አቶ ታዬ ደንደአ
የምስሉ መግለጫ,አቶ ታዬ ደንደአ

ከ 5 ሰአት በፊት

ትናንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ ታዬ ደንደአ የተያዙት ‘ሊሸሹ ሲሉ ነው’ መባሉን ባለቤታቸው ተናገሩ።

ከመያዛቸው በፊት የቀረቡበት ችሎት ቀደም ሲል ቀርበውባቸው ውድቅ የተደረጉትን ክሶች እንዲከላከሉ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ መደረጉን ባለቤታቸው ተናግረዋል።

የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰኞ ግንቦት 24/2017 ዓ.ም. አቶ ታዬ ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊሶች ተይዘው የተወሰዱ ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግን የተያዙት “ሲሸሹ” ነው ተብሎ እንደቀረበ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

አቶ ታዬ ሰኞ ግንቦት 25/2017 ዓ.ም. ከሰዓት 10 ሰዓት በኋላ ለጥያቄ እንደሚፈለጉ በመግለጽ ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ተናግረው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ላይ አቋርጧቸውን የነበሩትን ሁለት ክሶች የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን ተከትሎ ዳግም አንቀሳቅሷል።

ወ/ሮ ስንታየሁ ትናንት አቶ ታዬን ለመያዝ ቤታቸው የመጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እንደሚወሰዱ እንደነገሯቸው እና ዛሬ [ማክሰኞ] ጠዋትም ወደ ስፍራው ማምራታቸውን አስረድተዋል።

ነገር ግን ጠዋት ምርመራ ላይ ናቸው ተብለው ከሰዓት ስምንት ሰዓት ላይ ተመልሰው መሄዳቸውን ገልጸዋል።

“ጥያቄ ላይ ስለሆኑ ማግኘት አትችሉም” ተብለው እስኪጨርሱ መጠበቃቸውን እና በዚያ መካከል “መጥተዋል” ተብለው ለአጭር ደቂቃ እንዳገኟቸው ባለቤታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ጠዋት ላይ እኛን ቢሮ ነው ብለው መረጃ ሰጥተውን . . . ነገረ ግን ከእርሱ አንደበት እንደሰማሁት ቢሮ ሳይሆን ችሎት ነው የቀረብኩት ብሎኛል።”

አቶ ታዬ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ቤተሰብ እንዲሁም ጠበቃቸው አለመገኘታቸውን የተናገሩት ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ፣ “ከቤቱ ብሎም ከመኝታ ቤቱ ተወስዶ ችሎት ላይ ሲቀርብ ግን ‘ስትሸሽ ነው ያገኘንህ’ መባሉን ነገረኝ” ብለዋል።

ወ/ሮ ስንታየሁ አክለውም ወደ ቂሊንጦ ወርዶ ጉዳዩን እንዲከታተሉ መወሰኑንም ከአቶ ታዬ ደንደአ መስማታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ ችሎት ለመገኘት ጥረት ማድረጋቸውን የተናገሩት የአቶ ታዬ ጠበቃ አቶ አበራ ንጉሥ በበኩላቸው፣ በትናንትናው ዕለት ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሲያውላቸው እና ቤታቸውን ሲበረብር “በሌላ ወንጀል የተያዙ እንጂ ይኼኛው መዝገብ አልመሰለንም ነበር” ብለዋል።

ለዚህም የሕግ አሠራር ያሉትን ሲጠቅሱም፣ አቶ ታዬ በተመሳሳይ ክስ ፍርድ ቤት የወሰነውን ተከትሎ ችሎት እንዲቀርቡ የሚፈለግ ከሆነ የዋስትና መብታቸው በተጠበቀበት ሁኔታ ውስጥ ስላሉ “ታስረው እንዲቀርቡ ሳይሆን በመጥሪያ እንዲቀርቡ ነበር የሚደረገው” ብለዋል።

አቶ ታዬ ትናንት ሰኞ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው በኋላ ማታ ሁለት ሰዓት ላይ ቤታቸውን ብርበራ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

“ይህ የሚያሳየው አዲስ በወንጀል የጠረጠራቸው አቀራረብ ሆኖ ስለቀረበ ነው” ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ቤተሰብ በፌደራል ፖሊስ ቢሮ ቢገኝም ምረምራ እየተደረገባቸው መሆኑ ከተገለጸላቸው በኋላ ስድስት ሰዓት ላይ ማንም ሊገኝ በማይችልበት ሁኔታ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ወቅትም ቢሆን “በተከላካይ ጠበቃ በኩል ተወክልው እንዲከራከሩ ዕድል አልተሰጠም” ያሉት ጠበቃው “የተሄደበት መንገድ እርሳቸውን ለማሰር ካለ ፖለቲካዊ ውሳኔ የማስፈፀም ድርጊት አድርገን ነው የተረዳነው” ብለዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ፖሊስ በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት አቶ ታዬ ደንደአን ማቅረቡን ዘግበዋል።

ዐቃቤ ሕግም ከዚህ ቀደም የተዘጉ ሁለት ክሶችን ጨምሮ መዝገቡ በፍርድ ቤቱ እንዲቀሳቀስ የጠየቀ ሲሆን አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው፣ ለፍርድ ቤቱ ትናንት የተያዝኩበት መንገድ ልክ አይደለም፣ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎቼ ተይዘዋል፤ ከጠበቃዬ ጋር ተማክሬ መቅረብ ነበረብኝ በማለት መከራከራቸውን ጠቅሰዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎትም የሁለቱንም ክርክር ካደመጠ በኋላ የተከሳሹ የዋስትና መብት እንዲነሳ መወሰኑ ተጠቅሷል።

አቶ ታዬ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን፣ የመከላከያ ምስክርን ለመስማት ለሰኔ 30 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል ተብሏል።

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ፣ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ባለፈው ኅዳር ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል።

አቶ ታዬ ቀደም ሲል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት፣ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በሁለቱ ማለትም ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት እና ለፀረ ሰላም ኃይሎች ድጋፍ ማድረግ ክሶች በነጻ ተሰናብተው ነበር።

ነገር ግን የአቶ ታዬን ጉዳይ የተመለከተው ችሎት በድጋሚ ከመታሰራቸው ከሰዓታት ቀደም ብሎ ክሶቹ እንዲቀጥሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መወሰኑን ጠበቃቸው አቶ አበራ ንጉሥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ደንደአ በቀረቡባቸው ክሶች ምክንያት ለወራት በእስር ከቆዩ በኋላ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ኅዳር 23/2017 ዓ. ም. በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወስኖ ነበር።

ባለፈው ዓመት ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ ለእስር የተዳረጉት አቶ ታዬ፣ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሣሪያ ሕግን በመተላለፍ ወንጀሎች ተከሰው ነበር።

የጦር መሣሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ አቶ ታዬ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ አምስት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለምስክርነት ጠርተው ነበር።

አቶ ታዬ በምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኝ ካሏቸው መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል።

ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ተደራራቢ ክሶችን የመሠረተው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2016 ዓ. ም. ነበር።

አቶ ታዬ በአገሪቱ ስላለው የሰላም ሁኔታ እና በመንግሥት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆን፣ ከሥልጣን የተሰናበቱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ ሁለት መስመር ደብዳቤ መሆኑ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እና ክስ በሰነዘሩበት ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው ነው በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ የወጡት።