ቢል ጌትስ

ከ 7 ሰአት በፊት

የማይክሮሶፍት መስራች ቢልጌትስ፤ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ካለው ሀብት ውስጥ አብዛኛውን በአፍሪካ የጤና እና ትምህርት አገልግሎቶችን ለማሻሻል እንደሚያውል ተናገረ።

የ69 ዓመቱ ባለጸጋ፤ “በጤና እና ትምህርት የሰው ልጅን በማውጣት፤ አፍሪካ ውስጥ እያንዳንዱ ሀገር በብልጽግና ጎዳና ላይ መሆን አለበት” ብሏል።

ቢል ጌትስ፤ ባለፈው ሳምንት እሁድ ግንቦት 24/2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በብሔራዊ ቤተመንግሥት በተካሄደ ሥነሥርዓት የሀገሪቱን ታላቅ የክብር ኒሻን ሽልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተሸልሟል።

ዐቢይ፤ ይህንን ሽልማት ለጌትስ ያበረከቱት በባለሀብቱ የመሰረተው ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ “ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተፅዕኖዎችን” እውቅና ለመስጠት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ቢል ጌትስ በአዲስ አበባ ከተማ ባደረገው ንግግር አፍሪካውያን ወጣት ፈጣሪዎች ሰው ሰራሽ አስተውህሎትን (AI) በምን አይነት መንገድ በመጠቀም በአህጉራቸው የጤና አገልግሎትን ማሻሻል እንደሚችሉ እንዲያስቡ አሳስቧል።

ቤልጌትስ ከ20 ዓመት በኋላ 200 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ከሚጠበቀው ሀብቱ ውስጥ 99 በመቶውን ለመስጠት ማቀዱን ያስታወቀው ባለፈው ወር ነበር። የባለሀብቱ ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በ2045 ስራውን ያጠናቅቃል።

በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ “በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ውስጥ ያለኝን ሀብት እንደሚከፋፈል በቅርቡ ቃል ገብቻለሁ። አብዛኛው ገንዘብ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን እንድትፈቱ ለማገዝ ይውላል” በማለት ተናግሯል።

የሞዛምቢክ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ግራሳ ማሼል “በችግር ጊዜ” የመጣ ሲሉ የቤልጌትስን እቅድ አሞካሽተውታል።

“ሚስተር ጌትስ በለውጥ ጎዳና ላይ ከእኛ ጋር ለመጓዝ ባላቸው ጽኑ ቁርጠኝነት ላይ እንተማመናለን” ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት፤ ለኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚዎች ህክምና የተቀረጹ ፕሮግራሞችን ለአፍሪካ የሚሰጠውን እርዳታ አቋርቷል።

በፕሬዝዳንት ትራምፕ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” ፖሊሲ ምክንያት የመጣው ይህ ለውጥ የአህጉሪቱን የጤና አገልግሎት እጣ ፋንታ ላይ ስጋት ደቅኗል።

ቢል ጌትስ፤ በአፍሪካ ውስጥ ስራዎችን በማከናወን ረጅም ታሪክ ያለው ፋውንዴሽኑ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን ማሻሻል ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጿል።

“የተማርነው፤ እናት ከመጸነሷ አስቀድሞ ጤናማ እና የተመጣጠነ ምግብ የምታገኝ እንድትሆን ማድረግ ባረገዘች ጊዜ ጠንካራ ፍሬን እንድታገኝ እንደሚያደርግ ነው” ብሏል።

ቢል ጌትስ

“ህጻን ልጅ በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ጥሩ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘቱን ማረጋገጥም ውጤት ያመጣል” ሲል ተናግሯል።

ቢሊዮነሩ ለወጣት ፈጣሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት ሞባይል ስልኮች በአፍሪካ የባንክ አገልግሎት ላይ አብዮት ማምጣታቸውን ጠቅሶ፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትም ለአህጉሪቱ ጥቅም መዋል እንዳለበት ሞግቷል።

“አፍሪካ ባህላዊውን የባንክ አገልግሎት በአብዛኛው ዘልላለች፤ አሁን የቀጣዩን ትውልድ የጤና አገልግሎት ስርዓት ስትገነቡ ሰው ሰራሽ አስተውህሎት እንዴት እዚያ ውስጥ እንደሚካተት አስቡ” ብሏል።

ሩዋንዳን በማሳያነት የጠቀሰው ጌትስ፤ ሀገሪቱ ከፍተኛ አደጋ ያላቸው እርግዝናዎችን ለመለየት በሰው ሰራሽ አስተውህሎት የታገዘ አልትራ ሳውንድ በመጠቀም አገልግሎቶቿን ማሻሻሏን አንስቷል።

ጌትስ ፋውንዴሽን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሶስት ጉዳዮች መካከል አንዱ መከላከል የሚቻልን የእናቶች እና ህጻናት ሞት እንዲያበቃ ማድረግ ነው። ቀጣዩ ትውልድ በገዳይ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይሰቃይ ማድረግ እና ሚሊዮኖችን ከድህነት ማውጣትም ፋውንዴሽኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

“በ20 ዓመቱ ማጠናቀቂያ ላይ የፋውንዴሽኑ ስራ ላይ ፀሀይ ትጠልቃለች” በማለት ስለ ፋውንዴሽኑ ወደፈት ተናግሯል።

ጌትስ ባለፈው ወር በፋውንዴሽኑ አማካኝነት ልገሳውን እንደሚያሳልጥ ገልጾ ነበር።

“ስሞት ሰዎች ስለ እኔ ብዙ ነገሮችን ይናገራሉ፤ ነገር ግን ‘ሀብታም ሆኖ ሞተ’ የሚለው አንዱ አይሆንም” ሲል ፅፎ ነበር።

እንደ ብሎምበርግ መረጃ ከሆነ ቢል ጌትስ 99 በመቶ የሚሆነውን ሀብቱን ከሰጠም በኋላ የዓለም አምስተኛው ሀብታም ሰው ይሆናል።

ጌትስ ከፖል አለን ጋር በመሆን ማይክሮሶፍትን የመሰረተው እ.አ.አ በ1975 ሲሆን ኩባንያው በአጭር ጊዜ በሶፍትዌር እና በሌሎች የቴክ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ተጽእኖ ፈጣሪ ሆኗል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ራሱን ከኩባንያው እያራቀ የመጣው ጌትስ፤ እ.አ.አ በ2000 ከዋና ስራ አስፈጻሚነት፤ እ.አ.አ በ2014 ደግሞ ከሊቀመንበርነት ራሱን አግልሏል።

ገንዘቡን ለመስጠት የተነሳሳው ባለሀብቱ ዋረን ባፌት እና ሌሎች በጎ አድራጊዎች እንደሆነ ገልጿል።

ይሁን እንጂ የፋውንዴሽኑ ተቺዎች ጌትስ የበጎ አድራጎት ስራውን ከታክስ ለማምለጥ ይጠቀምበታል እንዲሁም በዓለም የጤና ስርዓት ላይ ያልተገባ ተጽእኖ አሳድሯል በማለት ይወቅሱታል።