
ከ 3 ሰአት በፊት
አንድ ከፍተኛ የሃማስ ባለስልጣን አሜሪካ ያቀረበችውን አዲሱን የጋዛን የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን እንደማይቀበል ለቢቢሲ ተናገሩ።
ዋይት ሀውስ ሐሙስ እለት እንዳስታወቀው እስራኤል የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ያቀረቡትን ‘ተቀብላለች’ ከሐማስ መደበኛ ምላሽ እየጠበቀች ነው ብሏል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ሐማስ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እና በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ለመፍታት በሁለት ደረጃ 10 በህይወት ያሉ ታጋቾችን እና የ18 ሟቾችን አስከሬን አሳልፎ እንደሚሰጥ ገልጿል።
የሃማስ ባለስልጣን ሃሳቡ ጦርነቱን ማቆምን ጨምሮ ዋና ዋና ፍላጎቶችን እንደማያሟላ እና በጊዜው ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል ።
የእስራኤል መንግሥት የሰጠው አስተያየት ባይኖርም፤ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የዊትኮፍን እቅድ መቀበላቸውን ሀሙስ እለት ለታገቱ ቤተሰቦች መናገራቸው ተዘግቧል።
እስራኤል በጋዛ ላይ አጠቃላይ እገዳን የጣለች ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኳታር እና ግብፅ አደራዳሪነት የተፈረመው የሁለት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረሱን ተከትሎ በሃማስ ላይ ወታደራዊ ወረራዋን በመጋቢት መጀመሪያ ቀጥላለች።
እስራኤል ሃማስ እስካሁን በእስር ላይ የሚገኙትን 58 ታጋቾች እንዲፈታ ጫና ማድረግ እንደምትፈልግ ተናግራለች። ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በህይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ገደማ በፊት ግንቦት 11፣ የእስራኤል ጦር ሰራዊት የተስፋፋ ጥቃት የጀመረ ሲሆን ኔታንያሁ [ሠራዊቱ] የጋዛን “ሁሉንም አካባቢዎች ይቆጣጠራል” ብለው ነበር።
በማግስቱ፣ እስራኤል በጋዛ ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ በማለዘብ ረሃብን ለመከላከል “መሰረታዊ” መጠን ያለው ምግብ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደምትፈቅድ ተናግረዋል።
በጋዛ ባለፉት 10 ሳምንታት ውስጥ ወደ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሌላ 600,000 ሰዎች በእስራኤል የመሬት ላይ ዘመቻ እና ትዕዛዝ እንደገና ተፈናቅለዋል ብሏል።
በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈው አይፒሲ ዘገባ በመጪዎቹ ወራት ወደ 500,000 የሚጠጉ ሰዎች አስከፊ የሆነ የረሃብ አደጋ እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቋል።
ሐሙስ እለት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት የሳዑዲ ንብረት የሆነው የአል-አረቢያ ቲቪ እስራኤል እና ሃማስ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱን የሚገልጽ ዘገባ ማረጋገጥ ይችሉ እንደሆነ ተጠይቀዋል።
“ልዩ መልዕክተኛ ዊትኮፍ እና ፕሬዝዳንቱ እስራኤል የምትደግፈውን የተኩስ አቁም ሃሳብ ለሀማስ ማቅረባቸውን አረጋግጣለሁው። እስራኤል ይህንን ሃሳብ ወደ ሃማስ ከመላኩ በፊት ስምምነቷን ገልጻለች” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “እነዚህ ውይይቶች መቀጠላቸውን አረጋግጣለሁ፣ እናም በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረግ ተስፋ እናደርጋለን ስለዚህ ታጋቾቹን በሙሉ ወደ ቤታቸው እንመልሳለን” ብለዋል።
ነገር ግን፣ የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን በኋላ እንደተናገሩት ስምምነቱ ቀደም ሲል በቡድኑ ተደራዳሪዎች እና በዊትኮፍ መካከል የተደረጉ ውይይቶችን የሚጻረር ነው።
ባለሥልጣኑ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሃሳቡ ጊዜያዊው የእርቅ ስምምነት ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስለማምራቱ ዋስትና አይሰጥም እንዲሁም ባለፈው የተኩስ አቁም ወቅት በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪኖች እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የፈቀደውን የሰብአዊ ፕሮቶኮል መመለስን አላካተተም።
ቢሆንም፣ ሃማስ ከአደራዳሪዎች ጋር ንግግሩን እንደሚቀጥል እና ምላሹን በጽሁፍ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የእስራኤል ቻናል 12 ቲቪ ኔታንያሁ ለታጋቾች ቤተሰቦች በስብሰባ ላይ “ዛሬ ምሽት የቀረበልንን የቅርብ ጊዜውን የዊትኮፍ እቅድ ለመቀበል ተስማምተናል። ሃማስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። ሃማስ የመጨረሻውን ታጋች ይለቅቃል ብለን አናምንም፣ እናም ሁሉንም ታጋቾች እስከምናስለቅቅ ድረስ ከ[ጋዛ] ሰርጥ አንወጣም” ማለታቸውን ዘግቧል
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በኋላ ላይ ባወጣው መግለጫ ከጣቢያው ጋዜጠኞች አንዱን ስብሰባው ወደተካሄደበት ክፍል የቀረጻ መሳሪያን “በድብቅ” ለማስገባት ሞክሯል ሲል ከስሷል። ነገር ግን ኔታንያሁ በአሜሪካ ሃሳብ መስማማታቸውን አልካደም።
ኔታንያሁ ቀደም ሲል እስራኤል ጦርነቱን የምታቆመው ሁሉም ታጋቾች ሲፈቱ ፣ ሀማስ ሲወድም ወይ ትጥቅ ሲፈታ እና መሪዎቹ ወደ ስደት ሲላኩ ብቻ ነው ብለዋል።
ሃማስ ጦርነቱን እንዲያቆም እና እስራኤል ከጋዛ ጠቅልላ የምትወጣ ከሆነ በምርኮ የተያዙትን በሙሉ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ53 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።
ከግጭቱ በፊት አራት ሰዎች በጋዛ ተግተው የነበረ ሲሆን ሁለቱ ሞተዋል።
እስካሁን ድረስ እስራኤል ከሃማስ ጋር ባደረገችው ሁለት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቶች 197 ታጋቾችን ያስመለሰች ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 148ቱ በህይወት ያሉ ናቸው።
ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ከፈረሰ በኋላ እስራኤል በጀመረችው ድጋሚ ጥቃት 3,986 የሚሆኑ መገደላቸውን የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሃማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ እንደገለጸው ሐሙስ ዕለት እስራኤል በጋዛ ላይ ባደረሰችው ጥቃት በትንሹ 54 ሰዎች ተገድለዋል። 23ቱ ሰዎች የተገደሉት በማዕከላዊ ቡሬጅ አካባቢ አንድ መኖሪያ ቤት በተመታ ጊዜ ነው ብሏል።
የእስራኤል ጦር ባለፈው ቀን “በደርዘን የሚቆጠሩ የሽብር ኢላማዎችን” መምታቱን ተናግሯል።