ኦሎራቶ ሞንጋል
የምስሉ መግለጫ,ኦሎራቶ ሞንጋል

ከ 4 ሰአት በፊት

የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረችው ኦሎራቶ ሞንጋል በመግደል በፖሊስ ሲፈለግ የነበረው ግለሰብ ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲያደርግ ተገደለ።

ኦሎራቶ ከግለሰቡ ጋር ከተገናኘች ከሁለት ሰዓታት በኋላ መጥፋቷ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ አስክሬኗ በጆሀንስበርግ ተገኝቷል።

በባሕር ዳርቻዋ ከተማ አማንዚምቶቲ ዋነኛው የግድያ ተጠርጣሪ መደበቁን ፖሊስ እንደደረሰበት የፖሊስ ቃል አቀባይ አቲልንዳ ማቲ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው ፖሊሶች ላይ መተኮስ ሲጀምር ፖሊሶችም ተኩስ ከፍተዋል።

ተጠርጣሪው 28 መታወቂያዎችና በርካታ ስልኮች ይዞ መገኘቱን የአካባቢው የፖሊስ ኮሚሽነር ናላናላ ምክዋንዚ ተናግረዋል።

የኦሎራቶ ቤተሰብ ቃል አቀባይ ክሪሲልዳ ካናዳ “ኦሎራቶን ሳንቀብራት ፍትሕ ማግኘታችን ለቤተሰቡ ትልቅ እፎይታ ነው” ብለዋል።

የኦሎራቶ ግድያ በደቡብ አፍሪካ ሴቶች ስለሚደርስባቸው ጥቃት የውይይት በር የከፈተ ነው። ደቡብ አፍሪካ በዓለም ሴቶች ላይ በሚፈጸም ግድያ እና ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ቀዳሚ ናት።

የፖሊስ ሚኒስትር ሴንዞ መቹኑ የኦሎራቶ ግድያ “አሰቃቂ፣ ኢሰብአዊ” ነው ብለዋል።

“ወንዶች ቀላልና አጣዳፊ ነገር ነው የምነግራችሁ። እባካችሁን ሴቶችን መግደል አቁሙ” ሲሉም ተናግረዋል።

ሌሎች በግድያው የተጠረጠሩ ሰዎችን ፖሊስ እየፈለገ ሲሆን፣ የዋና ተጠርጣሪውን ቤተሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሎ መጠይቅ አድርጎላቸው ለቋቸዋል።

የተገደለው ዋና ተጠርጣሪው “ከእስር እንዲያመልጥ” በማድረግ እናቱ በፖሊስ ተይዘው ቆይተዋል።

የዋና ተጠርጣሪው አባት ኦሎራቶ የተገደለችበት መኪና ባለቤት ሲሆኑ እሳቸውም በፖሊስ ተይዘው ቆይተዋል።

መኪናው ውስጥ ፖሊስ የደም ፍንጣሪዎችን አግኝቷል።

ፈዚል ኑግባኔ፣ ፊላንጌኮሲ ሲኖንኮሉሌ ማካናያ እና ቦንጋኒ ምቱምኩሉ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ስም ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ባለፈው አንድ ሴትን ጠልፈው በመዝረፍ ታስረው ነበር። የተጠቀሙት መኪና ኦሎራቶ የተገደለችበት ነው።

ከግድያው ጋር በተያያዘ፤ ሴቶችን በመገበያያ ሕንጻ ዒላማ በማድረግ የሚጠልፍና የሚዘርፍ የወንጀል ቡድን ላይ ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።

“ከተዋወቋቸው በኋላ የፍቅር ቀጠሮ ይዘው በድጋሚ ሲገናኙ ነው ዝርፊያውን የሚፈጽሙት” ብለዋል የፖሊስ ቃል አቀባይ።

የ30 ዓመቷ ኦሎራቶ ሞንጋል በመገበያያ ሕንጻ ውስጥ ካገኘችው ሰው ጋር ከተገናኘት በኋላ ነበር የተገደለችው።

የደኅንነት ካሜራ ወደ ግለሰቡ መኪና ስትገባ ያሳያል።

ግለሰቡ ስሙን ጆን ብሎ እንደነገራት ጓደኞቿ ገልጸዋል። በዊታዋተርሳርድ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን እየተማረች ሳለ ነበር የተገናኙት።

ከግለሰቡ ጋር ከመገናኘቷ በፊት ለጓደኛዋ የጽሑፍ መልዕክት ልካለች።

ፖሊስ የኦሎራቶን አስክሬን ያገኘው በአደባባይ ተጥሎ ነው። በርካቶችም ፍትሕ እንዲሰፍን ጠይቀዋል። የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል።

የኦሎራቶ ጓደኞችና ቤተሰቦች “በዓላማና በፍቅር የምትኖር፣ ተወዳጅና ሐሳቧን ፊትለፊት የምትገልጽ” እንደነበረች ተናግረዋል።