ህሙማኑ ከሆስፒታሉ ሲወጡ

ከ 3 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ አገልግሎት እየሰጠ የነበረው የመጨረሻው ሆስፒታል ህሙማን እና የጤና ባለሙያዎች ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ፤ አገልግሎቱ መቋረጡን የተቋሙ ዳይሬክተር ገለጹ።

ጦሩ ጃባሊያ የሚገኘውን አል አውዳ ሆስፒታል “ለሁለት ሳምንታት” ከበባ ውስጥ ካስገባው በኋላ፤ ህሙማኑ እንዲወጡ መደረጉን ዶክተር መሐመድ ሳልሃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በሰሜን ጋዛ ሰርጥ አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ተቋም እንደሌለም አክለዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ አስተያየት አልሰጠም።

የእስራኤል ጦር ሐሙስ ምሽት፣ግንቦት 21/ 2017 ዓ.ም አል አውዳ ሆስፒታልን ጨምሮ ነዋሪዎች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በአካባቢው “የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ” አለ ያለው ጦሩ፤ ጥቃቱንም እንደሚያሰፋ አስጠንቅቋል።

“ሆስፒታሉን ለቀን በመሄዳችን በጣም አዝነናል። ነገር ግን የእስራኤል ወራሪ ኃይሎች እኛ ለቀን ካልወጣን ውስጥ ገብተው ያለውን ሁሉ እንደሚገድሉ አስፈራሩን” ሲሊ ዶከተር ሳልሃ ለቢቢሲ በላኩት የድምጽ መልዕክት አስረድተዋል።

“ሆስፒታሉን በቦምብ ይደበድቡት ነበር። የህሙማን እና የሰራተኞቻችን ህይወት አስበን ወጣን” ብለዋል።

ሆስፒታሉ ሐሙስ እኩለ ቀን ላይ “ከታንኮች በርካታ የቦምብ እና ተኩስ ጥቃት” እንደተፈጸመበት ዶክተሩ ገልጸዋል።

ከዚያም በዚያኑ ቀን ሰባት ሰዓት ገደማ ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ የእስራኤል ጦር ትዕዛዝ ቢሰጣቸውም፤ መጀመሪያ ላይ የጤና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ስላሉ አልቀበልም ማለታቸውን ገልጸዋል።

ከአስር ሰራተኞቻው ጋር በሆስፒታሉ ለመቆየት ለጦሩ ሃሳብ ቢያቀርቡም፤ የእስራኤል ጦር ፈቃደኛ አልነበረም።

ከሰባት ሰዓታት በኋላም ምሽቱ 2፡30 ገደማ ህሙማኑ እና ሰራተኞቹ ሆስፒታሉን ለቀው ወጥተዋል።

የጤና ባለሙያዎች ህሙማኑን ተሸክመው ከሆስፒታሉ ርቀው ወደቆሙ አምቡላንሶች ወስደዋቸዋል።

ለዚህም ምክንያቱ በሆሰፒታሉ ዙሪያ ያሉ መንገዶች “ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው” ነው።

ህሙማኑ በጋዛ ከተማ ወደሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል ተወስደዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሐኖም ገብረ እየሱስ የአል አውዳ መዘጋት በሰሜን ጋዛ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል እንዳይኖር አድርጎታል ብለዋል።

በተጨማሪም ሲቪሎች እና የጤና ባለሙያዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበው “ሆስፒታሎች በፍጹም ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ወይም ወታደራዊ ኢላማዎች ሊሆኑ አይገባም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የመጨረሻው የጤና ተቋም አገልግሎት መስጠት አቁሟል የተባለው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረቶች በቀጠለበት ወቅት ነው።

አሜሪካ ያቀረበችው የተኩስ አቄም ስምምነት ዕቅድ ሐማስ እየገመገመው እንደሆነ የገለጸው ዋይት ሃውስ ፤እስራኤል ተቀብላዋለች ብሏል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነት ላይ ለመድረስ “ተቃርበዋል” ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።

ሐማስ በበኩሉ እስራኤል የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ያላትን ቁርጠኝነት የማያሳይ እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎችን የማይመልስ ነው ብሎታል።

እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃቷን ቀጥላለች።

ባለፉት 24 ሰዓታት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 72 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ53 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።