
ከ 5 ሰአት በፊት
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር የተማሪዎችን የቪዛ ቀጠሮ በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ማድረጉን ተከትሎ በመላው ዓለም ተማሪዎች ጭንቀት ውስጥ ናቸው።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ የተመለከተው ይፋዊ ማስታወሻ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአመልካች ተማሪዎችን የማኅበራዊ ገፅ ፍተሻውን እስኪያጠናክር ድረስ የቪዛ ቀጠሮዎች በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
እርምጃው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዘብተኛ በሚሏቸው ታዋቂ ዩኒቨርስቲዎች ላይ እየወሰዱት ያለው ሰፊ እርምጃ አካል ነው።
ፕሬዝዳንቱ በካምፓሱ ፀረ ሴማዊነትን አልተቆጣጠረም ያሉትን ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል እገዳ ጥለውበታል።
ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ክስ በመመሥረት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ ዳኛው የትራምፕን እገዳ ለጊዜው አንስቷል።

የትኞቹ ተማሪዎች የበለጠ ይጎዳሉ?
የውጭ አገራት ተማሪዎችን የሚመዘግበው ኦፕን ዶርስ በተባለው ድርጅት መረጃ መሠረት ከ2023 እስከ 2024 ባለው ትምህርት ዘመን በአሜሪካ ኮሌጆች ከ210 አገራት የመጡ 1.1 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበዋል።
ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ለመማር ከመጡ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት የሕንድ ተማሪዎች ሲሆኑ ቁጥራቸውም 330 ሺህ ነው።
ቻይና 280 ሺህ ተማሪዎችን በመላክ ሁለተኛውን ከፍተኛ ቁጥር የያዘች ሲሆን፤ ደቡብ ኮሪያ፣ ካናዳ፣ ታይዋን፣ ቬትናም፣ ናይጄሪያ፣ ባንግላዲሽ፣ ብራዚል እና ኔፓል ይከተላሉ።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር የቻይና ተማሪዎች ከኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ወይም በወሳኝ የትምህርት ዘርፍ የሚያጠኑትን ጨምሮ ቪዛቸው እንደሚሰረዝ ተናግረዋል።https://flo.uri.sh/visualisation/23481722/embed?auto=1
የዚህ ዕቅድ አካል የቻይና እና ሆንግ ኮንግ የቪዛ አመልካቾች “ምርራን ማሻሻል” ሲሆን፣ መመዘኛዎች ይስተካከላሉ ተብሏል።
እስካሁን በእርምጃው ምክንያት ምን ያህል የቻይና ተማሪዎች ተፅዕኖ እንደሚደርስባቸው ግልፅ አይደለም።
ቻይና ድርጊቱን “በፅኑ የተቃወመች” ሲሆን፤ አሜሪካ ገንቢ ግንኙነት እንድትከተል አሳስባለች።
የትራምፕ አስተዳደር በሺህዎች የሚቆጠሩ ቪዛዎችን ሲሰርዝ በርካታ የውጭ አገር ተማሪዎችን ደግሞ ከአገር ለማስወጣት እንቅስቃሴ ጀምሯል።
ባለፈው መጋቢት ማርኮ ሩቢዮ ፍልስጤምን የሚደግፉ ሰልፎችን ለመቆጣጠር አሜሪካ 300 የውጭ አገር ተማሪዎችን ቪዛ መሰረዟን ገልፀዋል።
ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ በፍርድ ቤት ማመልከቻው ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ፈቃድ መነጠቁ በዩኒቨርስቲው ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል ብሏል።
ዩኒቨርስቲው እርምጃው በተማሪዎች እና ምሁራን ላይ “ከፍተኛ ጭንቀት” እየፈጠረ መሆኑንም ገልጿል።
ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓቶችን አለመካፈል፣ ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን መሰረዝ እና ወደ ሌሎች ኮሌጆች ለመዘዋወርም እያመነቱ ስለመሆኑ አስረድቷል።
አንዳንዶች ደግሞ ግጭት ወይም የፖለቲካ አፈና ወዳለባቸው አገሮቻቸው በግዴታ እንመለሳለን የሚል ስጋት እንዳላቸውም ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ሌሎች አማራጮችስ?
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ በርካታ ተማሪዎችን እየሳቡ ነው።
ይሁን እንጂ በኢሚግሬሽን ሕጎች ምክንያት የተማሪዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል።
ለአብነት ያህል ካናዳ ትቀበላቸው የነበሩ ተማሪዎችን ቁጥር ቀንሳለች። ወደ አገሪቱ የሚገቡ ተማሪዎችን መጠን ለመገደብ ያቀርቡት የነበረውን በስማቸው የተመዘገበ ሀብት እና ንብረት ግምት ከፍ አድርጋለች።
ኦክስፎርድ እና ኬምብሪጅን የመሰሉ ታዋቂ ዩኒቨርስቲዎች ያሏት ዩናይትድ ኪንግደም ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች የሚቀርቡ ዕድሎችን ገድባለች።
ከጥር 2024 ጀምሮ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዳያመጡ እንዲሆም አዳዲስ ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት ወደ ሥራ ቪዛ እንዳይቀይሩ ከልክላለች።
ሌላኛዋ ትልቅ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ተቀባይ አገር የሆነችው አውስትራሊያ ከውጭ አገራት የሚመጡ ተማሪዎች ቁጥር ላይ ገደብ ጥላለች።
በአንፃሩ ሆንግ ኮንግ አሜሪካ ፊቷን ያዞረችባቸውን ተማሪዎች ለመቀበል በሯን ከፍታለች።
የማሌዢያው ሰንዌይ ዩኒቨርስቲም የአሜሪካን እርምጃ ተከትሎ ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች ግብዣ አቅርቧል።
በአውሮፓ ጀርመን ከአሜሪካ ውጭ አማራጮችን ለሚያማትሩ ተማሪዎች መዳረሻ እየሆነች ነው።
አገሪቱ በ2025 ከ400 ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ተቀብላ ታስተናግዳለች።
ባለፈው መጋቢት ወር ከአውሮፓ ኅብረት ውጪ የመጡ ተማሪዎች በሳምንት እስከ 20 ሰዓታት እንዲሠሩም ፈቅዳለች።
ባለፉት 15 ዓመታት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገበያ መሠረታዊ ለውጥ የታየ ሲሆን፤ ምሥራቅ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ ዓይን ውስጥ እየገቡ ነው።