ድምፅ ማጉያ እና የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች

ከ 8 ሰአት በፊት

ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያን የሚለየው አጥር የኤሌክትሪክ ገመድ አለው። ይህን አጥር የሚጠብቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችም ተደርድረዋል።

በየመሐሉ ቅጠልማ የወታደር ልብስ ቀለም የተቀቡ ግዙፍ የድምፅ ማጉያዎች ተሰቅለዋል።

የቢቢሲዋ ጃን ማኬንዚ ባለፈው ወር ወደሥፍራው አቅንታ በነበረበት ወቅት አንደኛው ድምፅ ማጉያ የደቡብ ኮሪያ ሙዚቃ ሲለቅ ሰምታለች።

ሙዚቃው ቅኔ አዘል ነው። “ወደ ውጭ ስንጓዝ ጉልበት እናገኛለን” ይላል። ሰሜን ኮሪያዊያን ከሀገራቸው መውጣት አለመቻላቸውን በሾርኔ ለመንካት የተከፈተ ሙዚቃ ነው።

ከሰሜን ኮሪያ ድምፅ ማጉያም ወታደራዊ ፕሮፖጋንዳ የሚነዛ ሙዚቃ ይሰማል።

ምንም እንኳ ደቡብ ኮሪያ እና ሰሜን ኮሪያ ጥይት ባይተኳኮሱም አሁንም ጦርነት ላይ ናቸው። ይህ ጦርነት የመረጃ ጦርነት ነው።

ደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን መረጃ ታሾልካለች። የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ደግሞ ይህ የመረጃ ፍሰት ለመግታት ተግተው ይሠራሉ። ሕዝባቸው ከውጭ የሚመጣ መረጃ እንዲሰማ አይሹም።

ሰሜን ኮሪያ ኢንተርኔት ዘልቆ ያልገባባት የዓለማችን ብቸኛዋ ሀገር ናት ማለት ማካበድ አይደለም። ሁሉም የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ጣቢያዎች እንዲሁም ጋዜጣዎች የመንግሥት ናቸው።

“ይህ የሆነበት ምክንያት የኪም ቤተሰብ ታሪክ አፈ-ታሪክ መሆኑ ነው። ለሕዝባቸው የሚናገሩት አብዛኛው ነገር ሐሰት ነው” ይላሉ ማርቲን ዊሊያምስ።

ማርቲን መቀመጫውን ዋሺንግተን ያደረገው ስቲምሰን ማዕከል ነባር አባል ናቸው። በሰሜን ኮሪያ ቴክኖሎጂ እና መረጃ ፍሰት ጥናት ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው።

ደቡብ ኮሪያ እንዲህ ነው የምታስበው – መንግሥት የሚነዛውን ሐሰት ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ ከተቻለ የሰሜን ኮሪያው አገዛዝ ይፈራርሳል።

የድምፅ ማጉያዎቹ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ከሚጠቅምባቸው መሣሪያዎቹ መካከል ናቸው።

ጥቂት የሚባሉ የሬድዮ ጣቢያዎች እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች በድቅድቅ ጨለማ ወደ ሰሜን ኮሪያ መረጃ ያስተላልፋሉ። ሰሜን ኮሪያዊያን ይህን መረጃ መስማት የሚችሉት ከብርሃን እና ከመንግሥት ጆሮ ተደብቀው ነው።

ደቡብ ኮሪያዊቷ ሙዚቀኛ ጄኒ
የምስሉ መግለጫ,የደቡብ ኮሪያዊቷ ሙዚቀኛ ጄኒ ሥራዎችና ድራማዎች በድብቅ ወደ ሰሜን ኮሪያ ይገባሉ

በሺዎች የሚቆጠሩ ዩአስቢ እና ማይክሮ ኤስዲ የተባሉ የመረጃ ቋቶች (ፍላሽ ዲስኮች) በድብቅ ወደ ደቡብ ኮሪያ ይገባሉ።

የደቡብ ኮሪያ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ድራማዎች እና የፖፕ ሙዚቃዎች እንዲሁም ዜናዎችን ይዘዋል። ዓላማቸው የሰሜን ኮሪያን ፕሮፖጋንዳ መገዳደር ነው።

ነገር ግን በአካባቢው የሚሠሩ ሰዎች ሰሜን ኮሪያ ይህን የመረጃ ጦርነት እያሸነፈች ነው ይላሉ።

ኪም የውጭ ሀገር ይዘት ያለባቸው ቋቶችን ይዘው የሚገኙ ዜጎች ላይ ከባድ እርምጃ እየወሰዱ ነው። ሌላኛው ስጋት ለዚህ ጦርነት የሚውል በጀት ጉዳይ ነው።

የዚህ ሥራ አብዛኛው ገንዘብ የሚገኘው ከአሜሪካ መንግሥት ነበር። ነገር ግን አሁን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው የምትሰጠውን እርዳታ መግታታቸው ሌላ ስጋት ፈጥሯል።

በድብቅ የሚገቡ ሙዚቃዎች እና ድራማዎች

ዩኒፊኬሽን ሚድያ ግሩፕ (ዩኤምጂ) የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ የደቡብ ኮሪያ ተቋም ነው ዜና እና አዝናኝ ፕሮግራሞችን እየጫነ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚልከው።

ድርጅቱ ዜናዎች እና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በጎራ በጎራ ያስቀምጣል። አስጊ የማይባሉ ዩኤስቢዎች ውስጥ የኮሪያ ድራማዎች፣ የፖፕ ሙዚቃዎች እና የኔትፍሊክስ ተከታታይ ድራማ ይጫናል።

በጣም አስጊ በሚባሉ ቋቶች ውስጥ ደግሞ “ትምህርታዊ ፕሮግራሞች” ማለትም ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት የሚሰብኩ ይዘቶች ይካተታሉ።

እነዚህ ዩኤስቢዎች በአሽከርካሪዎች ወደ ቻይና ድንበር ይላካሉ። የድርጅቱ ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ዩኤስቢዎቹን ወንዝ ያሻግራሉ።

የኮሪያ ድራማ ጉዳት ያለው ባይመስልም የደቡብ ሰው እንዴት በነፃነት እንደሚኖር ያሳያሉ። ግዙፍ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፈጣን መኪና ሲያሽከርክሩ እና ከትላልቅ የገበያ ማዕከላት ምግብ ሲሸምቱ ይታያሉ። ይህ በሰሜን ኮሪያ የሚታሰብ አይደለም።

ኪም የደቡቡ ሰው እጅግ ደሃ እና በጭቆና የሚኖር ነው ብለው ለሕዝባቸው ለሚነዙት ፕሮፖጋንዳ ይህ ትልቅ አደጋ ነው።

“አንዳንድ ሰዎች ድራማዎቹን ሲያዩ እንዳለቀሱ ይነግሩናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ሕልም እንዳላቸው እንዳወቁም ያስረዱናል” ይላሉ የዩኤምጂ ዳይሬክተር ሊ ክዋንግ-ባክ።

ምን ያክል ሰዎች የኮሪያ ድራማ እና ዜና እየኮመኮሙ እንደሆነ መረጃው ባይኖርም በቅርቡ የተሰሙ ምስክርነቶች መረጃዎቹ በሰፊው እየተሠራጩ እንደሆነ ያሳያሉ።

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም። አገዛዙን በግልፅ የሚቃወም ሰውም የለም። ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት የሚታሰብ አይደለም። ዳይሬክተሩ በመረጃዎቹ መሠራጨት ምክንያት ሰሜን ኮሪያዊያን ትግል ይጀምራሉ የሚል ተስፋ አላቸው።

የ24 ዓመቷ ካንግ ግዩሪ
የምስሉ መግለጫ,የ24 ዓመቷ ካንግ ግዩሪ አምልጣ ደቡብ ኮሪያ ገብታለች

ከሰሜን ኮሪያ ማምለጥ

የ24 ዓመቷ ካንግ ግዩሪ ሰሜን ኮሪያ ነው ያደገችው። በ2023 በታንኳ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከማምለጧ በፊት ዓሳ በማጥመድ ሥራ ነበር የምትተዳደረው።

ከውጭ የሚገቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መመልከቷ በከፊልም ቢሆን ሀገሯን ጥላ እንድትወጣ እንዳበረታት ትናገራለች።

“የሆነ ያፈነኝ ነገር ነበር። ድንገት ጥለሽ ጥፊ የሚል ስሜት ይሰማኝ ጀመር።”

ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሪያ ድራማ ያየችው በ10 ዓመቷ ነበር። እነዚህ ድራማዎች በድብቅ ወደ ሰሜን እንደሚገቡ ያወቀችው ከዓመታት በኋላ ነው። ዩኤስቢዎቹ በፍራፍሬ ሳጥኖች ውስጥ ተደብቀው ነው የሚገቡት።

“መጀመሪያ የማስበው ሕይወት ማለት እንዲህ እንደሆነ ነበር። ሌሎችም ሀገራትም እንዲህ [እንደ ሰሜን ኮሪያ] የሚኖሩ ይመስለኝ ነበር። ድራማዎቹን መመልከት ስጀምር ግን ሰሜን ኮሪያ ብቻ እንደሆነ ገባኝ።”

እሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ጓደኞቿ የኮሪያ ድራማ ይመለከታሉ። ድራማዎቹን የያዙ ዩኤስቢ ይዋዋሳሉ።

በድንበር አጥር አቅራቢያ በሳይክል የሚጓዙ ሰዎች

የቅጣት ዘመቻ

ይህ የመረጃ ጦርነት አገዛዙ ላይ የሚያመጣው አደጋ የገባቸው ኪም የራሳቸውን ጦርነት አውጀዋል።

በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከቻይና ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ የኤሌክትሪክ አጥር ገነቡ። የውጭ ሀገር ዜና እና ድራማ ይዘው የተገኙ ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት እንዲጣል ወሰኑ።

እነዚህን ይዘቶች የሚያሠራጩ ሰዎች እስር አሊያም የሞት ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል።

“በቀደመው ጊዜ ገበያዎች ውስጥ ሁሉ ይሸጥ ነበር። ማንም ሰው መግዛት ይችላል። አሁን ግን ከሚታመን ሰው ካልሆነ በቀር ማግኘት ከባድ ነው” ይላሉ ሊ።

ካንግ እንደምትለው ዩኤስቢ ይዘው የተገኙ ወጣቶች በሞት እንደተቀጡ ታውቃለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የደቡብ ኮሪያ ቋንቋ ቃላትን መጠቀም እና በደቡብ ኮሪያ ዘይቤ መናገር ጭምር ወንጀል መሆኑ ተሰምቷል።

በየትኛውም ሰዓት የአገዛዙ ጠባቂዎች ስልክ ነጥቀው ውስጥ ምን እንዳለ ማየት ይችላሉ ትላለች።

በ2024 ዴይሊ ኤንኪ የተባለው የደቡብ ኮሪያ ሚድያ ከደቡብ ኮሪያ በድብቅ ያስመጣው ስልክ እንደሚያሳየው የደቡብ ኮሪያ ቃላትን ስልኩ መጠቀም እንደማይቻል ነው።

ማታ ማታ ሰሜን ኮሪያ ይሰሙ የነበሩት ሬድዮ ፍሪ ኤዥያ እና የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ በትራምፕ ትዕዛዝ ምክንያት ተዘግተዋል።

የኪም አገዛዝ እየወሰደ ያለው እርምጃ እና ትራምፕ ገንዘብ ለመቆጠብ በሚል ያሳለፉት ውሳኔ ሰሜን ኮሪያ የመረጃ ጦርነቱ የበላይ እንድትሆን እንዳደረጋት ብዙዎች ይናገራሉ።

አንዳንዶች የገንዘብ እርዳታው ጫና አሜሪካ ላይ መውደቅ የለበትም ይላሉ። ደቡብ ኮሪያ ድጋፍ ማድረግ አለባት የሚል ሐሳብ ቢኖርም፤ የደቡብ ኮሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ይህ ከሰሜን ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል የሚጠቅም አይደለም ይላሉ።