የሚቺጋን ከተማ

ከ 5 ሰአት በፊት

ሁለት የቻይና ዜጎች የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ‘አደገኛ የስነ ሕይወት ተህዋሲያን’ ያሉትን ፈንገስ ወደ አሜሪካ በማስገባት ክስ ተመሰረተባቸው።

ያንኩንግ ጂያን እና ዙያንግ ሊዊ የተባሉ ሴት እና ወንድ ቻይናዊያን በማሴር፣ ሕገ ወጥ እቃዎችን በማስገባት፣ ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብ እንዲሁም ቪዛ በማጭበርበር መክሰሱን የሚቺገን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ አስታውቋል።

የ34 ዓመቱ ዙያንግ ሊዊ ፈንገሱን በዲትሮይት አየር ማረፊያ በማስገባት የ33 ዓመት ፍቅረኛው በምትሰራበት በሚችገን ዩኒቨርስቲ ቤተ ሙከራ ለማጥናት ሙከራ ማድረጉን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል።

‘ፉሳሪየም ጋራሚነረም’ የተባለው ፈንገስ የስንዴ፣ ባቄላ፣ በቆሎ እና ሩዝ ሰብሎችን ሙሉ ለሙሉ የሚያጠፋ በሽታ የሚያስከትል ሲሆን ምግብ ላይ ሲገኝ ደግሞ የጉበት ጉዳት ያስከትላል።

ፈንገሱ በሳይንስ ጽሑፎች “እምቅ የግብርና የሽብር መሳሪያ” የሚል ስያሜ እንዳለው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገልጿል።

“በመላው ዓለም በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላሮች የምጣኔ ሀብት ኪሳራ” የሚያደርስ መሆኑንም አክሎ ተናግሯል።

ባለስልጣናቱ ሴቷ ተከሳሽ ተህዋሲያኑን በቻይና ለማጥናት ከቻይና መንግሥት ገንዘብ ተቀብላለች ሲሉ ተጨማሪ ክስ ያቀረቡ ሲሆን፤ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አባል መሆኗንም ተናግረዋል።

የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ጀሮም ኤፍ ጎርገን ጁኒየር ክሱን “ከባድ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት” ብለውታል።

“እነዚህ ሁለት የውጭ አገር ዜጎች፤ ‘እምቅ የግብርና የሽብር መሳሪያ’ ተብሎ የሚታወቅ ፈንገስ በመሀል አሜሪካ አስገብተዋል። ግባቸውን ለመምታት በሚቺገን ዩኒቨርስቲ ቤተ ሙከራ ለመጠቀም ወጥነው ነበር” ብለዋል።

የወንጀል ምርመራው በአሜሪካ የምርመራ ተቋም (ኤፍቢኤይ) እና በአሜሪካ የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ በጋራ መደረጉ ተነግሯል።

ያንኩንግ ጂያን ማክሰኞ በዲትሮይት ሚቺጋን ፍርድ ቤት ትቀርባለች።

ቢቢሲ ለሚቺገን ዩኒቨርስቲ እና በዋሽንግተን ለቻይና ኤምባሲ አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቋል።

ክሱ የቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት በሻከረበት እና ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቻይና ተማሪዎችን ቪዛ እንደሚነጥቁ በተናገሩበት ወቅት የመጣ ነው።

በሳምንቱ መጀመሪያ በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ የሚማር ቻይናዊ በ2024ቱ ምርጫ በሕገ ወጥ መንገድ በመምረጥ ክስ ቀርቦበታል።