
ከ 4 ሰአት በፊት
የካናዳ መንግሥት የጥገኝነት ጠያቂዎችን ቁጥር ለመቀነስ ያለመ እና ለባለስልጣናቱ የበለጠ ስልጣን የሚሰጥ ረቂቅ ሕግ አቀረበ።
የካናዳ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ሊና ዲያብ ጠንካራ የድንበር ቁጥጥር የአገሪቱን የኢሚግሬሽን ስርዓት በማሳደግ፤ የተደራጀ ወንጀልን እና በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡ አደንዛዥ እፆችን እነ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነው ብለዋል።
ሕጉ ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የምትጋራውን ድንበር ለመቆጣጠር ለፖሊስ ተጨማሪ ስልጣን የሚሰጥ ደንብንም ያካተተ ነው።
በተጨማሪም የጥገኝነት ጥያቄ አመልካቾች ከአንድ ዓመት በላይ በካናዳ እንዳይቆዩ የሚከለክል ነው።
የቀረበው ሕግ በስደተኛ ተቀባይነቷ በምትታወቀው ካናዳ ላይ ጫናዎች መበርታታቸውን ተከትሎ የመጣ ሲሆን፤ አገሪቱ ለገባችበት የመንግሥት አገልግሎት እና የቤት ቀውስ መፍትሄ ለማበጀት ስደተኞችን መገደብ አልሟል።
የቀድሞው የጀስቲን ቱሩዶ መንግሥት የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት እድገት ለማነቃቃት ስደተኞች በመቀበል የሚታወቅ ሲሆን፤ በአገሪቱ በጊዜያዊነት ለስራ እና ትምህርት የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተመሳሳይ ወቅትም ካናዳ የጥገኛ ጠያቂዎች ቁጥር ያሻቀበ ሲሆን፤ አመልካቾች ጉዳያቸው እስኪታይላቸው እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ለመጠበቅ ግድ ብሏቸው ነበር።
የሚያዚያውን የፌደራል ምርጫ ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ያልተረጋጋውን የካናዳን ኢሚግሬሽን ለመፍታት ቃል ገብተዋል።
በነባሩ ሕግ ስደተኞች ወደ ካናዳ ወዲያው እንደገቡ እንደ አየር ማረፊያ ባሉ መግቢያዎች አሊያም ካናዳ ከገቡ በኋላ ጥገኝነት መጠየቅ ይችላሉ።
ስደተኞች ጥገኝነት ከመጠየቃቸው በፊት ካናዳ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ መቆየት እንዳለባቸውም ገደብ አልነበረም።
አዲሱ ሕግ ግን ከአንድ ዓመት በላይ በካናዳ የቆዩ ስደተኞችን የጥገኛ ጥያቄ የማይቀበል ሲሆን፤ ወደ አገራቸው እንዲመለሱም የሚያደርግ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ ሕግ በሦስተኛ አገር ስምምነት እንደ አሜሪካ ካሉ አገራት ወደ ካናዳ የሚገቡ ስደተኞች ጥገኝነት ጥያቄያቸውን በ14 ቀናት ማቅረብ አለባቸው ይላል።
አዲሱ ሕግ የአዲስ አመልካቾች ጉዳይ “ለኅብረተሰብ ጤና እና ብሔራዊ ደኅንነት” ሲባል የመሰረዝ ስልጣን ለመንግሥት የሰጠ ነው።
127 ገፆችን የያዘው ሕግ ለወንጀል ምርመራ ሲባል የደብዳቤ ልውውጦችን አስቀድሞ የመክፈት ስልጣን መስጠቱ ታውቋል።
ይሁን እንጂ ተቺዎች ረቂቅ ሕጉ የሲቪል መብቶችን ይጥሳል እያሉ ነው።
በተጨማሪም ሕጉ የገንዘብ ዝውውር ላይ ገደብ የጣለ ሲሆን አንድ ግለሰብ ከ10 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ እንዳያዘዋወር ይከለክላል።