ትራምፕ

ከ 3 ሰአት በፊት

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከውጭ በሚገቡ ብረትና አልሙኒየም ላይ ከ25 እስከ 50 በመቶ ቀረጥ መጣሏን አስታወቁ።

በፔንስልቬንያ ባደረጉት ንግግር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ቀረጡ እንደሚተገበርም ተናግረዋል።

ቀረጡ ከቻይና የሚገባ ምርት ላይ ላለመመርኮዝና የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ታልሞ እንደተጣለም ገልጸዋል።

የአሜሪካ የብረት አምራች ዩኤስ ስቲል ከጃፓኑ ኒፖን ስቲል ጋር በመጣመር 14 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚደረግ ትራምፕ ተናግረዋል።

ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ አነጋጋሪ ታሪፎች ሲጥሉ ቆይተዋል።

“ምርቶች በሌላ አገር እየተሠሩ ከዚህ በኋላ አይገቡም። አሜሪካዊያን ብረት አምራቾች የሚገባቸውን 5ሺህ ዶላር ጉርሻ ያገኛሉ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

አሜሪካና ጃፓን አብረው ለመሥራት መወሰናቸውን ተከትሎ እንዴት ጃፓን የሠራተኞችን መብት ታስጠብቃለች? የሚለው የአሜሪካዊያን ብረት አምራቾች ጥያቄ ነው።

ትራምፕ የአሜሪካን የብረት ዘርፍ “እንደታደጉ” ሲናገሩ በርካቶች በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

“50 በመቶ ቀረጥ ሲጣል ማንም ድንበራችንን አልፎ አይገባም። ፔንስልቬንያ ተመልሳ የአሜሪካ የጀርባ አጥንት ትሆናለች” ብለዋል።

የአሜሪካ የብረት ምርት ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲቀዛቀዝ ዘርፉን በዓለም አቀፍ ንግድ እየመሩ ያሉት ቻይና፣ ሕንድና ጃፓን ናቸው።

ወደ አሜሪካ ከሚገባው ብረት አንድ አራተኛው ከውጭ አገራት የሚገዛ ነው። አሜሪካ ከሜክሲጆና ካናዳም ብረት ታስገባለች።

ትራምፕ በአገራት ላይ እየጣሉ ያሉት አንዳንድ ታሪፎች በፍርድ ቤት ክስ ከቀረበበት በኋላ ነው ብረትና አልሙኒየም ላይ የጣሉትን ቀረጥ ይፋ ያደረጉት።

ዓለም አቀፍ የንግድ ፍርድ ቤት ቀረጥ እንዲገታ ከወሰነ በኋላ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤቱ ትራምፕ ቀረጥ መጣል እንደሚችሉ ወስኗል።

በክሱ ውስጥ ብረትና አልሙኒየም ላይ የጣሉትን ቀረጥ አልተካተተም።

የአሜሪካ ብረት አምራቾች ማኅበር አባል ጆጆ ቡርገስ “ለብረት አምራቾች ታላቅ ቀን ነው” ብለዋል።

አዲስ የብረት አምራች ትውልድ ወደ ዘርፉ እንደሚገቡም ተስፋ ሰንቀዋል። የትራምፕ ደጋፊ ባይሆኑም “የአሜሪካ አምራቾችን የሚጠቅም ነገር ሲሆን አልቀበልም አልልም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እስካሁን ድረስ የትራምፕ ቀረጥ ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ቀውስ ሲፈጥር ታይቷል።

በአሜሪካና የቅርብ አጋሮቿ መካከል መቃቃርም ፈጥሯል።

በተለይም በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል።