

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
ፖለቲካ ሰሞነኛ ውይይቶችና የመንግሥት ሠራተኞች ጥያቄ
ቀን: June 4, 2025
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሰሞኑ ከከተማ አስተዳደሩ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ አስተዳደሩ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ወደ 13 ሺሕ ተጨማሪ የጤና ባለሙያዎች መቀጠራቸውንና በአጠቃላይ የሕክምና ዘርፉ ሠራተኞች ቁጥር ወደ 32 ሺሕ ማደጉን ገልጸዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ሥር 41 ሺሕ መምህራን፣ በብዙ ሺዎች የሚጠቀሱ ፖሊሶች ወደ 12 ሺሕ የደንብ አስከባሪዎች፣ ወደ 30 ሺሕ ፅዳት ሠራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ በተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች ከ200 ሺሕ በላይ ሠራተኞች እንዳሉ ተናገረዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ቢሮዎች ተቀጣሪዎች ደግሞ የቤት፣ የትራንስፖርት፣ የኑሮ ውድነት፣ የደመወዝ ማሻሻያና ሌላም ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች እንዳላቸው የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ አስተዳደራቸው ለዚህ ሁሉ ሠራተኛ በአንዴ ሁሉንም ጥያቄ ይመልስ ቢባል ከባድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን ደረጃ በደረጃ የሠራተኞችን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሞከር ሲያብራሩም ተደምጠዋል፡፡ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ተብሎ ተከፋፍሎ የሚከናወን ሥራ መኖሩን በመጥቀስ፣ በአንድ ሌሊትና በአንድ ጀምበር ሁሉንም የሠራተኞች ጥያቄ መመለስ እንደማይቻል ነው ያብራሩት፡፡
በአጠቃላይ 16 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በ58 የፌዴራል መንግሥት ቢሮዎች ውስጥ ከ400 ሺሕ በላይ የመንግሥት ተቀጣሪዎች መኖራቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ 1.4 ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች አሉም ይባላል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ደግሞ፣ በአገሪቱ 2.5 ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው ያሉት፡፡ በ2016 ዓ.ም. መገባደጃ ለ2017 ዓ.ም. የበጀት ዕቅድ ሲቀርብ ለእነዚህ የመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ጫናን መቋቋሚያ እንዲሆን፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ እንደሚደረግ በመንግሥት ተነግሮ ነበር፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ 90 ቢሊዮን ብር የደመወዝ ማስተካከያ በጀት በዕቅድ መያዙን ተናግረው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ በትንሹ 1,500 ብር ዝቅተኛ ደመወዝ የሚያገኝ የመንግሥት ተቀጣሪ ወደ 300 ፐርሰንት የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግለት ቃል የተገባ ሲሆን፣ በየእርከኑ ላሉ ሠራተኞች ከ30 በመቶ ጀምሮ ጭማሪ እንደሚደረግላቸውም ነበር ዕቅድ የቀረበው፡፡
ይህም ተደረገ ከተባለ ወዲህ ግን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚጠይቁ የመንግሥት ሠራተኞች በርክተዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ደመወዝ ይጨመርልን የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ጠንከር ያለ ምላሽ እስኪሰጡበት ድረስ መነጋገሪያ የፈጠረ ጉዳይ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡ በሒደት የመምህራኑ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ወደ ሌሎች የሥራ መስክ ሠራተኞችም ሲሸጋገር መታየት ጀመረ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከመምህራን በተጨማሪ ሐኪሞች ጠንከር ያለ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ይህ የሠራተኞች ጥያቄ ደግሞ ከመንግሥትም አልፎ ወደ ግሉ ዘርፍ ሠራተኞች የተሸጋገረ ሲሆን፣ በቅርቡ የዲኤችኤል ሠራተኞች እንዲሁም የኤልሲ ዊዲ ኬብል ማምረቻ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ማንሳት ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
አሁን የሠራተኞች የደመወዝና የኑሮ መደጎሚያ ገቢ የማግኘት ጥያቄ እየበረታ የመጣው ደግሞ በአገሪቱ ባለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የዋጋ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት እስከ 35 በመቶ መድረሱ የተነገረው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ዓለም አቀፍ ትኩረት ጭምር የሳበ ነበር፡፡ በጦርነት የተነሳ ከፍተኛ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ውድመት መከሰቱ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ በብዙ ቦታዎች መደበኛ እንቅስቃሴና መደበኛ ሕይወትን እያወከ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት ጭምር ተንቀሳቅሶ የመሥራት ዕድል መስተጓጎሉ የሠራተኞችን ኑሮ እንዳከበደው ነው በሰፊው የሚወሳው፡፡
በቅርቡ የዓለም ሠራተኞች ቀንን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዘዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ‹‹ደመወዝ ተከፋዩ ሠራተኛ ኑሮውን መቋቋም አልቻለም፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ምክንያት ደመወዝ ተከፋዩ ሠራተኛ በጣም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለው። ኑሮውን መቋቋም አልቻለም። ግጭት ባለበት ሁሉ የተረጋጋ ሰላም የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፀጥታ መናጋት ችግሮችና አለመግባባቶች ለሠራተኞች ብርቱ አደጋ ደቅነዋል፤›› የሚል ይዘት ያለው ሐሳብ አሰምተዋል፡፡ አንዳንድ አሠሪዎች መብታቸውን የሚጠይቁ ሠራተኞችን ከማባረር ጀምሮ፣ ማስፈራራት፣ ማዋከብና አርቆ መመደብን እንደ ቅጣት እንደሚወስዱ ገልጸዋል። ሠራተኛው በማኅበር እንዳይደራጅ እንደሚከለክሉ፣ እንደ ምንም ቢደራጅም የሠራተኛ ማኅበር መሪዎች ላይ ጫና በመፍጠር የሠራተኞች መሠረታዊ ጥያቄ እንዳይደመጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ካሳሁን ከዚያ ቀደም ብሎ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ከሁሉ በላይ በአገሪቱ በቅርብ ዓመታት የብር የውጭ ምንዛሪ መግዛት አቅም እየተዳከመ መሄዱ፣ የዋጋ ንረቱና ግሽበቱ መጨመሩ የሠራተኛውን ህልውና የሚፈታተን ችግር መደቀኑን ነው ያወሱት፡፡
አምና ሰኔ አካባቢ የዓለም የሠራተኞች ድርጅት (ILO) በኢትዮጵያ አማካይ ወርኃዊ ደመወዝ 3,000 ብር እንደሆነ ይፋ ባደረገው ጥናት አስታውቆ ነበር። ይህ ደግሞ ለመሠረታዊ ፍላጎቶች ከሚያስፈልገው መኖሪያ ደመወዝ (Living Wage) እጅግ ያነሰ መሆኑን ጠቁሞ ነበር። የድርጅቱ የደመወዝ ባለሙያ ጊዮም ዴሎርት ለዶቼቬሌ፣ ‹‹በ2018 በሠራነው ጥናት በኢትዮጵያ የመኖሪያ ደመወዝ በወር 5,000 ብር ገደማ እንደሆነ ደርሰንበታል፡፡ ይህም ሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለመሙላት የሚያስፈልጋቸው የመኖሪያ ደመወዝ ከአማካይ ወርኃዊ ደመወዝ በ2,000 ብር ከፍ ያለ ነው። የመኖሪያ ደመወዝ (Living Wage) የቤት ኪራይ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጓጓዣና የጤና አገልግሎትን የመሳሰሉ የሠራተኞች መሠረታዊ ወጪዎች ተሰልተው የሚሰራ የገቢ መጠን ነው›፤› የሚል አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ አንድ ሠራተኛ የመንግሥትም ይሁን የግል ከወር እስከ ወር ሳይቸገር ለመኖር የሚያስችለው የገቢ መጠን ስንት ነው የሚለው ከባድ ሙግት ሲደረግበት ይታያል፡፡ በአይኤልኦ መስፈርት መሠረት አንድ ሠራተኛ የቤት ኪራይ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የጤና ወይም የትራንስፖርት የመሳሰሉ ወጪዎቹን ሸፍኖ ወር ለመዝለቅ አማካይ ደመወዙ ስንት ቢሆን ይበቃል የሚለው በተቃርኖ የተሞላ ሐሳብ ይሰማበታል፡፡
በኢትዮጵያም ሆነ በአዲስ አበባ ደረጃ ገቢያቸው ዝቅተኛ መሆኑ የሚነገረው የመንግሥት ሠራተኞች፣ በአሁኑ ጊዜ በሚያገኙት ወርኃዊ ገቢ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ለማኖር የሚያስችል አቅም አላቸው ወይ የሚለውም አከራካሪ ነው፡፡ መንግሥት አገሪቱ አሁን በምትገኝበት የኢኮኖሚ ሁኔታ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ለሠራተኛው እያደረገ መሆኑን ቢናገርም፣ የኑሮ ከበደን እሮሮ ግን በብዙ ሠራተኞች ዘንድ ጠንከር ብሎ ይሰማል፡፡ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሚባለውን የሠራተኞች የደመወዝ ወለል ካልወሰኑ አገሮች ተርታ የምትሠለፍ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በግሉ ዘርፍም በሚከፈለን ወርኃዊ ደመወዝ ኑሮን መግፋት ከብዶናል የሚለው የሠራተኞች ብሶት በሰፊው መደመጥ ቀጥሏል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በቅርቡ የጤና ባለሙያዎች የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ ይደረግ የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ በከፊል ሰላማዊ ሠልፍና የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን በተመለከተ አግባብነት የሌለው መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ሚኒስትሯ የሕክምና ባለሙያ በሥነ ምግባር ማገልገልን የሚጠይቅ በመሆኑ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ሥራን ማስተጓጎል ተገቢ አለመሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ባለሙያዎቹ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችና የዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት የሚፈታ መፍትሔ በመንግሥት መቀመጡንና እሱን ተከትሎም በንግግር ችግሩን ለማቅለል መታሰቡን ገልጸው ነበር፡፡
የጤና ሚኒስትር ደኤታው (ዶ/ር) ደረጀ ድጉማ እንደተናገሩት ከሆነ፣ የሐኪሞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ይሻሻልልን የሚል ጥያቄን መሠረት በማድረግ የሥራ ማቆም አድማ መምታት ይቅርታ የሌለው ስህተትና ተቀባይነት የሌለው እንቅስቃሴ ነው፡፡ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ለሐኪሞች እንደ ወንጀል የሚቆጠር መሆኑን በመጥቀስ፣ አስፈላጊ ከሆነ እስከ ሙያ ፈቃድ መንጠቅ ያለ ዕርምጃ መንግሥት እንደሚወስድ ነበር ያሳሰቡት፡፡
የሐኪሞችና የመንግሥት ውዝግብ አይሎ ቢሰነብትም በሒደት ግን መንግሥት ከተለያዩ ዘርፍ ሠራተኞች ጋር ተቀምጦ ንግግር መጀመሩ ተሰምቷል፡፡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በአርትኦት ተከሽነው ከተሠራጩ የስብሰባ ዘገባዎች መታዘብ እንደሚቻለው ከሆነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች ከሰሞኑ ከሐኪሞችም ሆነ ከመምህራን ጋር ባደረጉት ምክክር መንግሥት ጉዳዩን በረጋ ሁኔታና በጥሞና ለመያዝ ፍላጎት ያለው መሆኑን የሚጠቁሙ ስሜቶች ታይተዋል፡፡
የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ዕድል ማግኘት፣ የቤት ኪራይ አበል፣ የትራንስፖርት አቅርቦት፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪና የመሳሰሉ ጉዳዮች በሰፊው የተነሱባቸው የመምህራንና የሐኪሞች ውይይት መድረኮች ከንቲባዋ መልስ ያሉትን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ደመወዝ ብትጨምሩልንም ነጋዴው ዋጋ በማናር መልሶ ይወስድብናልና ባይጨመር ይሻላል ከሚሉ ጠያቂዎች ጀምሮ የቤት ኪራይና የኑሮ ውድነትን መቋቋም አቃተን የሚል ምሬት ያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ ከውይይቱ ቀደም ብሎ ጎበኘናቸው የሚሏቸውን የልማት ሥራዎች አስመልክቶ ከፍተኛ አድናቆት በማንቆርቆር፣ እንዲሁም ለሰብሳቢዎቹና ለመንግሥት ምሥጋና በማስከተል የሚጀምሩት ጠያቂዎች ጎልተው በተደመጡባቸው በእነዚህ የውይይት ዘገባዎች ላይ የሕክምናና የትምህርት ዘርፍ መዋቅራዊ ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው የሚጠይቁ ድምፆችም ሲስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡን እያከምን ነገር ግን ራሳችን መታከሚያ ተቸገርን›› ከሚሉ ጀምሮ ‹‹የምናዋልድባቸው የሕክምና ክፍሎች ጭምር በውኃ አቅርቦት ይቸገራሉ›› እስከሚሉ ጥያቄዎች ድረስ ተደምጠዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ከንግድ ባንክ ጋር ስምምነት በመፈራረም መምህራንና የመንግሥት ሠራተኞች 25 በመቶ ቅድሚያ በመቆጠብ በብድር ቤት የሚያገኙበትን አሠራር መዘርጋቱን አስመልክቶ፣ ‹‹የ25 በመቶ ወጪ በመሸፈን በብድር ቤት ማግኘት መምህሩ አይችልም›› ብለው አሁን ያለውን የመንግሥት ተቀጣሪውን ወርኃዊ ገቢ አቅም ውስንነት የጠቆሙ ጠያቂዎች ሐሳብም ተደምጧል፡፡
ከንቲባ አዳነች በ2014 ዓ.ም. የተደረገውን ወደ 5,000 ቤቶች የማከፋፈል ጥረት ጨምሮ ደመወዝ ጭማሪና ሌሎችም የመንግሥት ሠራተኛውን ሕይወት የሚያሻሽሉ ዕርምጃዎች ስለመወሰዳቸው በምላሻቸው አውስተዋል፡፡ ለመምህራን የራሳቸው ሆስፒታል መሥሪያ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ መንግሥት የሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞች ችግር በየደረጃው የሚያቀሉ ሥራዎች መሥራቱን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እናውራው ካልን እኮ ያለውን የኑሮ ፈተና እናውቀዋለን፡፡ ለመኖር ቤት ኪራይ ከፍላችሁ፣ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር የሚከፈላችሁ ደመወዝ ያንሳል፡፡ ሆኖም ሁሉንም በአንዴ መመለስ አይቻልም፡፡ የጤና ሪፎርም በተባለው ፓኬጅ የተያዘና የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ ዕቅድ አለ፡፡ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ደረጃውንና አከፋፈሉን ለማሻሻል እየተሠራ ነው፤›› የሚል ይዘት ያለው ምላሽ ለጤና ባለሙያዎች ሲሰጡም ተደምጠዋል፡፡
ከንቲባዋ በተለይ የጤና ባለሙያዎች የሥራ አድማ እስከ ማድረግ የደረሰ ዕርምጃ መውሰዳቸውና በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ሚዲያዎች በአንዳንድ ወገኖች ጉዳዩ ጮክ ብሎ መስተጋባቱን የወደዱት አይመስልም ነበር፡፡ በተለይም ከጤና ባለሙያዎች ጋር በተደረገው መድረክ ላይ ይህንኑ ጉዳይ በትኩረት ያነሱ ሲሆን፣ ‹‹የሕዝቡን ብሶት በማቀጣጠል በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመተማመን ለመፍጠር›› ሥራቸው ያደረጉ ኃይሎች መኖራቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ሌላ ሥራ የሌላቸው መሆኑንና የሚዲያ ዘመቻ ማድረግን መተዳደሪያ ገቢ እንዳደረጉት ገልጸዋል፡፡
‹‹የትኛው ችግር ነው ድንገት የተፈጠረው? የቤት ጥያቄ ከጥንት ጀምሮ ነበር፡፡ ቤት ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ቀስ በቀስ ቢያገኙ ዛሬ የሁሉም ይመለስ ነበር፡፡ ብድግ ብሎ በአንድ ቀን ካልተመለሰ ሲባል ከባድ ነው፡፡ ሳይሠራ ለዘመናት የቆየ ውዝፍ ችግርን በቦሌም በባሌም በአንዴ ሥሩት ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ እናንተ ከምትናገሩት በላይ ችግሩን እኔም ማውራት እችላለሁ፡፡ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር አለ፡፡ ጥያቄው ትክክል ቢሆንም የሚመለስበት ሚዛን ግን ያስፈልጋል፡፡ አፍራሽ ኃይሎች አሉ፡፡ እነሱ ችግር ማባባስና ብሶት ማባባስ ነው ሥራቸው፡፡ እነሱ ቢይዙት ኖሮ ጥያቄውን ይመልሱት ነበር? የአዛኝ ቅቤ አንጓች ነገር ካልሆነ በስተቀር የሁሉንም ጥያቄ መመለስ የሚችል አቅም ዛሬ በኢትዮጵያ አለ ወይ?›› በማለትም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አክለውም ፈጣን ልማት በሚያመጡ፣ ኢኮኖሚን በሚያነቃቁ፣ ሰፋፊ የሥራ ዕድል በሚፈጥሩና ሰፊ ተጠቃሚነት በሚፈጥሩ ልማቶች ላይ መንግሥት እየተረባረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ከወዲሁ ውጤት እያመጣ መሆኑን በመጠቆም፣ ከተማዋ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ብዙ ገቢ እያገኘች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ኮንፈረንስ ገቢ ማደግ ዞሮ ዞሮ ለሠራተኛው ነው፡፡ ለእያንዳንዳችሁ ጥቅም ይዞ የመጣ የጋራ ልማት ነው፡፡ የጤና ጉዳይ በመሆኑ የምንውልበትና የምንሠራበት ከተማ ንፁህ መሆን አለበት፡፡ አሁን የምንገኘው ተስፋ የሚያለመልም ምዕራፍ ላይ ነው፤›› የሚል ምላሽ ለሐኪሞቹ ሲሰጡም ተደምጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥሩ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችን ሰብስቦ በወቅቱ አሳሳቢ የኑሮ ችግር ላይ ልምከር የሚል ተነሳሽነት መውሰዱ መልካም መሆኑን፣ ነገር ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙ አስተያየቶች መንግሥት የሠራተኞቹን ብሶት ለማስተናገድ ከዚህ በላይ ርቀት መሄድ እንዳለበት የሚጠቁሙ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡ የውይይት ቪዲዮዎቹ በተሠራጩባቸው የዩቲዩብ ገጾች፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አስተያየት መስጫ ግርጌዎች ላይ ከሚለጠፉ አስተያየቶች ጀምሮ ሀቀኛና ትርጉም ያለው ውይይት ጉዳዩ እንደሚሻ የሚጠይቁ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ ‹‹ካድሬዎች ሰብስቦ ማናገሩንና ውዳሴ ከንቱ ማዳመጡን መንግሥት ያቁም፣ የውይይት መድረኮቹ በቀጥታ በሚዲያ ሊሠራጩ ይገባል፣ እንዲሁም የሠራተኛውን ጥያቄ ለማስታገስ የይስሙላ ውይይት ማድረግ አይጠቅምም›› የሚል ይዘት ያላቸው አስተያየቶችን በተለያዩ መንገዶች ተገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት 230.39 ቢሊዮን ብር ተብሎ የበጀት ዓመቱ ሲጀምር መቅረቡ አይዘነጋም፡፡ በጀቱ በ2016 ዓ.ም. ከተማ አስተዳደሩ ከበጀተው በጀት የ68.3 ቢሊዮን ብር ወይም 42 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑ ተነግሮም ነበር፡፡ ከበጀቱ ውስጥም 146.48 ቢሊዮን ብር ወይም 62 በመቶ ለካፒታል ወጪዎች ማለትም ለመንገድ ልማት 17 ቢሊየን ብር፣ ለቤቶች ልማት 9.1 ቢሊዮን ብር፣ ለአረንጓዴ ልማት 6.7 ቢሊየን ብር እንደተመደበ ነው የተነገረው፡፡ እንዲሁም ለሠራተኛ ደመወዝና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለመደበኛ ወጪዎች በአጠቃላይ 74.55 ቢሊዮን ብር ወይም 38 በመቶ መመደቡም ተመልክቶ ነበር፡፡ ለማዕከል ሴክተሮች 174 ቢሊዮን ብር፣ ለክፍላተ ከተሞች ደግሞ 56.16 ቢሊዮን ብር መመደቡንና በአጠቃላይ ለክፍላተ ከተሞች የተበጀተው ወደ 24 በመቶ ማደጉን የከተማው የበጀት ዕቅድ ሪፖርት ያሳያል፡፡ ከበጀቱ ውስጥ 9.4 ቢሊየን ብር ለመጠባበቂያ ወጪዎች መመደቡንም የከተማ አስተዳደሩ አስታውቆ ነበር፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከታክስ 150.1 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 43.5 ቢሊዮን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች 31.5 ቢሊዮን ብር፣ ከመንገድ ፈንድ 1.2 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከውጭ ዕርዳታና ብድር 3.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም በዚሁ በጀት ዕቅድ ሪፖርቱ ላይ አቅርቦ ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መዲና የምትባለዋ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ትልቅ የሕዝብ ቁጥርና ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለባት ናት፡፡ ከተማዋ በንፅፅር ሰላም የሰፈነባትና በገቢም ራሷን በራሷ የምትችል መሆኑ ይነገራል፡፡ ሞቅ ካለ የንግድ እንቅስቃሴዋ ከምታመነጨው ዳጎስ ያለ ገቢ በተጨማሪ፣ ከፌዴራል መንግሥት ጥቂት ቢሆንም ድጎማ ማግኘቷ መቀጠሉን የአገሪቱ የዘንድሮ በጀት ዕቅድም አመልክቷል፡፡ ለአብነት አዲስ አበባ በፌዴራል መንግሥት ለ2017 ዓ.ም. በቀረበው የበጀት ዕቅድ ሪፖርት መሠረት ለክልሎች ከተመደበው በጀት ውስጥ 5.4 ቢሊዮን ብር እንደምታገኝ ነው የተቀመጠው፡፡
ይህም ሆኖ ግን የከተማው የመንግሥት ሠራተኞች ኑሮ ከበደን ምሬትና ብሶት ከፍተኛ መሆኑ በሰሞነኛ የውይይት መድረኮቹ ላይ ጎልቶ ተሰምቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የመምህራን፣ የሐኪሞችም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ኑሮን የሚያሻሽሉ ድጎማዎችን ማድረጉንና ዕርምጃዎች መውሰዱን ሲናገር ቢደመጥም፣ በአዲስ አበባ የመንግሥት ሠራተኞች በሚያገኙት ገቢ ከወር እስከ ወር መኖር እንደከበዳቸው ማማረራቸው በእነዚህ መድረኮች ተሰምቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አምና ከ2016 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ለተገነባውና 48 ኪሎ ሜትሮች ይሸፍናል ለተባለው ለመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት 33 ቢሊዮን ብር ወጪ ማፍሰሱን አስታውቆ ነበር፡፡ ስምንት ኮሪደሮችና 132 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ሁለተኛው ዙር የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ለመገንባት 40 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡንም ፕሮጀክቶ ይፋ ሲሆን ተነግሯል፡፡ ከንቲባ አዳነች ይህንን መጠነ ሰፊ በጀት የጠየቀ ፕሮጀክት የከተማ ነዋሪውን ሕይወት እያሻሻለ ያለ ልማት መሆኑን የሞገቱ ሲሆን፣ ኮሪደር ልማት ዛሬ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ጭምር በመላ አገሪቱ የሚካሄድ ሰፊ የመንግሥት ፕሮጀክት ሆኗል፡፡
መንግሥት የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በሰፊው እየሠራቸው ያሉ የቱሪስት መሠረተ ልማቶች ሰው ተኮር ልማት መሆናቸውን ሲናገር ቢደመጥም፣ ነገር ግን ከእነዚህ ፕሮጀክቶች በፊት ሊቀድሙ የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ የሚሉ ወገኖች በተቃራኒው ድምፃቸውን ያሰማሉ፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከኮሪደርም ሆነ ከሌላም መሠረተ ልማት የሕዝቡን መሠረታዊ ሕይወት እየተፈታተነ ያለው የገቢና የኑሮ አለመመጣጠን ችግር አንገብጋቢና አጣዳፊ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ከሰሞኑ ከተካሄዱ መድረኮችም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሐኪሞችና በሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ከሚስተጋቡ ብሶቶች ኑሮ ከበደብን የሚለው ምሬት የገዘፈ ቦታ ሲይዝ መታዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ በተለያየ መንገድ በሚስተጋባበት በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሄደ የሚል ዜና መሰማቱ፣ ችግሩ ጎልቶ የሚሰማበት ዕድል ተፈጠረ የሚል ግምት አሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ከንቲባ አዳነችን ሥዕል ሸለሙ መባሉ ፓርቲዎቹን ሲከፋፍልና በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ለከፋ ትችት ሲያጋልጣቸው ነበር፡፡
ሪፖርተር ያናገራቸው አንድ የከተማው ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑ ፖለቲከኛ ግን የውይይት መድረኩ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው፣ መድረኩ በመንግሥት ሚዲያዎች ከተዘገበበት የተለየ ድባብ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ ስለሠራተኞች በተለይም የመንግሥት ተቀጣሪዎች የገጠማቸውን የኑሮ ጫናና የሕዝቡን ህልውና እየተፈታተነ ስላለው የኑሮ ሁኔታ በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ ፓርቲዎች በሚገባ ማንሳታቸውንና መጠየቃቸውን በመጥቀስ፣ ከንቲባዋን ለመሸለም ብቻ ውይይቱ እንዳልተጠራ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡