
ከ 2 ሰአት በፊት
ከዕለት ዕለት የግንኙነታቸው መበላሸት ይፋ የወጣው ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ቀጥተኛ ባለሆነ መንገድ በነገር እየተጎነታተሉ፣ አንዳቸው ሌላቸውን እየወቀሱ እና እየከሰሱ ይገኛሉ።
የአገራቱ መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለያዩ አጋጣሚዎች በተዘዋዋሪ የሚያቀርቡት ክስ እና የቃላት ምልልስ ከዕለት ዕለት እየጠነከረ የመጣ ይመስላል።
ማክሰኞ ግንቦት 26/2017 ዓ.ም. የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ምላሽ የሚመስል መልዕክት አጋርተዋል።
የማነ ገበረመስቀል “በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ደጋፊዎች/ተሳዳቢዎቸ ስለ ኤርትራ ማንኛውንም ነገር መተቸት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ የኤርትራው ፕሬዝደንት በ34ኛው የነጻነት በዓል ላይ ኢትዮጵያን ጠቅሰው ከተናገሩ በኋላ “አገር ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ” አገራት “በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር መሞከራቸው የተለመደ ባህሪ እንደሆነ እናውቃለን” ብለው ነበር።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአገሪቱ ነጻነት በዓል ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ግንቦት 16/2017 ዓ.ም. በተከበረው የአገሪቱ 34ኛ ዓመት ነጻነት በዓል ላይ “የውጭ ኃይሎች በብልጽግና ወኪላቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ያወጁት ጦርነት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ የሚያሳይ ነው” በማለት ተናግረው ነበር።
ይህንን ንግግር ተከትሎም የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትሯም የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በስም ያልጠቀሷቸው አካላትን “ምክር እየሰሙ ብድግ፣ ብድግ ለሚሉ ትናንሽ ኃይሎች የተደራጀ” እንዳልሆነ ተናግረዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‘ሆርን ሪቪው’ በተባለ ድረ ገጽ ላይ ባወጡት ጽሑፍ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲያስወጣ እና ለኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎች ድጋፍ ከመስጠት እንዲታቀብ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኤርትራ መንግሥት “የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛቶች እስከ ወዲያኛው ተቆጣጥሮ ሊቀጥል አይችልም” ሲሉ በጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል።
ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከትግራይ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ ሠራዊት በሕግ የተሰጠው ቦታ ላይ እንደሚገኝ እና ከዚያ ውጪ ያዛቸው ቦታዎች ካሉ የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሁለት አስርታት በላይ በፍጥጫ ውስጥ ከቆዩ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸው ቢሻሻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በመካከላቸው ያለው ቅራኔ እየጎላ መጥቷል።
ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ላይ ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመቆም የተሳተፈች ሲሆን፣ ደም አፋሳሹ ጦርነት በፕሪቶርያ ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ መትቷል።
የማነ ገብረ መስቀል የብልጽግና ፖለቲካ ደጋፊዎች ወይንም ተሳዳቢዎች ያሏቸውን “የአገሪቱን ጥንታዊ እና ዘመናዊ ታሪክ በመከለስ እና በማዛባት” የወነጀሉ ሲሆን፣ የኤርትራን ምጣኔ ኃብት እና እምቅ አቅም ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ ሲሉ ኮንነዋቸዋል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የዚህ መነሻ “የባሕር በር ለማግኘት ካለ ጥልቅ ፍላጎት ነው” ያሉ ሲሆን፣ ይህም “የጎረቤት አገራትን ሉዓላዊ መሬት እስከመውሰድ ይደርሳል” ሲሉ ወንጅለዋል።
የማነ ገብረ መስቀል የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብት እድገት በኤክስ ልጥፋቸው ላይ አጣጥለው “ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስተርታት ተደጋጋሚ የእዳ እፎይታ ማግኘቷን መዘንጋት የለብንም” ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ለዘላቂ ልማት ትልቅ አቅም አለ ያሉት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፣ “ነገር ግን እውነተኛ እድገት የሚወሰነው በዓለም አቀፍ ሕግ በማክበር ላይ ባለው ዘላቂ ቀጣናዊ ሰላም ላይ ነው” ብለዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሆርን ሪቪው ላይ ባወጡት ጽሑፍ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ዋና ትኩረት የትግራይ እና የአማራ የብሔር ሚሊሻዎችን በማሰባሰብ ‘የውጭ ኃይሎች መሳሪያ ሆኗል’ የሚሉትን የኢትዮጵያ መንግሥት “መገልበጥ” ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
አምባሳደር ዲና ይህ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጣልቃ ገብነት አደገኛ ውጤት ይኖረዋል በማለት አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር “የውጭ ኃይሎች በብልጽግና ወኪላቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ያወጁት ጦርነት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ የሚያሳይ ነው” በማለት ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት “የጦር መሳሪያ ግዢ እና የወታደራዊ ዝግጅት” ላይ ነው ሲሉ የከሰሱት ኢሳያስ፤ “እነዚህ የታቀዱ ጦርነቶችን ለማስጀመር የጦር መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጅዎችን ለማግኘት የሚደረገው የግዢ ጥድፊያ፣ ተጓዳኝ ፉከራዎች እና ወታደራዊ ዝግጅት ሁሉም ያወቀው እና የመዘገበው ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ሊያቀርቡ የሚፈልጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ” ነው በማለት ከስሰዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተለይም “የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ” በማለት የሰነዘሩት ሃሳብ ከተለያዩ አካላት ጠንካራ ምላሾችን አስከትሏል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ በኤርትራ በኩል ስጋት ተፈጥሯል።
ይህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር ትብብር በመፍጠር ውጥረቱ ተባብሷል።
በተጨማሪም በይፋ ባይነገርም ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ የምትከሰስ ሲሆን፣ በተመሳሳይም የኤርትራ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት እስከ መክፈት ደርሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተቃቃረው እና ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸው በስፋት እየተነገረ ይገኛል።
በድንበር ይገባኛል ምክንያት ጦርነት ውስጥ ከብተው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞቱበት ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሌላ ዙር ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አይሏል።