የተሸፈነ አስከሬንን እያዩ የሚያለቅሱ ወንዶች እና ሴቶች

ከ 5 ሰአት በፊት

በደቡባዊ ጋዛ ራፋ በሚገኝ እርዳታ ማከፋፈያ ስለተከሰተው እና ስላወዛገበው ጥቃት ቀይ መስቀል በጥይት ወይንም በተተኳሽ ፍንጥርጣሪዎች “በርካታ ሰዎች ተጎድተው” ወደ ድርጅቱ የመስክ ሆስፒታል መምጣታቸውን ገለፀ።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ 21 ሰዎች ሆስፒታል ሲደርሱ “ሞተው የነበረ መሆኑን” ከተጎዱት 179 ሰዎች መካከል ደግሞ ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚገኙበት ገልጿል።

የድርጅቱ መግለጫ የወጣው በጋዛ ሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባነጣጠረ እና “በእስራኤል ወታደሮች የተከፈተ ተኩስ” የተነሳ ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ያስታወቀበት መግለጫ ካወጣ በኋላ ነው።

ነገር ግን የእስራኤል መከላከያ ኃይል የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤት በማለት ባወጣው መግለጫ ሠራዊቱ በእርዳታ ማዕከሉ አቅራቢያ ወይም ውስጥ ባሉበት ወቅት አልተኮሱም ብሏል።

የእስራኤል ጦር በተጨማሪም ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምሥል የታጠቁ እና ጭምብል ያደረጉ ሰዎች በአቅራቢያው በምትገኘው ኻን ዮኒስ እርዳታ በሚቀበሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ እና ሲተኩሱ ያሳያል ብሏል።

ቢቢሲ የተንቀሳቃሽ ምሥሉን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ወደ ጋዛ እንዲገቡ አትፈቅድም። ይህም በግዛቱ ውስጥ ያለውን ነገር ማረጋገጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከሉን የሚመራው የጋዛ ሂውማኒቴሪያን ፋውንዴሽን ሐማስ በቦታው ደርሷል ሲል የተናገረውን ጥቃት እና ጉዳት ውድቅ አድርጓል።

እስከ እሁድ አመሻሽ ድረስ ስለተፈጠረው ነገር በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በመግለጫው “179 ሴቶችን እና ሕጻናትን ጨምሮ በጅምላ የቆሰሉ ሰዎች በራፋህ የሚገኘው የቀይ መስቀል የመስክ ሆስፒታል “እሁድ ዕለት ማለዳ ላይ ደርሰዋል” ብሏል።

“አብዛኞቹ በጥይት ወይም በተተኳሽ ፍንጥርጣሪዎች ቆስለዋል” እንዲሁም “21 ታካሚዎች ደግሞ ሆስፒታል ሲደርሱ መሞታቸው ታውቋል።”

ቀይ መስቀል በመግለጫው ላይ የገለፀው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከሐማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ የተለየ ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም።

“ሁሉም ታካሚዎች የእርዳታ ማከፋፈያ ቦታ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ እንደነበር ተናግረዋል” ሲል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ገልጿል።

ቀይ መስቀል “የመስክ ሆስፒታሉ ከተቋቋመ አንድ ዓመት የሞላው ቢሆንም በአንድ ክስተት በጦር መሳሪያ የቆሰሉ በርካታ ሰዎች” ሲቀበል የመጀመሪያው መሆኑን ተናግሯል።

ሆስፒታሉ ያሉት 60 አልጋዎች ሲሆን፣ ይህም ካለው አቅም “እጅግ የላቀ” መሆኑን አስታውቋል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በበኩሉ “ብዙ ሰዎች ጉዳት” ደርሶ ድጋፍ መስጠቱን እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እየታከሙበት የሚገኘው የናስር ሆስፒታል የደም ባንክ ባዶ ነበር ብሏል።

በዚህም የተነሳ የሕክምና ባለሙያዎች ደም በመለገስ የተጎዱትን ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን ገልጿል።

የድርጅቱ የድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ ክሌር ማኔራ ክስተቱ “ይህ አዲስ የእርዳታ አሰጣጥ ሥርዓት ሰብዓዊነት የጎደለው፣ አደገኛ እና በጣም ውጤታማ ያልሆነ መሆኑን በድጋሚ አሳይቷል” ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ በመግለጫው “በቅርብ ሰዓታት ውስጥ በጋዛ ሰርጥ የሰብዓዊ እርዳታ ማከፋፈያ ቦታ በጋዛ ነዋሪዎች ላይ የተቃጣውን ጥቃት በተመለከተ በእስራኤል መከላከያ ላይ ከባድ ውንጀላዎችን ጨምሮ የውሸት ዘገባዎች ተሠራጭተዋል።

“የመጀመሪያው የምርመራ ግኝት እንደሚያመለክተው የመከላከያ ሠራዊቱ በሰብዓዊ እርዳታ ማከፋፈያ ቦታ ላይ ወይም በሰላማዊ ሰዎች ላይ አልተኮሰም እና ከዚህ ጋር የተያያዙት ዘገባዎች ውሸት ናቸው” ሲል አክሏል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአምቡላንስ ናስር ሆስፒታል መጥተው
የምስሉ መግለጫ,በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአምቡላንስ ወደ ናስር ሆስፒታል ተወስደዋል

ኤምኤስኤፍ ቢያንስ ሁለት ታካሚዎች እነሱ እና ሌሎች እርዳታ ለማግኘት ሲሞክሩ የነበሩ ሰዎች በጥይት መመታታቸውን መናገራቸውን ገልጿል።

የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ኑር አልሳካ እንደተናገሩት የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች ሕሙማንን በማከም ላይ በነበሩበት ወቅት “የአንድ ባልደረባቸው ወንድም ከማዕከሉ እርዳታ ለመቀበል ሲሞክር መሞቱን ማረጋገጫ አግኝተዋል” ብለዋል።

በማዕከላዊ ጋዛ ኔትዛሪም ኮሪደር ውስጥ በተለየ የእርዳታ ማዕከል አቅራቢያ ሌላ ተመሳሳይ ጥቃት ተከስቷል የተባለ ሲሆን፣ የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ 14 ሰዎች ቆስለዋል ብሏል።

ቢቢሲ በናስር ሆስፒታል በጥይት ወይም በፍንጣሪዎች የተጎዱ 200 ያህል ሰዎች ማከማቸውን የተናገሩ ዶክተሮችን አነጋግሯል።

በአካባቢው የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎች በጋሪ ተጭነው ወደ ቀይ መስቀል የመስክ ሆስፒታል ሲወሰዱ የሚያሳይ ምሥል አጋርተዋል።

ቢቢሲ አስከሬኖች በጋሪ እና በጭነት መኪና ወደ ናስር ሆስፒታል ሲወሰዱ የሚያሳይ ምሥልም ተመልክቷል።

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ 31 ሟቾችን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ወደ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን አስታውቋል።

ከተጎዱት ውስጥ 79ኙ ወደ ናስር ሆስፒታል መወሰዳቸውን የብሪታንያ በጎ አድራጎት የሕክምና እርዳታ ለፍልስጤማውያን ባልደረቦች ተናግረዋል።

የተገደሉት እና የተጎዱት “በዋነኛነት የተመቱት በቀጥታ በተተኮሰ ጥይት ነበር፣ ብዙ ተጎጂዎች በቀጥታ ወደ ጭንቅላታቸው ወይም ደረታቸው በተተኮሰ ጥይት ነው የተመቱት” ሲሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሠራተኞች ተናግረዋል።

ራፋህ የሚገኝ አንድ የመከላከያ ሠራዊት ወታደር ለቢቢሲ እንደተናገረው የእስራኤል ወታደሮች በሕዝቡ አቅራቢያ መተኮሳቸውን አረጋግጦ ወደ ሰላማዊ ሰዎች ግን አልተተኮሰም፤ ማንም አልተመታም ብሏል።

የጋዛ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት “የእስራኤል ወታደሮች መኪና ላይ በመሆን በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ በከፈቱት ተኩስ” ከ100 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

ክስተቶቹ በቅርብ ጊዜ የእስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የእርዳታ እና የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶችን ተደራሽነት በእጅጉ በተገደቡባት ራፋህ ውስጥ ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ሁኔታ አጉልተው ያሳያሉ።

የጋዛ ሂውማኒቴሪያን ፋውንዴሽን በመላው ጋዛ በተመረጡ ቦታዎች ምግብ ሲያከፋፍል የቆየ በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፍ አዲስ ድርጅት ነው።

የጋዛ የሂውማኒቴርያን ፋውንዴሽን በዚህ ሳምንት 4.7 ሚሊዮን ምግቦችን ማከፋፈሉን ተናግሯል።

ይህንን መረጃ ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ አልቻለም።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1,200 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሌሎች መታገታቸውን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

ከዚያ ወዲህ በተቀሰቀሰው ጦርነት በጋዛ ቢያንስ 54,418 ሰዎች መሞታቸውን የግዛቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።