
31 ግንቦት 2025
የአውሮፓውያኑ 2024/25 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ውድድር በሊቨርፑል አሸናፊነት ተጠናቋል።
ግብፃዊው አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ የውድድር ዘመን ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ሳላህ 29 ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ለግብ የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ አቀብሏል።
ካሜሩናዊው ብራያን ምቡዌሞ ድንቅ ዓመት አሳልፏል። 20 ግቦችን ያስቆጠረው የብሬንትፈርዱ አጥቂ በዝውውር መስኮቱ ስሙ እየተነሳ ነው።
ሌሎች በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ደምቀው የታዩ አፍሪካውያን ተጫዋቾች እነማን ናቸው?
ድንቅ አጥቂዎች
ሞሐመድ ሳላህ፣ ብራያን ምቡዌሞ፣ ዮዋን ዊሳ
የ32 ዓመቱ ሞሐመድ ሳላህ 130 ጊዜ ኳስ ወደ ተቃራኒ መረብ ሰዷል። ከዚህ መካከል 61 ኳሶች ዒላማቸውን የጠበቁ ነበሩ።
ሳላህ 89 ጊዜ የግብ አጋጣሚ ፈጥሯል። ይህም በሊጉ ሁለተኛ ያደርገዋል። ምቡዌሞ በ70 የግብ አጋጣሚዎች አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በውድድር ዘመኑ 20 ግቦችን ያስቆጠረው ምቡዌሞ በብሬንትፈርድ ታሪክ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ቁጥር አንድ መሆን ችሏል።
ሌላኛው የብሬንትፈርድ አጥቂ የዲሞክራቲክ ኮንጎው ዮዋን ዊሳ ሲሆን፣ በውድድር ዘመን 19 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።
ጋናዊው አንቶኒዮ ሴሜንዮ ደግሞ በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች ጨምሮ 11 ግብ በስሙ አስመዝግቧል።
ጎልተው የታዩ አማካዮች

አሌክስ ኢዮቢ፣ ኢድሪሳ ጉዬ፣ ካርሎስ ባሌባ
ናይጄሪያዊው አሌክስ ኢዮቢ 9 ግቦችን በማስቆጠር እና ስድስት ኳሶችን በማመቻቸት በሊጉ ምርጥ አፍሪካዊ አማካይ መሆኑን አስመስክሯል። ከኢዮቢ ቀጥሎ የማንቸስተር ዩናይትዱ አማድ ዲያሎ ይገኛል። ነገር ግን ዲያሎ በጉዳት ምክንያት በርካታ ጨዋታዎችን ሳይሰለፍ ቀርቷል።
ጋናዊው የአርሰናል አማካይ ቶማስ ፓርቴ በርካታ የተሳኩ ኳሶችን በማንሸራሸር ከአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ቁንጮው ቢሆንም ክለቡ አርሰናል ዘንድሮም ዋንጫ ሳይቀናው ቀርቷል።
ሴኔጋላዊው የ35 ዓመት አማካይ ኢድሪሳ ጉዬ ለኤቨርተን ወሳኝ መሆኑን አስመስክሯል። ኢድሪሳ 133 ኳሶች ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች መንጠቅ ችሏል።
ካሜሩናዊው አማካይ ካርሎስ ባሌባ በብራይተን ማሊያ ድንቅ የውድድር ዘመን አሳልፏል። ወጣቱ አማካይ በበርካታ ክለቦች እየተፈለገ ይገኛል።
ደጀን ተከላካዮች

ካልቪን ባሲ፣ አሮን ዋን ቢሳካ፣ ራያን አይት-ኑሪ
በቅርቡ ለዲሞክራቲክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ለመሰለፍ የተስማማው አሮን ዋን ቢሳካ 66 ጊዜ ኳስ በመንጠቅ አስተማማኝ ተከላካይ መሆኑን አሳይቷል። ቢሳካ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ በዌስት ሀም ደጋፊዎች ተመርጧል።
አልጄሪያዊው ራያን አይት-ኑሪ በክንፍ በኩል የሚፈጥራቸው ዕድሎች ብዙ አድናቆት ተችሯቸዋል። አይት-ኑሪ ለክለቡ ዎልቭስ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።
ናይጄሪያዊው የኖቲንግሀም ፎሬስት የቀኝ ክንፍ መስመር ተጫዋች ድንቅ የውድድር ዘመን ካሳለፉ ከዋክብ መካከል ነው።
ሌላኛው ናይጄሪያዊ ተከላካይ ካልቪን ባሲ በፉልሀም ማሊያ አስገራሚ የሚባል ብቃቱን ያሳየ ሲሆን፣ የእንግሊዝና የአውሮፓ ክለቦች ዓይናቸውን ጥለውበታል።
ሞሮኳዊው የማንቸስተር ዩናይትድ ተከላካይ ኑሳይር ማዝራዊም በሊጉ አሉ ከሚባሉ የኋላ መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑን ቁጥሮች ያሳያሉ።
ደካማ ቁጥሮች

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ብቸኛው አፍሪካዊ በረኛ የማንቸስተር ዩናይትዱ አንድሬ ኦናና ቢረሳው የሚመኘው የውድድር ዘመን አሳልፏል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በ50 ዓመታት ውስጥ ደካማ የሚባል ውጤት አስመዝግቦ ነው የጨረሰው።
ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ በዘጠኝ ጨዋታዎች ግብ ባይቆጠርበትም በ25 ጨዋታዎች 44 ግቦች አስተናግዷል።
የ29 ዓመቱ በረኛ ሦስት ጊዜ የሠራቸው ስህተቶች ግብ ሆነው ተቆጥረዋል።
በፕሪሚዬር ሊጉ በርካታ ጥፋት በመፈፀም አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የቦርንመዙ ሴሜንዮ ነው። ጉዬ እና ዱኩሬ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ግብፃዊው የኢፕስዊች አማካይ ሳሚ ሞርሲ 10 ጊዜ ቢጫ ካርድ በማየት አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የዌስት ሀሙ አጥቂ ጋናዊው ሞሐመድ ኩዱስ ስድስት ጊዜ የሞከራቸው ኳሶች የጎሉን አግዳሚ ገጭተው ተመልሰዋል።
በተመሳሳይ ኒኮላስ ጃክሰን፣ ሳላህ እና ፓልመር እያንዳንዳቸው 6 ጊዜ የጎሉን ቋሚዎች መትተዋል።