
ከ 8 ሰአት በፊት
በጋዛ የእርዳታ ማከፋፈያ አቅራቢያ እርዳታ ሲጠባበቁ በነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ላይ የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ ከፍተው ግድያዎች ፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥሪ አቀረበ።
ራፋህ በሚገኘው በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን (ጂኤችኤፍ) ማዕከል እርዳታ ሲጠብቁ የነበሩ እማኞች እንደተተኮሰባቸው ተናግረዋል።
አለም አቀፉ ቀይ መስቀል 179 ተጎጂዎችን ሆስፒታሉ እንደተቀበለ ገልጾ ከነዚህም ውስጥ 21 ሰዎች መገደላቸውን አክሏል።
በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ የተገደሉ ፍልስጤማውያንን ቁጥር 31 አድርሶታል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ወታደሮቹ በእርዳታ ማከፋፈያው ማዕከል ወይም አቅራቢያ ላይ በሲቪሎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል መባሉን አስተባብሏል።
ጂኤችኤፍ በበኩሉ ሪፖርቶቹ “የፈጠራ ወሬዎች” ናቸው ሲል የከሰሰ ሲሆን በተቋሙ ወይም በአቅራቢያው ስለደረሰው ጥቃት እስካሁን ማስረጃውን አላየንም ብሏል።
እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ አለም አቀፍ ሚዲያዎችን ወደ ጋዛ ገብተው ሪፖርት እንዳያደርጉ ክልከላ መጣሏን ተከትሎ አንዳንድ መረጃዎችን ማጣራት አስቸጋሪ አድርጎታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጉቴሬዝ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ “በጋዛ ዕርዳታ ሲጠባበቁ የነበሩ ፍልስጤማውያን መገደላቸው እና መቁሰላቸው በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጦኛል” ብለዋል።
አክለውም “በእነዚህ ክስተቶች ላይ አስቸኳይ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ እና አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርባለሁ” ብለዋል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጉቴሬዝ አስተያየት “አሳፋሪ” በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ ዋና ጸሐፊው ሐማስን ባለመጥቀሳቸው ተችቷቸዋል።
ሰብዓዊ እርዳታ በአሁኑ ወቅት የሚከፋፈልበት መንገድ “ተቀባይነት” የሌለው እና “ሰብዓዊነትን የሚያወርድ ነው” ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ተርክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ይህ የሚያሳየው ለሲቪሎች ፍጹም ንቀትን ነው። ለሶስት ወራት ያህል ምግብ እና መድኃኒት ሳያገኙ የቆዩ ሰዎች በዚህ መንገድ እርዳታ ለማግኘት መሮጣቸው ወይም እንዲህ መፈተናቸውን ማሰብ ይቻል ይሆን?” ሲሉ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም “በጣም የተቸገሩ እነዚህን ሰዎች በከፍተኛ መንገድ ከሰብዓዊነት የማውረድ ተግባርን የሚያሳይ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
እስራኤል “በራፋህ በሚገኘው የአሜሪካ የዕርዳታ ማዕከል ሲጠባበቁ በነበሩ በሺዎች በሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ላይ ባነጣጠረችው ጥቃት” 31 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 176 መቁሰላቸውን የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።
አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ በራፋህ በሚገኘው ሆስፒታሉ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 179 ተጎጂዎች መምጣታቸውን ገልጿል።
አብዛኞቹ የተተኮሰባቸው ሲሆን 21ዱም በስፍራው እንደደረሱ መሞታቸውን ገልጿል።
ተቋሙ አክሎም “ሁሉም ተጎጂዎች እርዳታ ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው” ብሏል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በኻን ዩኒስ በሚገኘው የናስር ሆስፒታል በርካታ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው አንዳንዶቹም በአስጊ ሁኔታ ላይ ያሉ ፍልስጤማውያንን ማከማቸውን ገልጿል።
ተጎጂዎቹ ” የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች)፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ጀልባዎች፣ ታንኮች እና ወታደሮች ከሁሉም አቅጣጫ እንደተኮሱባቸው” ሪፖርት ማድረጋቸውን እና የተቋሙ ሰራተኛ ወንድም ዕርዳታ ሊቀበል ሲሞክር መገደሉን ኤምኤስኤፍ ተናግሯል።
በራፋህ የሚገኝ አንድ ጋዜጠኛ በበኩሉ የእስራኤል ታንኮች ተኩስ ሲከፍቱ በርካታ ፍልስጤማውያን በእርዳታ ማዕከሉ አቅራቢያ ተሰባስበው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።