
ከ 4 ሰአት በፊት
ኢራን በቢቢሲ ጋዜጠኞች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እያደረሰችው ያለውን የማስፈራሪያ ዘመቻዎች እያባባሰች ነው ሲል ተቋሙ ወቀሰ።
የሚዲያ ተቋሙ እነዚህ ዛቻዎች እየደረሱ ያሉት በኢራናውያን ጋዜጠኞች እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ላይ ነው ብሏል።
የብሪታንያው የዜና ወኪል እንዳለው የቢቢሲ የፐርዢያ አገልግሎት ጋዜጠኞች “በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው መከራ እየጨመረ መሆኑን” እያዩ ነው ብሏል።
የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች የዘፈቀደ ምርመራዎች፣ የጉዞ እገዳ፣ ፓስፖርቶቻቸው መነጠቅ እንዲሁም የንብረት መታገድ ማስፈራሪያዎች እየደረሱባቸው ነው ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት መቀመጫቸውን ያደረጉ የቢቢሲ ፐርዢያ ጋዜጠኞች ወደ ኢራን መመለስ አልቻሉም እንዲሁም ስራቸውን እንዲተው ለማስገደድ የተለያዩ ጥቃቶች እና ዛቻዎችን እየተሰነዘረባቸው ነው ብሏል።
“የኢራን ባለስልጣናት ይህንን የማስፈራራት ዘመቻዎችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን” ሲሉ የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ አትተዋል።
ኢራን ቢቢሲ ላቀረበባት ክስ ምላሽ አልሰጠችም።
የኢራን ባለስልጣናት በውጭ አገራት በሚገኙ ጋዜጠኞች ላይ ህገወጥ ዘመቻዎችን አካሂደዋል የሚሉ ክስ ከዚህ ቀደም ቀርቦባቸዋል።
ባለስልጣናቱ የቀረበባቸው ክሶች ውድቅ በማድረግ ቢቢሲን የአገሪቱን መንግሥት ከስልጣን ለማውረድ ለማበረታታት ሃሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ ነው ሲሉ ተችተውታል።
ቢቢሲ ኒውስ ፐርዢያ አገልግሎቱ በታገደበት ኢራን ውስጥ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን መድረስ ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 22 ሚሊዮን የሚጠጉ ታዳሚዎች አሉት ።
ቢቢሲ የኢራን ባለስልጣናት አገሪቱ ላይ ለባለፉት አስርት ዓመታት ዘገባ በሚሰሩ የፐርዢያ ቋንቋ ጋዜጠኞችን ኢላማ አድርጓል ሲል በአውሮፓውያኑ 2018 እና 2022 ቅሬታውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አቅርቦ ነበር።
ሆኖም በቅርብ ጊዜያት እነዚህ ማስፈራሪያዎች “በአስጊ ሁኔታ” እየተባባሱ መሆናቸውን ነው ቢቢሲ ያስታወቀው።
ተቋሙ ለተባበሩት መንግስታት አዲስ ቅሬታ እያዘጋጀሁ ነው ብሏል።
“የቢቢሲ ፐርዢያ አገልግሎት ጋዜጠኞች ከኢራን ድንበር ባሻገር በሚንቀሳቀሱ የኢራን መንግሥት ወኪሎች የግል ደህንነታቸው ስጋት ከመጋረጡ በተጨማሪ፤ በኢራን ውስጥ በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሱ መከራዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተመልክተዋል” ሲሉ የቢቢሲ ኃላፊ ገልጸዋል።
“እንዲህ አይነት ችግሮች በፕሬስ ነጻነት እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ቀጥተኛ ጥቃቶች ናቸው። በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል” ብለዋል።
ቢቢሲ አዲስ ቅሬታዎችን ለተባበሩት መንግሥታት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና ልዩ መልዕክተኞቹ ኢራን በበቢሲ ጋዜጠኞች ላይ ትንኮሳ፣ ክትትል እና የግድያ ዛቻዎችን ትፈጽማለች ያሉ ሲሆን እነዚህም የዓለም ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ናቸው ብለዋል።