
ከ 6 ሰአት በፊት
የእስራኤል ጦር በጋዛ ወደ እርዳታ ማከፋፈያዎች የሚወስዱ መንገዶች እንደ “የጦርነት ቀጠና” ተደርገው እንደሚወሰዱ በማስጠንቀቅ ረቡዕ ዕለት እንደሚዘጉ አስታወቀ።
ባለፈው ሳምንት ስራ የጀመረው እና በአሜሪካ እና እስራኤል የሚደገፈው አወዛጋቢው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን የማዕከላቱን “አደረጃጀት እና ቅልጥፍና መጨመር የሚያስችሉ ማሻሻያ ስራዎች” ለመስራት በሚል እንደሚዘጋ ተናግሯል።
ድርጅቱ እሰራቸዋለሁ ካላቸው የማሻሻያ ስራዎች በተጨማሪ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ፍልስጤማውያን ወደ እርዳታ ማከፋፈያ ማዕከላቱ እንዳይገቡ ወይም ወደ እነሱ በሚወስዱ መንገዶች መንቀሳቀስ “የተከለከለ ነው” ብሏል።
ማክሰኞ ምሽት ላይ ቢያንስ 27 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው መሞታቸውን በሃማስ የሚመራ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ገልጿል።
በቀናት ልዩነት ውስጥ ወደ እርዳታ ማከፋፈያዎቹ በሚወስደው መንገድ ላይ አደጋ ሲከሰት ይህ ሦስተኛው ነው።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ “ከተመረጡት የመዳረሻ መንገዶች በማፈንገጥ” ወደ እነርሱ በማምራት ላይ የነበሩ የተለዩ ተጠርጣሪዎች ላይ ወታደሮቹ መተኮሳቸውን ተናግሯል።
የማክሰኞውን ክስተት ተከትሎ በካን ዮኒስ የሚገኘው የናስር ሆስፒታል ዳይሬክተር አቴፍ አል-ሀውት የእስራኤል ወታደሮች “በምዕራብ ራፋ እርዳታ ለመቀበል እየጠበቁ በነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ” ላይ ተኩስ ከከፈቱ በኋላ በጥይት ተመትተው የተጎዱ ሰዎች እየመጡ ነው ብለው ነበር።
በሃማስ የሚመራ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ሰላማዊ ዜጎች በእርዳታ ጣቢያ አቅራቢያ በታንክ፣ በድሮኖች እና ሄሊኮፕተሮች ተተኩሶባቸዋል ብለዋል።
በአካባቢው የሚሰሩ የውጭ አገር የሕክምና ባለሙያዎች ሁኔታውን “አጠቃላይ እልቂት” ሲሉ ገልፀው በተጎጂዎች መጥለቅለቃቸውን ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ በመግለጫው ወታደሮቹ “የጋዛን ሰላማዊ ዜጎች ወደ ሰብዓዊ እርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች እንዳይሄዱ እየከለከሉ አይደለም” ብሏል።
የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ሐሙስ ዕለት እንደገና እርዳታ ማከፋፈል እንደሚጀምር ተናግሯል።
የረድኤት ቡድኑ ቃል አቀባይ የእስራኤል ጦር በወታደራዊ ድንበሮች አቅራቢያ “ግራ መጋባት ወይም ፍጥጫ” ውስጥ የሚያስገቡ አደጋዎችን ለመቀነስ “የእግር እንቅስቀሴን እንዲያሳልጥ” ጠይቋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን አክሎም ለሰላማዊ ዜጎች የበለጠ ግልጽ መመሪያን ለማዘጋጀት እና ደኅንነታቸውን ለመደገፍ የሚያስችል ስልጠናዎችን ለማሻሻል እየሰራ ነው።
“አሁንም የእኛ ዋና ተቀዳሚ ጉዳይ እርዳታ የሚያገኙ ሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት እና ክብር ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በተፈጸመው ጥቃት ላይ “አፋጣኝ እና ገለልተኛ” ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የጉተሬዝ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእርዳታ ማዕከላት መዘጋታቸው “የሰብዓዊ ድርጅቱ ማን እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን” እና “የተጠያቂነት እጦት” መኖሩን ያሳያል።
“በእነዚህ ማከፋፈያዎች ዙሪያ የታጠቁ ኃይሎችን እያየን ነው። ማን እንደሆኑ፣ ለማን ተጠያቂ እንደሆኑ ማንም አያውቅም” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋዛ ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውን አስጠንቅቋል።
በጋዛ እርዳታ መከፋፈል የጀመረው እስራኤል ለ11 ሳምንታት አጠቃላይ የምግብ እና ሌሎች እርዳታዎች እንዳይገቡ ካገደች በኋላ ነው።
ሃማስ መስከረም 26/ 2016 ዓ.ም. የእስራኤልን ድንበር ተሻግሮ ጥቃት በመፈፀም 1,200 ሰዎች ሲገደል 251 ሌሎች ደግሞ አግቶ ወስዷል።
የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ 54,470 ሰዎች ተገድለዋል ይላል።