
ከ 7 ሰአት በፊት
ወደ ሰሜን ዳርፉር እርዳታ ጭነው ይጓዙ የነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መኪኖች ጥቃት ደረሰባቸው።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በማለት ባወጡት የክስተቱ መግለጫ ላይ “በርካቶች መጎዳታቸውን” ገልጸዋል።
የሱዳን መንግሥት “የጥበቃ ሠራተኞች፣ አሽከርካሪዎች እና ሰላማዊ ዜጎች” በጥቃቱ መገደላቸውን ገልጾ፣ ግድያውን የፈጸሙት ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጉ የሚገኙት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ናቸው ሲል ወንጅሏል።
ይሁን እንጂ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥቃቱን ያደረሰው የሱዳን ጦር ነው ሲሉ በአጸፋው ከስሷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኞ ዕለት ማታ ኤል ኮማ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ጥቃቱን ማን እንደፈጸመ ያለው ነገር ባይኖርም፣ መኪኖቹ ረሃብ እየታየባት ነው ወደ ተባለችው ኤል ፋሸር ከተማ ለመንቀሳቀስ እየተጠባበቁ ባለበት ወቅት መፈጸሙን አስረድቷል።
ኤል ፋሸር በሰሜናዊ ዳርፉር በሱዳን ጦር ቁጥጥር ስር የምትገኝ የመጨረሻዋ ከተማ ነች።
የሱዳን ንፁኃን ዜጎች እና ወታደሮች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ከአንድ ዓመት በላይ ጥቃት ሲፈጸምባቸው ነበር።
ሰኞ ማታ በተፈጸመው ጥቃት ወደ ኤል ፋሸር ይጓዙ የነበሩ የተባበሩት መንግሥታት መኪኖች ላይ የነበሩ አራት አባላት ሲገደሉ ሁለት ደግሞ መቁሰላቸውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቃል አቀባይ ባሻ ታቢቅ በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
የኤል ኮማ አስቸኳይ ጊዜ በጎ ፈቃድ ሠራተኞች በፌስቡክ ላይ ባጋሩት ተንቀሳቃሽ ምሥል እርዳታ የጫነ መኪና ሲቃጠል የሚታይ ሲሆን፣ ለጥቃቱ “የሱዳን ጦር ድሮኖችን” ተጠያቂ አድርገዋል።
ኤል ኮማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ስትሆን ከዚህ ቀደም ከሱዳን ጦር ጋር በነበረው ውጊያ በተደጋጋሚ ዒላማ ነበረች።
በከተማዋ ላይ በደረሰ ተደጋጋሚ ጥቃትም ንፁኃን ሲገደሉ የመሠረተ ልማቶች ወድመዋል።
በኤል ኮማ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ በጎ ፈቃደኞች እሁድ ዕለት የሱዳን ጦር ሠራዊት በአውሮፕላን የተደገፈ ጥቃት ፈጽሞ 89 ሰዎች መገደላቸውን ወይንም መጎዳታቸውን ገልጸዋል።
የሱዳን ጦር በቀረበበት ውንጀላ ላይ ምላሽ አልሰጠም።
እንደ ሱዳን ትሪቢውን ዘገባ ከሆነ ጥቃቱ የደረሰው በኤል ኮማ በሚገኝ በርካታ ሰዎች በሚገበያዩበት ስፍራ ነው።
በሱዳን የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ በዓለም ላይ አስከፊ የተባለውን የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።
ማክሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ቃል አቀባይ ዩጂን ቢዩን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።
ጦርነቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ባለ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት የተቀሰቀሰ ነው።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል አለመግባባት ከመፈጠሩ በፊት በጋራ በመሆን የሱዳን የሽግግር መንግሥትን ከሥልጣን አውርደው ነበር።