ዜና
የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ እንደማያስችል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ

ሳሙኤል አባተ

ቀን: June 4, 2025

የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ እንደማያስችል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡ ሪፖርተር በሚቀጥለው ዓመት እንደሚካሄድ በተገለጸው ሰባተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አያስችልም ብለዋል፡፡

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉትና የምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደ ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን ተወዳድሮ ብቻውን የሚያሸንፍበት፣ ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ የከፋው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለምርጫው አስፈላጊው ነገር የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር፣ ፓርቲዎች መዋቅራቸውን መዘርጋት፣ መንቀሳቀስ፣ ታዛቢዎችን ማዘጋጀት ነው፤›› ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹ፓርቲዎች እንደ አማራና ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ውስጥ ተንቀሳቅሰው መሥራት አይደለም፣ በአዲስ አበባ እንኳን መሰብሰብ አልቻሉም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንኳን ምርጫ ማድረግ ማሰብ አይቻልም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የፀጥታ ችግር ትልቁ የምርጫው ሥጋት ነው፡፡ ሕዝብን ሰብስበን ስለፕሮግራማችን ማስረዳት አንችልም፡፡ ጦርነት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ከባድ ይሆናል፤›› ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው፡፡

‹‹ኦፌኮ አገር አቀፍ ፓርቲ እንደ መሆኑ መጠን በሁሉም ቦታዎች የመወዳደር ዕቅድ ነበረን፡፡ ነገር ግን በየቦታው ያሉ ቢሮዎቻችን ተዘግተው እንዴት መወዳደር እንደሚቻል አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡

ሕዝብ የሚፈልገውን መምረጥ የሚችልበት መድረክና ፓርቲዎችም ፖሊሲዎቻቸውን ለመራጩ ሕዝብ ማስተዋወቅ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሌለም ፖለቲከኛው ተናግረዋል፡፡

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነትና የፖለቲካ ውጥረት ውጤታማ ምርጫ ማካሄድ ያስችላል ወይ ለሚለው፣ እኛን ጨምሮ ብዙዎቹን ፓርቲዎች ያሳስባል፡፡ ከምርጫው በፊት የምርጫ ሥርዓት እንዲለወጥ እንፈልጋለን፡፡ ይህንን በተመለከተ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና በሌሎች መድረኮች ጥያቄ ሲቀርብ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የምርጫ ሥርዓቱ እንዲቀየር ስንጠይቅ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት መሻሻልን የሚጠይቅ ነው በመባሉ፣ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት በሚደረጉ ውይይቶች ዕልባት ያገኛል ተብለን እየጠበቅን ነው፤›› ሲሉም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በ7ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከትናንት በስቲያ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የፀጥታ ችግሮች መኖራቸው እንደማይካድ ገልጸዋል፡፡

በመግለጫው ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫውን እንዴት ልታካሂዱ አስባችኋል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የፀጥታ ችግር አለ ተብሎ ይነሳል፣ እውነት ነው የፀጥታ ችግሮች እንዳሉ ልንክድ አንችልም፣ ችግሩ አለ፡፡ ነገር ግን ጊዜው በደረሰ ቁጥር ቦርዱ ምርጫውን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ በሌለበት ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ የሚፎክርበት ሁኔታ የለም፡፡ እኛም እኮ መራጮችና ምርጫ አስፈጻሚዎች አሉን፣ ደኅንነታቸው ያሳስበናል፡፡ የምንልካቸው ዕቃዎች ቦታው ላይ ደርሰዋል ወይ የሚለው ያሳስበናል፡፡ ፓርቲዎችም እንደሚያሳስባቸው እኛንም ያሳስበናል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ልናካሂድ አንችልም ብለን ዛሬ አንቆምም፣ እየተዘጋጀን እንጠብቃለን፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ምርጫን በፀጥታ ምክንያት ማድረግ የማንችል ከሆነ አናደርግም፡፡ ሁኔታዎችን በየምርጫ ክልሉ እየገመገምን በጋራ እየወሰንን እንቀጥላለን፤›› ሲሉም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰባተኛው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡት ሰብሳቢዋ፣ ፓርቲዎች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ቦርዱ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ፓርቲዎች ጽሕፈት ቤቶቻቸው ይዘጋሉ፣ አባላቶቻቸውና መሪዎቻቸው ይታሰራሉ፡፡ ቦርዱ በፓርቲዎች ላይ በተለያዩ አካላት የሚፈጸሙ በደሎችን ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ሲፈታ ቆይቷል፣ በቀጣይም ይህንን ያደርጋል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከምርጫ ሕጉ መቀየርና ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በተያያዘ፣ ‹‹እኛ የምርጫ ሕጉ ከተቀየረ የሚወጣውን ሕግ ለመተግበር ዝግጁ ነን፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የምርጫ ሕግ በየአምስት ዓመቱ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ያንን ለማስፈጸም የምርጫ ዝግጅት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሰባተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫን ለማስፈጸም ቦርዱ ከዚህ በፊት ከነበረው ጠቅላላ ምርጫ ያወጣው ወጪ እጥፍ የሆነ በጀት መጠየቁም ተገልጿል፡፡

ቦርዱ ሰባተኛውን አገራዊ ምርጫ በቀጣዮቹ 11 ወራት ውስጥ ይካሄዳል ብሎ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን፣ የድምፅ መስጫ ቀን በቀጣይ ከምርጫ ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ይገለጻልም ተብሏል፡፡

በመጪው ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡