍርድ ቤት ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሷል።