
ከ 7 ሰአት በፊት
ኢሎን መስክ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የግብር እና የወጪ ሕግ “አሳፋሪ እና አስጸያፊ” ሲል ኮነነው።
የባለብዙ ትሪሊዮን ዶላር የታክስ እፎይታ እና ተጨማሪ የመከላከያ ወጪዎችን ጨምሮ የአሜሪካ መንግሥት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲበደር የሚፈቅደው ይህ ሕግ በግንቦት ወር በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጹ ላይ በለጠፈው ጽሑፍ ላይ “ይህንን ሕግ ለማጽደቅ ድምጻቸውን የሰጡ ያሳፍራሉ” ብሏል።
ቢሊየነሩ መስክ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ዶጅ ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለ129 ቀናት ወጪን ለመቀነስ ከሠራ በኋላ በድንገት አስተዳደሩን መልቀቁ ይታወሳል።
ኤለን መስክ ቀደም ሲል እቅዱን “አሳዛኝ” ብለው የጠራው ቢሆንም፣ አሁን የሰጠው አስተየየት ግን የመንግሥትን ኃላፊነት ከለቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያለውን አለመግባባቱን ያመለክታል።
ደቡብ አፍሪካ የተወለደው ቢሊየነሩ መስክ ምንም እንኳን ትራምፕ “ሁልጊዜም ከእኛ ጋር በመሆን በሁሉም መንገድ ይረዳናል” ቢሉም፣ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ያለው ስልጣን ከቀናት በፊት ግንቦት 23/2017 ዓ.ም. አብቅቷል።
ትራምፕ “ግዙፍ ቆንጆ ሕግ ” ብለው የሚጠሩት ይህ አዋጅ መንግሥታቸው ያለበትን የበጀት ጉድለት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚያደርገው ተገምቷል ።
ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገፁ ላይ በተከታታይ ባጋራቸው ልጥፎች ላይ መስክ “አስፈሪ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ወጪን ለመሸፈን” የወጣ ሕግ “ቀደም ሲል ያለውን ግዙፍ የበጀት ጉድለት ወደ 2.5 ትሪሊዮን ዶላር (!!!) በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል” እንዲሁም ” የአሜሪካ ዜጎችን በሚያስደነግጥ አስተማማኝ ባልሆነ እዳ ይጫናቸዋል” ሲል ተችቶታል።
ከዚህ ቀደም የትራምፕን አጀንዳ በሚቃወሙ ሪፐብሊካን የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ቃል ገብቶ የነበረው መስክ በሌላ ልጥፍ ላይ ከዚህ በተቃራኒ የቆመ የፖለቲካ ማስጠንቀቂያ አክሎ ተናግሯል።
“በሚቀጥለው ዓመት ሕዳር ወር ላይ የአሜሪካን ሕዝብ የከዱ ፖለቲከኞችን በሙሉ እናባርራለን” ሲል ጽፏል።
ከመጀመሪያው ጽሑፍ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ስለ መስክ አስተያየት የተጠየቁት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሌቪት “ፕሬዚዳንቱ ኤሎን መስክ በዚህ ሕግ ላይ ያለውን አቋም ያውቃሉ” ብላለች።
“ይህ አንድ፣ ትልቅ፣ የሚያምር ሕግ ነው” ስትል አክላለች። “እናም በአቋማቸው እንደፀኑ ናቸው።”
ሕጉ በ2017 በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር ጊዜ የጸደቀውን እና በቅርቡ የሚጠናቀቀውን የግብር ቅነሳ እና ለመከላከያ ወጪ የሚመደበውን የገንዘብ መጠን ለማራዘም ያስችላል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም አስተዳደሩ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞችን በጅምላ ለማባረር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ያስችለዋል።
እንዲሁም መንግሥት የሚበደረውን የገንዘብ ጣሪያ ለማንሳት ሀሳብ አቅርቧል።
የመስክ አስተያየት በሪፐብሊካኖች መካከል ያለውን ሰፊ ውጥረት የሚያንፀባርቅ ነው።
ሴኔቱ ጋር የደረሰው ይህ ሕግ በሪፐብሊካን ቁጥጥር ስር ባለው ምክር ቤት ውስጥ ክፍፍሎች መኖራቸውን አሳይቷል።
የኬንታኪ ሪፐብሊካን ተወካይ ሴናተር ራንድ ፖል ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሕጉ የዕዳ ጣሪያውን ከፍ ማድረግን የሚያካትት ከሆነ አዋጁን እንደማይደግፉ ተናግረዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ ኒውስ በሳምንቱ መጨረሻ “የሪፐብሊካን ፓርቲ ድምፁን የሚሰጥ ከሆነ የእዳው ባለቤት ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በፖል አቋም የተበሳጩት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቁጣ የተሞሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ስለ ሕጉ በጣም ትንሽ ግንዛቤ አለው” ካሉ በኋላ “የኬንታኪ ሰዎች ሊደግፉት አይችሉም” ሲሉ ወንጅለውታል።
ትራምፕ “የእሱ ሀሳቦች በእውነቱ የእብድ ናቸው” ሲሉም ጽፈዋል።
የሪፐብሊካን ሕግ አውጭዎች የመስክን አስተያየት ገሸሽ አድርገውታል።
የሴኔቱ መሪ ጆን ቱኔ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩትፓርቲው “የአመለካከት ልዩነት” ቢኖረውም “ሙሉ በሙሉ ወደፊት ለመቀጠል” አቅዷል ብለዋል።
“ሁሉም ሰው የሚቆምለት አጀንዳ አለው፤ በተለይም ፕሬዝዳንቱ።”
ሕጉን በምክር ቤቱ በኩል ያፀደቀው የሪፐብሊካኑ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ማይክ ጆንሰን “ጓደኛዬ ኢሎን በጣም ተሳስቷል” ሲሉ በካፒቶል ሂል ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ጆንሰን “በጣም አስፈላጊ የሆነው መጀመሪያ መጀመር ነው። ኤሎን ይህንን ስቷል”
ጆንሰን ሰኞ ዕለት ከባለጸጋው ጋር ስለ ሕጉ 20 ደቂቃ የቆየ የስልክ ውይይት ማደረጋቸውን ገልፀው ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚፈቀደውን የታክስ ክሬዲት ማቋረጥ በመስክ ኩባንያ ቴስላ ላይ “ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል” ተነጋግረናል ብለዋል።
“በዚያ አዝናለሁ” ያሉት ጆንሰን፣ በስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላም መስክ ሕጉን መተቸቱ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
“ይህን ስህተት በመስራቱ በጣም አዝኛለሁ።”
መስክን ካበሳጩት ጉዳዮች መካከል በፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ውስጥ የአየር ትራፊክ ቁጥጥርን ያካተተው ውሳኔ እንደነበር አክሲዮስ ዘግቧል።
መስክ አቪየሽኑ በእርሱ የስታርሊንክ ሳተላይት ሲስተም እንዲሰራ ፈልጎ ነበር።
ነገር ግን ከቴክኖሎጂ እና ከጥቅም ግጭት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክንያት ተከልክሏል ሲል መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።
በመስክ እና በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ በነበበረው ኃላፊነቱ ላይ ትችት ሲዘነዝሩ የቆዩ አንዳንድ ዲሞክራቶች አሁን አስተያየቱን በደስታ ተቀብለዋል።
የሴኔቱ የዲሞክራቶች መሪ የሆኑት ቸክ ሹመር “የአጠቃላይ ሂደቱ አካል የሆነው እና የትራምፕ ጓደኛ ኤለን መስክ እንኳን ሕጉ መጥፎ ነው ብሏል። ይህ ሕግ ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ መገመት እንችላለን” ብለዋል።
ትራምፕ እና ሪፐብሊካኖች በኮንግረስ ውስጥ ሕጉ እንዲፀድቅ እና እንዲፈርም ለሐምሌ 4 ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።
መስክ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የለጠፋቸው ጽሑፎች ባለፈው ዓመት ሕዳር ወር በተካሄደው ምርጫ ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ ስጦታ በመስጠት ከደገፋቸው ከትራምፕ ጋር አለመግባባት እንዳለው ይጠቁማሉ።