
ከ 7 ሰአት በፊት
የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ አሽከርካሪ የሆኑት አቶ ታረቀኝ* ብዙ ጊዜ ይመላለሱበት በነበረው የአዲስ አበባ ወደ ጎጃም መስመር፣ ከፍቼ እስከ ጎሃ ጽዮን ያሉት አካባቢዎች ‘የሞት ቀጠና’ ነው የሚመስሏቸው።
በዚያ መስመር ሲመደቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ሞት አሊያም ቤተሰቦቻቸው ከእገታ ማስለቀቂያ ምፅዋት ሲጠይቁ ነው።
‘እንጀራ ስለሆነባቸው’ እንጂ በተደጋጋሚ በባልደረቦቻቸው ላይ ደርሶ የሰሙት እገታ እና ግድያ አንድ ቀን በእርሳቸውም ላይ ሊከሰት እንደሚችል ስጋት ነበራቸው፤ የሰጉትም አልቀረ።
ከሁለት ወር ገደማ በፊት በጠዋት ሥራ ቦታቸው ተገኝተው ከ50 በላይ መንገደኞችን አሳፍረው ወደ ደብረ ማርቆስ ለማቅናት ጉዞ ጀመሩ።
እንደ ወትሮው ሁሉ ለጉዞ ከተነሱ በኋላ የመንገድ ቅኝት እስከሚደረግ ድረስ ከአዲስ አበባ መውጫ ላይ ባሉ ኬላዎች ቆመው ጠብቀዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ተሽከርካሪዎች አዲስ አበባ መውጫ ላይ በጫንጮ እና በፍቼ ከተሞች በሚገኙ ኬላዎች ላይ ለረዥም ሰዓታት እንዲቆሙ ተደርጎ የመንገዱ ደኅንነት ይጣራል።
ቅኝቱን የሚያካሂዱት በየአካባቢዎቹ የሚገኙ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው።
አቶ ታረቀኝ እና ሌሎች አሽከርካሪዎች ከኬላዎቹ የተነሱት የመንገዱ ደኅንነት ከተረጋገጠ እና እንዲያልፉ ከተፈቀደላቸው በኋላ ነበር።
ሆኖም መንገዳቸውን ሳያገባድዱ ነበር ድንገት የተኩስ ሩምታ የተከፈተባቸው።
ጥቃቱ የተከፈተባቸው ከእገታ ጋር ተያይዞ ስሟ ከሚነሳው አሊ ዶሮ ቀበሌ ሳይደርሱ ባለች ትንሽ መንደር ላይ ነበር።
“ታጣቂዎቹ ወደ 30 ገደማ ይሆናሉ” የሚሉት አቶ ታረቀኝ፤ ከእርሳቸው በፊት ይጓዝ የነበረ አውቶብስ ካመለጣቸው በኋላ እርሳቸው ሲደርሱ ተኩሱ ድንገት እንደተከፈተባቸው ይናገራሉ።
“እንድንቆም ቢጠይቁን እነርሱ መሆናቸውን ስለምናውቅ እንቆም ነበር። ግን ተኩስ ነበር የከፈቱት። እኔም ለማምለጥ ስል ነዳሁት” ይላሉ።
መቆም የቻሉትም በዘነበባቸው ጥይት የተሽከርካሪው ጎማ ከተመታ በኋላ ነው። ድንጋጤ ውስጥ ስለነበሩ አንድ እግራቸው ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰ ያወቁት ከመኪናው ለመውጣት ሲሞክሩ እንደነበር ይናገራሉ።
“እንደምንም ወርጄ፣ በደረቴ እየተሳብኩ ከመኪናው መንገድ ከወጣሁ በኋላ በአንድ እግሬ እየዘለልኩ ስሮጥ ደረሱብኝ። እቆማለሁ ስል ወደቅኩ። ሌሎቹ ወደ መኪናው እየተኮሱ ተሳፋሪው እንዲወርድ አደረጉ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
“እያገላበጡ ሲፈትሹኝ እንደ ሞተ ሰው ዝም አልኳቸው። ኪሴ ውስጥ የነበረ ገንዘብ እና ስልክ ወስደው ሞቷል ብለው ጥለውኝ ሄዱ።”
ታጣቂዎቹ ትተዋቸው ከሄዱ በኋላ ግን [በግምት ከ30 ደቂቃ በኋላ] ሌላ ተኩስ መሰማት ተጀመረ። ይህ የሕይወታቸው የመጨረሻ ሰዓት ነበር የመሰላቸው።
“ታጣቂዎቹ ሊጨርሱኝ ድጋሚ የመጡ ነበር የመሰለኝ። ነገር ግን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው። ‘አይዟችሁ! ደርሰንላችኋል!’ ብለው ከወደቅኩበት አነሱኝ።”
አቶ ታረቀኝ እና ያሳፈሯቸው መንገደኞች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት እንደማሳያነት ጨለፍነው እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ በርካቶች የሚያልፉበት ተደጋጋሚ ክስተት ነው።
ከፍቼ – ጎሃ ጽዮን
ሲራክ* በአውራ ጎዳናው በሳምንት ውስጥ ቢያንስ አራት ጊዜ ይመላለሳል።
የጭነት መኪና በማሽከርከር በሚያገኘው ገቢ ራሱን እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ሲራክ፣ አካባቢውን የሚያልፈው በጭንቀት እንደሆነ ይናገራል።
ከፍቼ እስከ ጎሃ ጽዮን ድረስ ያሉት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች እጅጉን አስጊ ቦታዎች መሆናቸውንም ይጠቅሳል።
ሲራክ እንደሚለው ከፍቼ እስከ ሙከጡሪ፤ ከገርበ ጉራቻ እስከ ጎሃ ጽዮን ባሉት አካባቢዎች በመንገደኞች እና በአሽከርካሪዎች ላይ በርካታ ወንጀሎች ተፈፅመዋል።
ከእነዚህ ልዩ ቦታዎች መካከልም አሊ ዶሮ፣ ገርበ ጉራቻ፣ ሙከጡሪ፣ ቱሉ ሚልኪ፣ ጎርፉ ገብርኤል እና ዱበር የተባሉ አካባቢዎች እንደሚገኙበት አሽከርካሪው ይጠቅሳል።
በተደጋጋሚ የአውቶብስ ተሳፋሪዎች በታጣቂዎች ታግተው የመወሰዳቸው ዜና እየተለመደ እንደመጣ የሚናገረው አሽከርካሪው፣ “እኛም ተራችንን ነው የምንጠብቀው” ይላል።
ሲራክ እንደሚለው በዚህም ስጋት ምክንያት አሽከርካሪዎች እነዚህን አካባቢዎች በአንድ ላይ እጅብ ብለው ማለፍ ግድ ይላቸዋል።
“እነዚህን አካባቢዎች በቶሎ ለማለፍ ለቁርስም ሆነ ለምሳ፣ አንዳንዴ ለውሃ ሽንትም ቢሆን አንቆምም” ይላል።
በአውራ ጎዳናው ከሚሄዱ ሌሎች መኪኖች ጋር በጋራ አብሮ ለማለፍና ርቀትን ለመጠበቅ በፍጥነት ማሽከርከርን ስለሚጠይቅ አደጋ ሲከሰትም ተመልክቷል።
አለበል* የተባለ ሌላ አሽከርካሪም ከሲራክ የተለየ ሃሳብ የለውም። ለእርሱም ከፍቼ ጀምሮ እስከ ጎሃ ጽዮን ያለው አካባቢ የስጋት ቀጠና ነው።
መንግሥት ከታጣቂ ቡድን ጋር ግጭት ውስጥ በገባበት እና ከአዲስ አበባ ጋር በሁሉም አቅጣጫዎች በሚዋሰነው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱ ቢነገርም፣ እገታዎች ግን አልቆሙም።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚፈፀመው የሰላማዊ ሰዎች እገታ በክልሉ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሲከሰት ተዘግቧል።
ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል ኩዩ፣ ወረ ጃርሶ፣ ደገም፣ ሂደቡ አቦቴ፣ ያያ ጉለሌ የተሰኙ ወረዳዎች በተለየ ይጠቀሳሉ።
በደገም ወረዳ ሥር የምትገኘው አሊ ዶሮ ቀበሌ እና የወረ ጃርሶዋ ከተማ ቱሉ ሚልኪ እንዲሁም የኩዩ ወረዳ ከተማ – ገርበ ጉራቻ የእገታ ወንጀል ከሚፈፀምባቸው አካባቢዎች ስማቸው በዋናነት ይነሳል።
‘አሊ ዶሮ’ ግን ዋነኛ ማዕከል ናት። አሊ ዶሮ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ መንገደኞች ብቻ ሳይሆን፣ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችም በስጋት የሚያልፉባት አነስተኛ ቦታ ነች። ማለፍ የሚችሉትም ዕድል የቀናቸው ናቸው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ለምን በዚያ አካባቢ የእገታ ወንጀሎች እንደተበራከቱ እንደማያውቁ ይናገራሉ። ሆኖም ጉዳዩ ፖለቲካዊ ሳይሆን እንደማይቀር ግምት አላቸው።
“ድርጊቱን የሚፈፅመው ‘ሸኔ’ የሚባለው ታጣቂ ቡድን እንደሆነ ነው የምናውቀው፤ በአብዛኛው በዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የአማራ ተወላጆችን ዒላማ ይደረጋሉ” ሲሉም ብሔርን ዒላማ በማድረግ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር የሚጠቀሙበት መንገድ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በሌላ በኩልም ታጣቂዎቹ የገንዘብ አቅማቸውን ለማጎልበት ሲሉ እገታውን እንደሚፈፅሙ አሽከርካሪዎቹ ይጠቅሳሉ። በዚህም ታጋቾችን ለመልቀቅ ከመቶ ሺዎች እስከ ሚሊዮኖች የሚደርስ ገንዘብ ይጠይቃሉ።
“ታጣቂዎቹ ከጭነት አሽከርካሪ ይልቅ የሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ” የሚለው ሲራክ፣ ይህም በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን ለመያዝ እና በርከት ያለ ገንዘብ ለመጠየቅ ሲሉ የሚያደርጉት መሆኑን ይገልጻል።
የበርካታ ታጋች ቤተሰቦችም የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ስለማይችሉ በእምነት እና በገበያ ሥፍራ፣ በለቅሶ፣ በሰርግ እና በሌሎች ማኅበራዊ ክንውኖች ላይ ገንዝብ ሲለምኑ መመልከቱን ይናገራል።
“በፊት ለውጭ አገር ሕክምና ገንዝብ ለመሰብሰብ በየመንገዱ ምፅዋት እንደሚጠየቀው፣ አሁን ላይ የታገተ ቤተሰብን ለማስለቀቅ የሚለምኑ ሰዎችን ነው የምናየው።”
ምንም እንኳን በአካባቢው የፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ቢኖሩም ብዙውን ጊዜ የሚደርሱት ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ መሆኑ ጥያቄ እንደሚፈጥርበትም ይጠቅሳል።
“አሁን በአካባቢው ሚሊሻዎች እየተነሱ ነው የደረስኩት። ምን እንደሚያጋጥመኝ አላውቅም። እንግዲህ እንደ ዕድሌ ነው የማልፈው” ብሏል ሲራክ ቢቢሲ ባነጋገረው ወቅት።
በቅርቡ በተፈፀመ እገታ በታጣቂዎች ጉዳት የደረሰባቸው አቶ ታረቀኝም፤ እርሳቸው ያሽከረክሩት በነበረው አውቶብስ ላይ ጥቃት የተፈፀመው አሊ ዶሮ የተባለው አካባቢ አቅራቢያ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከአሊ ዶሮ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንደነበሩ ይናገራሉ።
“ኢስት ሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ነበሩ። ወንጀሉ በጠራራ ፀሐይ ሲፈፀም በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው እያዩ እና እየተኮሱ ነበር። ሆኖም ታጣቂዎቹ ሕዝቡን አሰልፈው ይዘው ሲሄዱ በአፋጣኝ የደረሰ አካል የለም” ይላሉ።
በዚያ መስመር ለመጓዝ መንግሥት ቀድሞ የፀጥታ ቅኝት ያደርጋል የሚሉት አቶ ታረቀኝ፣ ሰላም ነው ተብለው መንገድ ቢጀምሩም ከዚህ ጥቃት እና እገታ አላመለጡም።
ይህም የመንግሥት ኃይሎች የሚሳተፉበት የተቀነባበረ ሴራ እንዳለ እንዲጠረጥሩ አስገድዷቸዋል።
እገታውን የፈፀሙት በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች እንደሆኑ ከለበሱት ልብስ እና ከሁኔታቸው መረዳታቸውን አቶ ታረቀኝ ይናገራሉ።
መንግሥት ኦነግ ሸኔ ሲል በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው በተደጋጋሚ ለሚፈፀሙ የእገታ ወንጀሎች ይከሰሳል።
ታጣቂ ቡድኑ ግን ባለፈው ዓመት ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ ከ100 በላይ መንገደኞች እዚያው አካባቢ መታገታቸውን ተከትሎ ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ እጁ እንደሌለበት ገልጾ፣ ጣቱን የመንግሥት አካላት ላይ ቀስሯል።
የእገታ ማዕከል የሆነችው አሊ ዶሮ
አሊ ዶሮ ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን 142 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ትንሽ ቀበሌ ስትሆን፣ የምትገኘው መዲናዋን ከአማራ ክልል ጋር ከሚያገናኙ ዋና ጎዳናዎች አንዱን ተከትሎ ነው።
ቀበሌዋ በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደገም ወረዳ ውስጥ የምትገኝ ናት።
ስያሜዋን ያገኘችው በድሮ ጊዜ በዶሮ እርባታ የተሰማሩ አሊ የተባሉ ግለሰብ ስምን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል። በኦሮምኛ ቋንቋ ሙካ ቁሌ በሚል ስምም ትታወቃለች። ቢቢሲ እንዳነጋገራቸው አንድ የአካባቢው ተወላጅ ከሆነ ‘ሙካ ቁሌ’ የዛፍ ዓይነት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህቺ አነስተኛ መንደር በሚበቅልባት የዛፍ ዓይነት ሳይሆን በእገታ ወንጀል ነው ስሟ ጎልቶ የሚነሳው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ተወላጆች እንደሚሉት በአካባቢው እገታው የተበራከተው የኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ከወለጋ ወደ ሸዋ መዛመቱን ተከትሎ ነው።
ቀበሌዋ በግራ እና በቀኝ ያያ ጉለሌ እና ህደቡ አቦቴ በሚባሉ ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱባቸው ወረዳዎች የተከበበች እንደሆነች ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ታጣቂዎቹ በስፋት ሰፍረው የሚገኙት ሙገር በረሃ ውስጥ ነው። በመሆኑም የሙገር ወንዝን ተከትሎ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል እና ሆሮ ጉድሩ – ወለጋ ድረስ በሚዘልቅ ሰፊ በረሃ ውስጥ በስፋት ይንቀሳቀሳሉ።
ሙገር ወንዝ የአባይ ወንዝ ገባር ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋን ጨምሮ እስከ ወለጋ – ሆሮ ጉዱሩ ድረስ ይዘልቃል።
ታጣቂዎቹ ቀደም ብሎ በስፋት ወለጋ አካባቢ ይንቀሳቀሱ እንደነበር የሚገልጹት አንድ የአካባቢው ተወላጅ፣ ከአንድ ዓመት ወዲህ እንቅስቃሴያቸው ወደ ሸዋ የመጣው በወለጋ በተከሰተ የወባ በሽታ ምክንያት በርካታ ታጣቂዎች ከተጎዱ በኋላ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ታጣቂዎቹ በስፋት ይንቀሳቀሱበት በነበረው የክልሉ ቄለም እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የጤና ተቋማት አገልግሎት ባለመስጠታቸው እና መንግሥትም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መድኃኒት ማሠራጨት ባለመቻሉ በርካታ ሰዎች በወባ በሽታ መሞታቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር። ከእነዚህ መካከልም ታጣቂዎች እንደሚገኙበት ይገመታል።
የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ከህሙማኑ 35 በመቶው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን አመልክቶ ነበር።
በሌላ በኩልም መንግሥት በክልሉ በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች አጠናክሮ የወሰደው እርምጃ ታጣቂዎቹን ወደ ማዕከል እንዳስጠጋቸው የሚነገር ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ ግን ለዚህ የእንቅስቃሴ አድማሳቸው እየሰፋ መምጣቱን ይገልጻሉ።
ቢቢሲ ይህንን ማረጋገጥ ባይችልም ታጣቂ ቡድኑ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በሚገኙ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።
ለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ላይ በታጣቂዎች የሚሰነዘረው ጥቃት አንዱ ማሳያ ነው።
ከታኅሣሥ እስከ የካቲት 2017 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ወራት ብቻ በርካታ የዞኑ አመራሮች መንግሥት ሸኔ በሚለው ታጣቂ ቡድን በተፈፀመባቸው ጥቃቶች መገደላቸው ይታወሳል።
የኦሮሚያ የፀጥታ ኃይሎች፣ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት ካምፖች ከአካባቢው በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ።

“እገታ የሚፈፀመው በአብዛኛው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ነው” የሚሉት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ተወላጅ፣ ታጣቂዎቹ ይህን የሚያደርጉት በአንድ ጊዜ በርካታ ሰው ይዞ ለመሄድ እና ብዙ ገንዘብ ለመቀበል ስለሚፈልጉ እንደሆነ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን በአካባቢው ነዋሪዎችም ላይ ተመሳሳይ ወንጀሎች ቢፈፀሙም ማንነት ላይ መሠረት ያደረገ ጥቃት ለመፈፀም አካባቢውን ተመራጭ እንደሚያደርጉት እኚሁ ግለሰብ ይገልጻሉ።
“አካባቢው የአማራ ክልልን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ በሚፈፀሙት ወንጀሎች ዒላማ የሚደረጉት በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች ናቸው” ይላሉ።
አካባቢውን የሚያውቁና የመንግሥት ውስጠ አዋቂ የሆኑ አንድ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው በአካባቢው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም ወንጀሉ የሚፈፀምበት ቦታ አስቸጋሪ የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ።
እኚህ ውስጠ አዋቂ በአካባቢው የሚፈፀመውን እገታ እና ጥቃት የሚፈፅመው ማን ነው? የሚለው ጉዳይም አጠያያቂ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ከዚህ በፊት በሐረር መስመር በፈንታሌ እና ሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊት ይፈፀም እንደነበርና የፌደራል የፀጥታ ኃይል ከተሰማራ በኋላ መቆሙን የሚያስታውሱት ውስጠ አዋቂው፤ አሊ ዶሮ አካባቢ ላይ የሚፈፀመውን ወንጀል ማስቆም ያልተቻለው ለምን እንደሆነ ግን “እንቆቅልሽ ነው” ይላሉ።
“በሁሉም መስመር የሚያልፈው ዜጋ ነው። ለምን ይህኛው አካባቢ ትኩረት ተነፈገው? ለምን መገናኛ ብዙኃንስ ዝምታን መረጡ? ለትንሽ ነገር ትኩረት የሚሰጠው መንግሥት ይህንን ለምን ችላ አለው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
የእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ በባንክ በኩል እንደሚተላለፍ መስማታቸውንም ጠቅሰው፤ የመንግሥት ኃይሎች ተሳትፎም ሊኖርበት እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳላቸው ውስጥ አዋቂው ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተንሰራፋውን እገታ በተመለከተ መስከረም ወር ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በክልሎቹ ውስጥ ካለው የትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች፣ በተደራጁ ቡድኖች እና በአንዳንድ የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚደርስባቸው እገታ መባባሱን መግለጹ ይታወሳል።
አሊ ዶሮ እና በአካባቢው የተፈፀሙ እገታዎች
በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በርካታ የእገታ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። በአካባቢው ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው እና ከመሥሪያ ቤታቸው ተወስደው እንደሚታገቱ በተደጋጋሚ የተዘገበ ሲሆን፣ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችም የዚህ ወንጀል ሰለባ ሆነዋል።
ቢቢሲ ባለፈው አንድ ዓመት በአካባቢው በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ ብቻ የተፈፀሙ እና ሪፖርት የተደረጉ የእገታ ወንጀሎችን ነቅሶ ለማውጣት ሞክሯል።
- ግንቦት 2/2016 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ የተነሱ በተለምዶ አባዱላ በተባሉ የሕዝብ ማመላላሻዎች እና በሌሎች ተሽከርካሪዎች ተሳፍረው የነበሩ 29 መንገደኞች በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሙከጡሪ ከተማ መግቢያ ላይ ታግተው መወሰዳቸው ተዘግቧል።
- ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. መነሻቸውን ከአማራ ክልል፣ ደባርቅ እና ባሕር ዳር ከተሞች ያደረጉ ሦስት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ተሳፍረው የነበሩ ከ100 በላይ መንገደኞች ገርበ ጉራቻ አካባቢ ታግተው ተወስደዋል።
- መጋቢት 8/2017 ዓ.ም. ከ50 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ ሲጓዝ የነበረ ፈለገ ግዮን የተባለ ዘመናዊ አውቶብስ አሊ ዶሮ አቅራቢያ በጥይት ተመትቶ ተሳፋሪዎች ታግተው ተወስደዋል። በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይል ዘግይቶ በመድረሱ ታጋቾችን ማስመለጥ እንዳልቻለና ታጋቾቹ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማይታወቅ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የትራንስፖርት ማኅበር ባለሥልጣን በወቅቱ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ አጋቾቹን ለመልቀቅ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር መጠየቃቸውም ተዘግቧል።
- መጋቢት 13/2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ከጎርፎ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ሃይሩፍ ተብለው በሚጠሩ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች ሲጓዙ የነበሩ 40 ያህል ተሳፋሪዎች ታግተው ተወስደዋል። በወቅቱ አንድ አይሱዙ መኪና ከታጣቂዎቹ ለማምለጥ ሲሞክር ተገልብጦ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
- መጋቢት 27/2017 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ 56 መንገደኞችን አሳፍሮ እየተጓዘ የነበረ አገር አቋራጭ አውቶብስ ቱሉ ሚልኪ ላይ ጥቃት የተፈፀመበት ሲሆን፣ ተሳፋሪዎች ታግተው ተወስደዋል። በጥቃቱ ቢያንስ ስድስት ተሳፋሪዎች ተጎድተው፣ የረዳቱ ሕይወት ማለፉን የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እገታ ‘እንደ ወረርሽኝ’ የተስፋፋው መቼ ነው?
በኢትዮጵያ ስለ እገታ በስፋት መሰማት የጀመረው 17ቱ የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በታጣቂዎች ከታገቱ በኋላ ነበር።
ሆኖም ከዚያ በፊት በአገሪቷ እገታ ተፈፅሞ አያውቅም ማለት አይቻልም።
የእገታ ወንጀል ግን እንዲህ እንደ አሁኑ የዕለት ተዕለት ዜና ሆኖ የሚያውቅበት ጊዜ ያለ አይመስልም። እገታ እንደ ወረርሽኝ የተዛመተው ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ነው።
ለዚህም በአገሪቷ ውስጥ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ መኖር እና ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ተገቢው ክትትል እና እርምጃ አለመደረጉ እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል።
የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እገታ በተመለከተ በመንግሥት በኩል የተሰጡት ምላሾች እና በወቅቱ የነበሩት ውዥንብሮች በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ወንጀሎች በተለያዩ ቦታዎች እንዲፈፀሙ በር እንደከፈተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ይናገራሉ።
የተማሪዎቹ እገታ የሚከታተል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን ባለሥልጣናትም የተጎጂ ቤተሰቦችን አግኝተው አነጋግረዋል።
ሆኖም ግብረ ኃይሉ የደረሰበትን ሳያሳውቅ ተማሪዎቹም የደረሱበት ሳይታወቅ ዓመታት ተቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማሪያም እንደሚሉት አጋች የሚባሉት አካላት አንድም ጊዜ ለፍርድ አለመቅረባቸው፣ መደበኛ ስልክ እየተጠቀሙ ታጋቾችን ለመልቀቅ በገንዘብ ሲደራደሩ እንዲሁም በባንክ ገንዘብ ሲተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል አለመደረጉ ወንጀሉን አባብሶታል።
“በአሊ ዶሮ አካባቢ ተደጋጋሚ እገታ መፈፀሙም አንድም አካባቢው ላይ ያሉ የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆኑን፣ አሊያም ይህን ድርጊት ከሚፈፅሙ ወንጀለኞች ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ መጠርጠር ይቻላል” ይላሉ።
ይህም የሕግ መላላት መኖሩንና መንግሥት የሕግ የበላይነትን እያስከበረ አለመሆኑን የሚያመለክት እንደሆነም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ይናገራሉ።
“ዜጎች የሚደርስባቸውን ችግር እራሳቸው ጠይቀው ራሳቸው መልስ መስጠት ከጀመሩ ቆዩ” የሚሉ አንድ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው መንግሥት እየተንሰራፉ ያሉ ወንጀሎችን ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ይገልጻሉ።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታጠቅ አሰፋ በእገታ እና ጥቃት ስጋት ምክንያት አሁን ላይ ከወከሏቸው የፓርቲ አባላት ጋር ያላቸው ግንኙነት በአየር ጉዞ እና በስልክ ተወስኗል ይላሉ።
መጋቢት ወር 2017 ዓ.ም. ውስጥ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአንድ ቦታ ላይ [አሊ ዶሮ አካባቢ] ተመሳሳይ ወንጀል እንደተፈፀመ የሚጠቅሱት አቶ ታጠቅ፣ አካባቢው በአሰቃቂ ድርጊት ሲወረር የሚወሰድ እርምጃ የለም ሲሉም ይወቅሳሉ።
“ከሦስት ዓመት በፊት ለማደራጀት ሥራ ወደ ባሕር ዳር ሄጄ ነበር። ወደ አዲስ አበባ እየተመለስኩ ሳለ የአባይ በረሃን ሳንሻገር በርካታ ተሽከርካሪዎች ተደርድረው ቆመዋል። ተሽከርካሪዎቹ የቆሙት በአንድ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተፈፅሞ መኪናው በመገልበጡ ነው። ሹፌሩ እና ረዳቱም በጥይት ተመትተዋል” ሲሉ እማኝነታቸውን የሚናገሩት አቶ ታጠቅ፣ አካባቢው በመከላከያ ቁጥጥር ሥር መዋል የቻለው ከ15 ደቂቃ ገደማ በኋላ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች የሚፈፀሙት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሥፍራው ከተነሱ በኋላ መሆኑም ጥያቄ እንደፈጠረባቸው ያስረዳሉ።
የአካባቢው ነዋሪዎችም በተለያዩ ጊዜያት አደባባይ በመውጣት ሰላም እንዲመጣ ተማፅኗቸውን በተደጋጋሚ አሰምተዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲም በኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ ለማግኘት እየተፈፀሙ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች እና የተማሪዎች እገታዎች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።
ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተፈፀመውን የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እገታን ተከትሎ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙት እገታዎች እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች ምን ያህል ወንጀለኞችን እንዳደፋፈሩ እና የሕግ የበላይነትን እንዳዳከሙ ያሳያሉ ብለዋል።
መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂ ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ሲገልጽ ቢቆይም በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን እና እገታዎችን ማስቆም ግን አልቻለም።
______________________________
* ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የተለወጠ