ዜና
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕግ አግባብን የተከተለ ፍተሻና ብርበራ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: June 4, 2025

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ማክሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሕግ አግባብን የተከተለ ፍተሻና ብርበራ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ኅብረተሰቡ ለፀጥታው ሥራ ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፣ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ሥጋት ላይ የሚጥሉ ወንጀለኞችን አስመልክቶ ለጠቅላይ መምሪያው በደረሱ ጥቆማዎችና በጥናት በለያቸው የሰላምና ፀጥታ ሥጋቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድና ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚያስችል የተጠናከረ ቁጥጥርና ፍተሻ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ደረሱኝ ካላቸው ጥቆማዎችና በጥናት እንደለያቸው ከገለጻቸው ከባድ ወንጀሎች መካከል የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ይገኙበታል።

እነዚህንና ሌሎች የወንጀል ሥጋቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርና አጥፊዎችንና ተባባሪዎቻቸውን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የተጠናከረ ቁጥጥርና ፍተሻ ለማድረግ መዘጋጀቱን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፣ የወንጀል ድርጊቶቹ ይፈጸምባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩና በተለዩ በሁሉም አካባቢዎች የሕግ አግባብን ተከትሎ ፍተሻና ብርበራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ጠቅላይ መምሪያው ያቀደውን ፍተሻና ብርበራ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ባይገልጽም፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተጠናከረ ፍተሻና ብርበራ እንደሚደረግ ተገንዝበው አስፈላጊውን ትብብርና ወንጀል እንዳይፈጸም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ለዚህም ሲባል የከተከማው ነዋሪዎች የተለመደ ጥቆማ የመስጠት ተግባራቸውን በማጠናከር ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።