
ከ 5 ሰአት በፊት
ሩሲያ ወደ ምዕራቡ ዓለም ከምትልከው ነዳጅ ዘይት ሽያጭ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደምታገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት ትልቁ የገንዘብ ምንጭ ሆኗታል።
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀች በኋላ ነዳጅ ዘይት (ሀይድሮካርበን) ወደ ውጭ በመላክ ያገኘችው ገቢ ዩክሬን ከምዕራባዊያን ወዳጆቿ ካገኘችው በሦስት እጥፍ የሚልቅ ነው።
ቢቢሲ የመረመረው መረጃ እንደሚያሳየው ምዕራባዊያን የዩክሬን አጋሮች ለኪየቭ ከሰጡት እርዳታ በላይ ከሩሲያ ጋዝ ለመግዛት ያወጡት ወጪ ይልቃል።
ይህንን የሚቃወሙ ወገኖች የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ከሩሲያ ጋዝ እና ነዳጅ መግዛት እንዲያቆሙ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ሩሲያ ምን ያህል ገቢ ታገኛለች?
ሩሲያ ከነዳጅ እና ጋዝ የምታገኘውን ገቢ ለጦርነቱ ማስኬጃ እየተጠቀመችበት ነው።
ነዳጅ እና ጋዝ ከሩሲያ ገቢ አንድ ሦስተኛውን የሚይዝ ሲሆን፣ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት ደግሞ 60 በመቶውን ድርሻ ይሸፍናል።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ከከፈተችው ጦርነት በኋላ የዩክሬን አጋሮች የሩሲያ የነዳጅ እና ጋዝ ምርት ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ እንዳይገባ አግዷል።
ነገር ግን ማዕቀብ የተጣለባት ሩሲያ ከጦርነቷ በኋላ ባለው ጊዜ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ 973 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። ከዚህ መካከል 228 ቢሊዮን ዩሮ የተገኘው ማዕቀብ ከጣሉ ሀገራት መሆኑን ሪሰርች ፎር ኢነርጂ ኤንድ ክሊን ኤር የተባለው ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት 209 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ የነዳጅ ምርት ከሩሲያ ሸምተዋል።
የኅብረቱ ሀገራት በነዳጅ ቱቦ አማካይ ከሩሲያ የሚያስገቡት ነዳጅ የተቋረጠው ባለፈው ጥር ዩክሬን ቱቦውን በመቁረጧ ነው። የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ አሁን ወደ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ በቱቦ ይተላለፋል።
የድርጅቱ መረጃ እንደሚሳየው የሩሲያ ነዳጅ ከሚተላለፍባቸው ሀገራት አንደኛዋ ቱርክ ናት። የሚተላለፈው የነዳጅ መጠን ባለፈው ጥር 26 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።https://flo.uri.sh/visualisation/23503127/embed?auto=1
ሦስተኛ ሀገር
ሩሲያ በቀጥታ ከምትሸጠው በተጨማሪ በሦስተኛ ሀገር በኩል ተጣርተው የሚመጡ የነዳጅ ምርቶችም አሉ።
የምርምር ተቋሙ እንደሚጠቁመው በቱርክ እና በሕንድ የሩሲያን ድፍድፍ ነዳጅ አጣርተው ማዕቀብ ለጣሉ ሀገራት የሚሸጡ ኩባንያዎች አሉ።
እነዚህ ኩባንያዎች 6.1 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ አጣርተው ማዕቀብ ለጣሉ ሀገራት ሸጠዋል።
የሕንድ ፔትሮሊየም ሚኒስቴር የምርምር ማዕከሉን መረጃ አጣጥሎ “የሕንድን ስም ለማጠልሸት የተቃጣ ውንጀላ ነው” ብሏል።
የተቋሙ ተመራማሪ የሆኑት ቫይባቭ ራጉናዳን “ማዕቀብ የጣሉ ሀገራት እንደሚቀበሏቸው ያውቃሉ። ሕጋዊ እንደሆነም ያውቃሉ። ይህን ጉዳይ ለማስቆም የሞከረ ማንም የለም” ይላሉ።
የቀድሞው የሩሲያ የኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ እና አሁን የፑቲን ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑት ቭላድሚር ሚሎቭ ሩሲያ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ “ጠንካራ ሊሆን” ይገባል ይላሉ።
ነገር ግን አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን አያደርጉም የሚል ስጋት አላቸው።
ምዕራባዊያን ሀገራት ከሩሲያ የሚያስመጡትን ነዳጅ እንዲያቆሙ የሚቀሰቅሱ ተቋማት አውሮፓውያኑ ሀገራት የሩሲያን ፈሳሽ የተፈጥሮ ነዳጅ ማስቀረት ይችላሉ ሲሉ ይከራከራሉ።
የትራምፕ ዕቅድ
ቢቢሲ ያናገራቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት ዶናልድ ትራምፕ የኦፔክ ሀገራት የነዳጅ ዋጋን ዝቅ ካደረጉ የዩክሬን ጦርነት ይቆማል ሲሉ ያቀረቡት ሐሳብ የሚያስኬድ አይደለም ይላሉ።
“ሞስኮው ያሉ ሰዎች በዚህ ሐሳብ እየሳቁ ነው። ምክንያቱም በዚህ ዕቅድ መሠረት ዋነኛ ተጎጂዎች የሚሆኑት የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ናቸው” ይላሉ ሚሎቭ።
ራጉናዳን እንደሚሉት ሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ለማምረት የምታወጣው ወጪ የኦፔክ አባል ሀገር ከሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ዝቅ ያለ ስለሆነ አትጎዳም ይላሉ።
“ሳዑዲ አረቢያ በዚህ ሐሳብ አትስማማም። ይህ ከዚህ ቀደም ተሞክሯል። ይህ ሐሳብ በሳዑዲ አረቢያ እና በሩሲያ መካከል ግጭት መፍጠሩ ይታወሳል።”
ሮዝነር፤ ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን ድጋፋቸውን እየገለፁ የሩሲያን ነዳጅ መግዛታቸው ግብዝነት ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
“በአንድ በኩል ወራሪውን አካል እየተቃወምን ተወራሪውን እየደገፍን ነው። ነገር ግን ወራሪውን በገንዘብ እየደገፍን እንገኛለን።”