
ከ 7 ሰአት በፊት
ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ ሰፊ እና የዓመት ከስድስት ወራት ዝግጅት በጠየቀ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ ትንሿ ዩክሬን ወደ ግዙፏ ሩሲያ በሺህ ኪሎ ሜትሮች ዘልቃ በመግባት የፈጸመችው ጥቃት ነው።
ግንቦት 24/2017 ዓ.ም. እሁድ ከ100 የሚበልጡ የዩክሬን ድሮኖች ሩሲያ ግዛት ውስጥ በመግባት የኒውክሌር ቦምቦችን የሚሸከሙ ወሳኝ የጦር ጄቶች የሚገኙባቸውን የአየር ኃይል ሰፈሮችን ደበደቡ።
ስፓይደር ዌብ (የሸረሪት ድር) ተብሎ የተሰየመው ይህ የዩክሬን የጥቃት ዘመቻ ገና ከመጀመሩ በተለያዩ የሩሲያ ግዛቶች ውስጥ በተመሳሳይ ሰዓት ፍንዳታዎች ተሰሙ።
ከዩክሬን 8,000 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሰሜን እስከ መርማንስክ፣ በምሥራቅ ደግሞ እስከ አሙር ክልል በሩሲያ ግዛቶች ውስጥ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ በአምስት የሩሲያ ክልሎች ማለትም መርማንስክ፣ ኢርኩትስክ፣ ኢቫኖቮ፣ ራያዛን እና አሙር መፈጸሙን አረጋግጦ፣ የጦር አውሮፕላኖች የተጎዱት ግን በመርማንስክ እና ኢርኩትስክ ብቻ ነው ብሏል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በተለቀቁት ፎቶዎች ላይ የዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ቫሲሊ ማሊውክ በሩሲያ ውስጥ የሚገኙትን የአየር ኃይል ጦር ሠፈሮችን በሳተላይት ካርታ ሲመለከቱ ይታያል።

የአየር ኃይሉ ላይ ጥቃት ያደረሰው ዘመቻ
ማሊውክ እንዳሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ በድብቅ ወደ ሩሲያ የገቡት ከእንጨት በተሠሩ ሳጥኖች ውስጥ ተደርገው በጭነት መኪናዎች አማካይነት ነው።
የጭነት መኪኖቹ ጣሪያ ደግሞ በርቀት መቆጣጣሪያ የሚከፈቱ ናቸው።
የጭነት መኪኖቹን የሚያሽከረክሩት ግለሰቦች ስለጫኑት ነገር ምንም እውቀቱ አልነበራቸውም።
የተሰጣቸው ኃላፊነት በአየር ኃይል ሰፈሮቹ አቅራቢያ ወደሚገኙ ቦታዎች እንዲያደርሱ ብቻ ነው።
ከዚያም ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ በርቀት መቆጣጠሪያ እየተመሩ ዒላማቸውን ደብድበዋል።
በበይነ መረብ ላይ የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደሚያሳዩት ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ተደብቀው ከተጫበት ከባድ መኪና ጣሪያ ላይ በአንድ ላይ ሲወጡ ይታያል።
የሩሲያ መንግሥት ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ሪያ ያነጋገረው ኖቮስቲ የተባለ አሽከርካሪ፣ እሱ እና ሌሎች አሽከርካሪዎች ከጭነት መኪና ላይ እየወጡ የሚበሩ ድሮኖችን ሲመለከቱ በድንጋይ መትተው ለመጣል መሞከራቸውን ተናግሯል።
“በጭነት መኪናው ላይ ነበር የተጫኑት፤ ድሮኖቹ ወደ ላይ እንዳይበሩ እና እንዲወድቁ ለማድረግ ድንጋይ ወረወርንባቸው።”

ከሩሲያ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚታወቀው ‘ባዛ’ የተሰኘ የቴሌግራም ቻናል ባወጣው ያልተረጋገጠ ዘገባ መሠረት ድሮኖቹን ጭነው ያጓጓዙ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ሁሉም የተነገራቸው ተመሳሳይ ታሪክ ነበር።
አሽከርካሪዎቹ በሩሲያ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ነጋዴዎች ያዘዙትን የእንጨት ሳጥኖችን እንዲያደርሱ እንደተነገራቸው ተገልጿል።
ከአሽከርካሪዎቹ አንዳንዶቹ ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ተጨማሪ መመሪያ በስልክ እንደተቀበሉ ተናግረዋል።
የደረሳቸው ትዕዛዝ መኪናቸውን የት ማቆም እንዳለባቸው የሚገልጽ ሲሆን፣ ይህን ሲያደርጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከውስጣቸው እየወጡ ሲበሩ በማየታቸው ደንግጠዋል።
ዘመቻውን በቀጥታ የሚቆጣጠሩት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እሁድ ምሽት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ባጋሩት የድል ዜና “አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከዘጠኝ ቀን” በፈጀው ዝግጅት በጥቃቱ ላይ 117 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ዒላማ ከተደረጉት ቦታዎች አንዱ ከሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት ቢሮዎች አጠገብ የሚገኘው ነው።
ሩሲያ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ብትገልጽም፣ ዜሌንስኪ ግን ጥቃቱን በማቀላጠፍ የረዱ በሙሉ “ከሩሲያ ግዛት ወጥተዋል…አሁን ደኅንነታቸው በሚጠበቅበት ስፍራ ላይ ናቸው” ብለዋል።
አሁን በተሰረዘ የቴሌግራም ልጥፍ ላይ በኢርኩትስክ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የኡስት-ኩት ከተማ ባለሥልጣናት በቤላያ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ ከደረሰው የድሮን ጥቃት ጋር በተያያዘ አንድ የ37 ዓመት ዩክሬናዊን እየፈለጉ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ሰው አልባ አውሮፕላኖች
በዩክሬን የደኅንነት ተቋም የተጋሩ ምሥሎች በደርዘን የሚቆጠሩ ትናንሽ ጥቁር ሰው አልባ አውሮፕላኖች በመኪና ላይ ተጭነው በሚገኙ የእንጨት ሳጥኖች ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተቀምጠው ያሳያሉ።
ይህም የሩሲያ ወታደራዊ ጉዳዮች ጦማሪዎች በቼልያቢንስክ የሚገኝ ቦታ መሆኑን አመልክተዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሰው አልባ አውሮፕላኖች ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ስቲቭ ራይት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሩሲያን ወሳኝ የጦር አውሮፕላኖች ለመምታት ጥቅም ላይ የዋሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአንጻራዊ ሁኔታ ከባድ ጭነት የሚሸከሙ አራት ሽክርክሪቶች ያሏቸው ኳድኮፕተሮች ናቸው።
ይህንን ጥቃት “በጣም ያልተለመደ” ያደረገው ወደ ሩሲያ ግዛት አስርጎ ማስገባት እና ከዚያም በርቀት ማስወንጨፍ እና ማዘዝ መቻሉ ነው።
ይህም ሊሳካ የቻለው በሳተላይት ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ነው ሲሉ ደምድመዋል።
ዜሌንስኪ እንደተናገሩት 117ቱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እያንዳንዳቸውን ከርቀት የሚቆጣጠሩ የራሳቸው አብራሪዎች ነበሯቸው።
ዶ/ር ራይት በተጨማሪም ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ አቅጣጫ ጠቋሚ (ጂፒኤስ) በመጠቀም መብረር ይችሉ እንደነበር፤ ነገር ግን ድሮኖችን በርቀት መቆጣጣሪያ ማብረር የሩሲያ ሳተላይቶችን ለማለፍ ፈታኝ ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኪየቭ ሩሲያን ባስደነገጠው እና ዓለምን ባስደነቀው ጥቃት ውስጥ የተሳተፉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከየት እንደመጡ ዝርዝሮችን አላጋራችም።
ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዩክሬን ድሮኖችን በማምረት ረገድ እጅግ በጣም ውጤታማ ሆናለች። ስለዚህም በዚህ ዘመቻ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉት በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ናቸው።

ዒላማዎቹ
ዜሌንስኪ በእሁድ ምሽቱ የቪዲዮ መግለጫቸው ላይ “ሩሲያ ተጨባጭ ኪሳራዎች አጋጥሟታል” ብለዋል።
እንደ ዩክሬን ገለጻ የሩሲያ ወሳኝ የጦር አውሮፕላኖች ከሆኑት መካከል 41 ስትራቴጂካዊ ቦምቦ ጣይ ጄቶች የተመቱ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም “ቢያንስ” 13ቱ ወድመዋል።
ሞስኮ አንዳንድ አውሮፕላኖች ተጎድተዋል ከማለት ባለፈ ስለደረሰው ጉዳትም ሆነ ስለ ወደሙት አውሮፕላኖች ምንም ያለችው ነገር የለም።
በቢቢሲ የተረጋገጡ ቪዲዮዎች በመርማንስክ በሚገኘው ኦሌኔጎርስክ አየር ማረፊያ እና በኢርኩትስክ የሚገኘው የቤላያ አየር ማረፊያ ላይ የወደሙ አውሮፕላኖች ይታያሉ።
በጥቃቱ ዒላማ የተደረጉት ስትራቴጂክ ሚሳዔል ተሸካሚ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከሌሎቹ መካከል ቲዩ-95፣ ቲዩ-22 እና ቲዩ-160 የሚባሉት ናቸው።
በጥቃቱ የወደሙትን የሩሲያን አውሮፕላኖች መጠገን አስቸጋሪ ይሆናል፤ አንዳቸውም በምርት ላይ ስላልሆኑ መተካትም የማይታሰብ ነው።
በኬፕላ ስፔስ የተጋራው የሳተላይት ምሥል ቢያንስ አራት የሩሲያ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ቤላያ አየር ማረፊያ ላይ ክፉኛ ተጎድተው ወይም ወድመው ይታያሉ።
ይህ ሩሲያ ካጋራቸው እና በቲዩ-95 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ላይ ጥቃት እንደደረሰ ከሚያሳየው የዩክሬን ምሥል ጋር ይዛመዳል።
የዩክሬን ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ቫሲል ማልዩክ እንዳሉት “በጦርነት ሕጎች እና ልማዶች መሠረት ፍፁም ሕጋዊ ዒላማዎችን ለይተናል፤ ወታደራዊ አየር ማረፊያዎች እና አውሮፕላኖች ሰላማዊ ከተሞቻችን ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ።”
ቲዩ-95 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ባለፈው ሳምንት በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ የኬኤች-101 ሚሳኤል ጥቃት ፈጽመዋል ተብሏል።
እያንዳንዱ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ስምንት ክሩዝ ሚሳኤሎችን የሚይዝ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ሚሳዔል ደግሞ 400 ኪሎ ግራም አረር ይሸከማል።
ኤ-50 ወታደራዊ የስለላ አውሮፕላኖችም ዒላማ ከተደረጉት መካከል ናቸው ተብሏል።
ሩሲያ የዩክሬን ሚሳዔሎችን የማክሸፍ እና የራሷን ጥቃት የማድረስ አቅምን የሚያሳድጉ ውድ አውሮፕላኖች ናቸው።
ሩሲያ ምን ያህል ኤ-50ዎች እንዳሏት አይታወቅም።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 2024 የሩሲያ ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ ስምንት ኤ-50 አውሮፕላኖች እንዳላቸው ተናግረው ነበር።
ስለዚህ ማንኛውም ኪሳራ ወይም ጉዳት ለሞስኮ ከባድ ሊሆን ይችላል ።
የዩክሬን የደኅንነት ተቋም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፈው በዚህ የስፓይደር ዌብ (የሸረሪት ድር) ዘመቻ ሩሲያ 7 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት እንደወደማባት ገልጿል።
የሩሲያ መንግሥት ሚዲያ በጥቃቱ ላይ ድምጻቸው አልተሰማም።
እሁድ ምሽት የሩሲያ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የክልል ባለሥልጣናት መግለጫዎችን ሲያነቡ የነበረ ሲሆን፣ ሰኞ ማለዳ ላይ አጠቃላይ ዜናው እንዳይቀርብ ተደርጓል።
ከዩክሬናውያን ባሻገር አንድ ግለሰብ በበይነ መረብ ላይ ዘመቻውን “ግዙፍ” በማለት አወድሶታል።
ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ “በእርግጥ፣ ሁሉም ነገር አሁን ሊነገር አይችልም፤ ነገር ግን እነዚህ የዩክሬናዊያን ገድሎች በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ እንደሚካተቱ ጥርጥር የለውም” ብለዋል።
