የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ
የምስሉ መግለጫ,የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ

ከ 1 ሰአት በፊት

ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች “ውስን” ስፍራዎች ውጪ በኢትዮጵያ “ሰብዓዊውም፣ ቁሳዊም ጉዳት እያደረሰ ያለ ግጭት የለም” ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ከገዢው ፓርቲ ጋር ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ረዘም ያለ ቃለ ምልልስ ላይ የአገሪቱ ሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑን እና “ነባራዊ ሁኔታን” እያነፃፀሩ አስረድተዋል።

አቶ መሐመድ አስቀድመውም ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ የትግራይ ጦርነት በማንሳት “ብስለትን መሠረት ያደረገ እርምጃ” ባሉት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ግጭቱ ማብቃቱን አድንቀዋል።

የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭትን በተመለከተም ከሁለት ዓመታት በፊት የክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደነበሩ አንስተው ክልሉ “ከፍተኛ ሰላም መደፍረስ” እንደነበረበት አስታውሰዋል።

በክልሉ ውስጥ መንግሥት ባከናወናቸው ሥራዎች እና በኅብረሰተሰቡ “አስተዋይነት” ነባራዊ ሁኔታው መቀየሩን ጠቅሰው “ከዕለት ዕለት የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ ነው” ብለዋል።

ክልሉ ካሉት 265 ወረዳዎች ውስጥ መንግሥት የማይቆጣጠራቸው ሁለት ወረዳዎችን ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትር መሐመድ፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ስምንት ትላልቅ ከተሞች “ሰላማዊ ናቸው” ብለዋል።

“. . . የመንግሥትን መኖር ሙሉ ነው ብለን መናገር የማንችልባቸው አንድ [ወረዳ] በከፊል፤ አንድ ደግሞ ከከፊል ከፍ ባለ መልኩ መንግሥት የለባቸውም የምንላቸው ሁለት ወረዳዎች ናቸው” ብለዋል።

ክልሉ ካሉት ከአራት ሺህ ገደማ ቀበሌዎች ከ80 በመቶ በላይ የመንግሥት መዋቅቅር ወደ ሥራ ተመልሷል ያሉት ሚኒስትሩ “መሠረታዊ አገልግሎት” እየሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ አክለው ሲያብራራ “ቀሪዎቹ ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ ናቸው ወይም በሌላ ኃይል ቁጥጥር ስር ውለው ሳይሆን” ተደራሽ ባለመሆናቸው ነው በማለት በታጣቂዎቸ ቁጥጥር ስር አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የሚናገሩት የፋኖ ታጣቂዎች ከዋና ዋና ከተሞች ውጪ ያሉ የክልሉን አብዛኛውን አካባቢ እንደሚቆጣጠሩ ይናገራሉ።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ “በክልሉ ውስጥ ፍላጎቱን የሚያስፈፅም፤ ከታጠቁ [ከመንግሥት] ኃይሎች ጋር ፊት ለፊት የሚያጠቃ ወይም የሚመክት፤ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ላስተዳድር የሚል ኃይል የለም” በማለት የዕለት ከዕለት “እንቅስቃሴን የሚያውኩ ወንጀለኞች የሉም ማለት ግን አይደለም” ብለዋል።

በስም ያልጠሯቸው የፋኖ መሪዎች ክልሉን ለቀው በጎረቤት አገራት “ብቅ ጥልቅ” የሚሉ እንጂ “ያን ያህል ተፅዕኖ የሚፈጥሩበት ሁኔታ ላይ አይደሉም” በማለት ተገዳዳሪ ኃይል የለም ሲሉ አጣጥለዋል።

“መንግሥት እግሩን ተክሎ፤ ለኅብረተሰቡ የሚገባውን አገልግሎት መስጠት፤ ሰላም እና ፀጥታ ማስከበር የሚችልበት ሙሉ ቁመና ላይ እየደረሰ ያለበት ዋዜማ ነው” ሲሉም መንግሥት በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሚኒስትሩ አክለዋል።

ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መደበኛ እንቅስቃሴዎች እና የመንግሥት ሥራ የተገደበ መሆኑን እና መደበኛ እንቅስቃሴዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት መስተጓጎላቸውን በከተሞች እና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

መንግሥት ‘ሸኔ’ ከሚለው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ችግር ባለበት የኦሮሚያ ክልልን ሰላም ሁኔታን አያይዘው ያነሱት አቶ መሐመድ “በተወሰዱ የፖለቲካ ውሳኔዎች” በክልሉ “መንግሥት ውስጥ ጠንካራ ሆኗል” ብለዋል።

ነገር ግን በክልሉ “ጥቂት ኪስ ቦታዎች” ላይ ብቻ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል።

በተለይ በምዕራብ እና በደቡብ እንዲሁም በማዕከላዊ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት ጥቃቶች እየተፈጸሙ በሰላማዊ ሰዎች እና በየአካባቢ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጭምር ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል።

ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እንድሪስ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልልሎች ባሻገር በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰላም መኖሩን የተናገሩ ሲሆን፤ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ውስን የፀጥታ ሁኔታ ውጪ “ሰብዓዊውም ቁሳዊም ጉዳት እያደረሰ ያለ ግጭት የለም” ብለዋል።

መገናኛ ብዙኃን በተለይም የማኅበራዊ ትስስር ገፆች “ፍርሃትን በመፍጠር” አቅደው ከገሃዱ ዓለም በተቃራኒ ይሠራሉ ሲሉ የወቀሱት ሚኒስትሩ፤ የሚፈጠሩ ትናንሽ ሁኔታዎችን ያጋንናሉ ሲሉም ከሰዋል።

ለዚህም ማሳያ ሲጠቅሱ ከውጭ አገሩ የሚመጡ እንግዶች “መጀመሪያ ቀን የሚያሳዩት ባህሪ እና ከሳምንት በኋላ ሚያሳያት ባህሪ ይለያያል” ብለዋል።

ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በንግግር ብቻ እንደሚፈቱ የጠቀሱት አቶ መሐመድ፤ እንቅስቃሴያቸውንም “ባህላዊ እና ኋላቀር” ብለውታል።

በሰላማዊ መንገድ ግባቸውን ለማሳከት የፈለጉ ኃይሎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ክፍት ነውም ብለዋል።

በሁለቱ የአገሪቱ ትላቅ ክልሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ታጣቂ ቡድኖች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገልጸው መንግሥት፣ የፀጥታ ኃይሉን በክልሎቹ ውስጥ አሰማርቷል።

በእነዚህ ክልሎች በሚካሄዱ የትጥቅ ግጭቶች ምክንያት የነዋሪዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ከመፈጠሩ በተጨማሪ ታጣቂዎቹ እና የመንግሥት ኃይሎች ተጠያቂ በተደረጉባቸው ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መንግሥታዊው የመብት ድርጅት ኢሰመኮን ጨምሮ ሌሎችም ሪፖርት ሲያደርጉ ቆይተዋል።