ወደ ትግራይ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሸቀጦች

30 ግንቦት 2025

ሸቀጦችን የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች በአማራ እና አፋር ክልሎች አልፈው ወደ ትግራይ እንዳይገቡ መከልከላቸውን አሽከርካሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የተለያዩ ሸቀጦችን ለትግራይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በሁለቱ ክልሎች ባሉ የፍተሻ ኬላዎች እንዲቆሙ መገደዳቸውን አሽከርካሪዎች ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።

እነዚህ ለክልሉ ሸቀጦችን የጫኑ መኪኖች ከቀናት በፊት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከማለፍ እንደታገዱ የትግራይ ክልል ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

የክልሉ ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካሳሁን ክንደያ፤ በእገዳ ምክንያት የቆሙት ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ሲጓጓዙ የነበሩ “መሠረታዊ ሸቀጦችን” የጫኑ እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ክንደያ እንደሚናገሩት በአፋር በኩል የተጣለው ክልከላ የጀመረው ሰኞ ግንቦት 18/2017 ዓ.ም. ነው። ከማግሥቱ ማክሰኞ ግንቦት 19 ጀምሮ ደግሞ በአማራ ክልል በኩል ወደ ትግራይ በሚወስደው መስመር ላይም እገዳ መጣሉን ገልጸዋል።

አሽከርካሪዎቹ በበኩላቸው በአፋር ክልል እንዲቆሙ ከተደረጉ ሰባተኛ ቀናቸውን እንዳስቆጠሩ ገልጸው “ከበላይ ትዕዛዝ በሚል” ወደ ትግራይ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ከመናገር ውጪ ምክንያቱን እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ አካባቢዎች እንደተነሱ የገለጹት እነዚህ የጭነት አሽከርካሪዎች፤ በአፋር እና በአማራ ክልል ወልዲያ አካባቢ በሚገኙ ሁለት የፍተሻ ኬላዎች ሲደርሱ ወደ ትግራይ አትገቡም መባላቸውን ገልጸው ይህም በሕዝቡ እና በነጋዴው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን አስረድተዋል።

በአፋር መስመር ሰርዶ ሜዳ በተባለ ስፍራ በሚገኝ ኬላ ከተሸከርካሪው ጋር ወደ ትግራይ እንዳይገባ የተከለከለ አንድ ሹፌር እገዳው ባለፈው ቅዳሜ፣ ግንቦት 16/2017 ዓ.ም. መጀመሩን ተናግሯል።

ቅዳሜ ምሽት አፋር ክልል፣ አዳይቱ የምትባል ስፍራ ላይ መስመሩ እንደተዘጋባቸው እና አታልፉም እንደተባሉ ያስረዳል።

“ለምንድን ነው የታገትነው? ስንላቸው ከላይ የተሰጠ ትዕዛዝ ነው፤ ሌላ ትዕዛዝ እስኪደርሰን ጠብቁ አሉን። ትዕዛዝ ስለመጣ እንድትቆሙ ተደርጓል። ሌላ ንግግር የለም። ልቀቋቸው የሚል ትዕዛዝ ሲሰጠን ደግሞ ትንቀሳቀሳለችሁ አሉን” ይላል።

እዚያው አዳይቱ ውለው አድረው ሰኞ፣ ግንቦት 18/2017 ዓ.ም. ላይ ተፈቅዶላቸው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ያስረዳል።

“ሰኞ ስምንት ሰዓት ላይ ለቀውን ጉዞ ጀመርን፤ ሆኖም ሰርዶ ሜዳ በሚባል መቀለ መገንጠያ ላይ አስቁመው አታልፉም አሉን” ሲል ለቢቢሲ ትግርኛ ሁኔታውን ገልጿል።

አዳይቱ ላይ ተሽከርካሪዎቹን ያስቆሟቸው የአፋር ፖሊሶች መሆናቸውን የገለጸው ይህ አሽከርካሪ፤ በሰርዶ ሜዳ ደግሞ የፌደራል ኬላ ስለሆነ ያስቆሟቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሆኑ ይናገራል።

ብዙ ሸቀጦችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለቀናት መቆማቸውን እና እስካሁን የተሰጠ መፍትሄ እንደሌለ አሽከርካሪዎቹ ይናገራሉ።

ከአፋር በተጨማሪ በወልዲያ አላማጣ መስመር ወደ ትግራይ ሸቀጥ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ መደረጋቸውን የገለጹት አሽከርካሪዎቹ በዚህ ኬላ ቢያንስ 30 የሚሆኑ የጭነት አሽከርካሪዎች መስመር ላይ እንዲቆሙ ተደርገዋል።

እነዚህ በወልዲያ ላይ እንዲቆሙ የተደረጉት መኪኖች በሰርዶ በኩል እንዳያልፉ ተከልክለው ከነበሩት መካከል እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።

በአፋር ክልል ያለውን ክልከላ አይተው ዞረው በአማራ ክልል ለማለፍ የሞከሩ ተሽከርካሪዎች ይገኙበታል።

“አራት ቀናትን አስቆጥረዋል፤ መጀመሪያ በሰርዶ ነው የመጡት። መስመሩ እንደተዘጋ ሲያውቁ ዞረው በወልዲያ ለመምጣት ሞክረው ነበር አልሆነም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አይታወቅም። አጋጣሚ ዕቃ አስጭኛለሁ [አሽከርካሪውን] ስጠይቀው ምክንያቱ ምን እንደሆነ አይታወቅም አለኝ። ቁሙ ነው የተባልነው፤ ትዕዛዝ ከላይ ነው የተሰጠን የሚሉት አሉኝ። መልሶ በወልዲያ አድርጎ ለመምጣት ሞክሮ ነበር እሱም አልተሳካም። እሱም ዝግ ሆነ። እስካሁን በሁለቱም መስመር ተዘግቶ ነው ያለው” ሲሉ ዮናስ የተባሉ የጭነት መኪና ባለቤት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እነዚህ ኬላዎች ቀደም ሲል በትግራይ ጦርነት ወቅት እርዳታ እና ማንኛውም ሸቀጦች ወደ ትግራይ እንዳያልፍ ለመከላከል ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው።

ሁሉም ተሽከርካሪዎች ሕጋዊ መሆናቸውን የሚገልጹ ሰነዶች እንዳሏቸው እና የታገዱበት ምክንያት እንዳልተገለጻቸው ተናግረዋል።

አሽካርካሪዎች እንዳያልፉ የከለከሏቸውን ፖሊሶች ቀርበው በሚጠይቁበት ወቅት እነሱም “ምክንያቱን እንደማያውቁ እና ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይናገራሉ።

ከጭነቶቹ መካከል በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች እንዲሁም ከጂቡቲ ደግሞ ስኳር እና ዘይት የጫኑ እንዳሉም አሽከርካሪዎቹ ያስረዳሉ።

“ንብረት አያልፍም ተብሎ መታገቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሆነ ነገር አለ ብሎ ወደ አላስፈላጊ ጥርጣሬ እንዲገባ አድርጓል። ይህ ሁኔታ ያለፈውን የጦርነት ሁኔታ እንዲያስታውስ አድርጎታል። የፈለገው የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርም ሕዝብን በንግድ መጉዳት ተገቢ አይደለም” ሲሉ እኚሁ የጭነት ተሽከርካሪ ባለቤት ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊት በአፋር በኩል ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ዱቄት ማለፍ አይችልም የሚል ክልከላ አጋጥሞናል የሚሉት ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት “ዱቄት እና ስንዴ በወልዲያ ነው የሚያልፈው” ይላሉ።

ክልከላው በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ ስጋትን ያጫረ ሲሆን፣ የሸቀጦች ዋጋ ንረት እንዳያመጣ ፍርሃት እንዳለ ቢቢሲ ከነዋሪዎች መረዳት ችሏል።

ለትግራይ ክልል የተለያዩ ሸቀጦች ይዘው በአፋር ክልል መስመር የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች ከ18/09/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሰርዶ በሚገኝ የፍተሻ ጣዚያ ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ እንደተከለከሉ ጠቅሶ የትግራይ ክልል ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ ረቡዕ፣ ግንቦት 20/ 2017 ዓ.ም. ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፏል።

ቢሮው በዚህ ደብዳቤው ላይ የፌደራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስለሁኔታው ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል። የክልሉ ንግድ ኤክስፖርት ቢሮ የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካሳሁን እስካሁን ድረስ በደብዳቤም ይሁን በሌሎች መንገዶች ከፌደራል መንግሥት ምላሽ አለመገኘቱን ተናግረዋል።

ባለፈው መጋቢት ወደ ትግራይ ክልል የሚጫን ነዳጅ ላይ እገዳ በተጣለበትን ጊዜም በተመሳሳይ ከፌደራል መንግሥት ግልጽ ምላሽ አለመገኘቱን አስታውሰዋል።

“ሁሌ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን፤ በነዳጅም ዙሪያ ደብዳቤዎችን እንጽፋለን። ነገር ግን ንግድ ሚኒስቴሩ ፎርማሊ [የምላሽ ደብዳቤ] መጻፍ ላይ ክፍተት አለው። በነዳጅም ዙሪያ በመደበኛ መልኩ ምላሽ አይሰጠንም” ብለዋል።

ተሽከርካሪዎች ላይ ክልከላ ለመጣል የሚያስችል ችግር ካለ በደብዳቤ ለቢሮው መገለጽ እንደነበረበት የሚያነሱት አቶ ካሳሁን፤ “አሁን ግን በስልክም፣ በደብዳቤም ምንም የተነገረን ነገር የለም። መዘጋቱን ያወቅነው እንደማንኛውም ሰው ነው። እንደ ቢሮ እንኳ ‘በዚህ በዚህ ምክንያት እንዲህ እየተደረገ ነው’ በሚል በመደበኛ መልኩ የተላከልን ነገር የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ፤ ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ ላይ የነበሩት ተሽከርካሪዎች በሙሉ “መሠረታዊ የሆኑ ሸቀጦችን” የጫኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። ማዳበሪያ እና ነዳጅ የጫኑ “አንድ ሁለት መኪናዎች” ግን በአፋር በኩል እንዲያልፉ መደረጉን አክለዋል።

ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮው ረቡዕ የጻፈው ደብዳቤ ምላሽ ባለማግኘቱ “የጉዳዩን አሳሳቢነት በመግለጽ” ሌላ ደብዳቤ ወደ ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለመላክ ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

“አሁን ጉዳዩን የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጭምር እንዲያዩት እየተደረገ ነው” ሲሉ ቢሮው እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስረድተዋል። በተጨማሪም ቢሮው የቆሙት መኪናዎች ብዛት እና የጫኗቸውን ሸቀጦች ዝርዝር እያጣራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሸቀጦቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ ለምን ክልከላ እንዳጋጣማቸው ከፌደራል መንግሥትም ሆነ ከአፋር ክልል የተሰጠ መግለጫ የለም።

ቢቢሲ ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግሥት አካላት በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።