ቢዝነስ
አሠሪዎች ሠራተኞችና የክልል መንግሥታት መዋጮ የሚያደርጉበት ተጠባቂው የቤቶች ፈንድ

ዳዊት ታዬ

ቀን: June 4, 2025

የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ዕድሳት ሊውል የሚችል የረዥም ጊዜ ብድር አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ የተባሉ ሁለት ተቋማትን ለማቋቋም የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊመከርበት እንደሆነ ተጠቆመ፡፡ በቅርቡም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ የሚጠበቀው ረቂቅ የቤቶች ኮርፖሬሽንና የቤቶች ፈንድን  ለማቋቋም የሚያስችል ነው፡፡ የተረቀቀው አዋጅም የኬንያን የቤቶች ፈንድ ልምድ ተንተርሶ የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል። በኮርፖሬሽኑ የሚተዳደረው ፈንድም ለቤቶች ልማት ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን፣ የቤቶች ፈንድ ዋነኛ ዓላማ የሚሆነው ከተለያዩ ዘርፎች ፋይናንስ ማሰባሰብ ሲሆን፣ ይህንን በፈንዱ የሚሰበሰበውን ፋይናንስ ደግሞ የሚተዳደረው በቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የሚል ስያሜ የሚሰጠው ተቋም እንደሆነ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባዘጋጀው የፋይናንስ ፎርም ላይ የሥራና ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀጋዬ ሞሼ እንደገለጹትም፣ የቤቶች ልማት ፈንዱ የሚሰበሰበው ከተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከሠራተኞችና አሠሪዎች በየወሩ የሚዋጣ መዋጮ አንዱ ሆኖ በረቂቅ አዋጁ ተካትቷል፡፡ 

በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ሠራተኞች ከሚያገኙት ደመወዝ 1.5 በመቶ፣ አሠሪዎችም በተመሳሳይ 1.5 በመቶ ማዋጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን በአጠቃላይ ከሠራተኛውና ከአሠሪው የሚሰበሰበው ሦስት በመቶ ፈንድ ለቤት ልማት ፈንዱ ገቢ የሚደረግ ይሆናል፡፡ 

ለቤቶች ግንባታ የሚል የረዥም ጊዜ ብድር ለማቅረብ ያስችላል ተብሎ የታመነበት ይህ ፈንድ ከሠራተኞችና ከአሠሪዎች ከሚሰበሰበው መዋጮ ባሻገር የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከዓመታዊ ከካፒታል በጀታቸው በቋሚነት በጀት እንዲይዙ በሚያስችል መልኩ ረቂቅ ስለመዘጋጀቱ የአቶ ፀጋዬ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ የፌዴራልና የክልል መንግሥት ከዓመታዊ የካፒታል በጀታቸው እስከ አምስት በመቶ ለቤቶች ፋይናንስ እንዲይዙ የሚል አንቀጽ በረቂቁ መካተቱ ተጠቁሟ፡፡ አቶ ፀጋዬ  እነዚህ ድንጋጌዎች አስገዳጅ ሆነው እንዲሠራባቸው ታሳቢ ተደርጎ ረቂቁ የተሰናዳ ሲሆን፣ ከሠራተኞች ውጭ ያሉ ሌሎች ዜጎች ደግሞ በፈቃደኝነት ከወርኃዊ ገቢያቸው  ሦስት በመቶ ለፈንዱ ማዋጣት ይችላል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚሰበሰበው የቤቶች ፈንድ ለቤት ገንቢዎችና ቤት ለማሳደግ ለሚፈልጉ ዜጎች በረዥም ጊዜ ብድር የሚውል ነው፡፡ እንደሆነ አቶ ፀጋ ማብራሪያ ፈንዱ አቅም ለማጠናከር ታሳቢ የተደረጉ ሌሎች አማራጮችም መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የውጭ የቤቶች ብድር አንዱ ነው፡፡

የሞርጌጅ ብድርን ለማስፋት እንደ አማራጭ የሚወሰደውና ታሳቢ የተደረገው ባንኮች ከዓመታዊ ብድራቸው የተወሰነውን ለቤቶች ፋይናንስ እንዲያውሉ ማድረግ ነው፡፡ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች በኩልም ለፈንዱ ሊኖራቸው የሚገባ አስተዋጽኦ በረቂቁ ውስጥ ስለመመላከቱ አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ ረቂቁን በተመለከተ ከፋይናንስ ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚመከርበት ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ሪፖርተር ባገኘው ተጨማሪ መረጃ ረቂቁ ተጨማሪ ግብዓቶችን ባማከለ በአጭር ጊዜ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዕቅድ መያዙን ነው፡፡

በነዚህ አዋጆች ዙሪያ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው ከተሞች ከሚሰበስቡት ገቢ እስከ አሥር በመቶ የሚደርሰውን ለዚሁ ለቤቶች ፈንድ ፋይናንስ ማጠናከሪያ እንዲውል ታሳቢ ተደርጓል፡፡

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን እየተከታተለ መሆኑን የገለጹት አቶ ፀጋዬ የቤት ልማት ከመንግሥት ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲሸጋገር ለማድረግ እየተሠራበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት የቤቶች ግንባታዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በዚህ አሠራር መንግሥት መሬት በማቅረብ የግል ዘርፉ ደግሞ ፋይናንስና ቴክኖሎጂ በማቅረብ ግንባታዎች እንዲካሄዱ እያደረገ ነው፡፡

ለዘለቄታ ግን የቤቶች ፈንድ በማቋቋም በፈንዱ የሚሰበሰበውን ፈንድ በተለያዩ አማራጮች ለቤት ልማት እንዲውል ማድረግ በመሆኑ የቤቶች ፈንድ ማቋቋምና አስተዳደሩን በተመለከተ በተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ላይ ከባለድርሻዎች ጋር በቅርቡ ውይይት የሚደረግበት ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የፈንድ አስተዳደሩንም በተመለከተ በረቂቁ ውስጥ የተለያዩ አማራጮች የቀረቡ ስለመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ፈንዱ በባንኮች በኩል ሥራ ላይ እንዲውል የሚደረግ ሲሆን፣ ባንኮችም ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ ራሱን የቻለ መስኮት በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሠራር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሊቋቋም የታሰበው የቤቶች ፈንድ ኮርፖሬሽን ረቂቅ ሕግ የኬንያን ድንጋጌ መሠረት ስለማድረጉ ተደጋግሞ የተገለጸ ሲሆን፣ የኬንያ ቤቶች ልማት ፈንድ አስገዳጅ ሕግ በ2004 የፀደቀ ነው፡፡ ሠራተኞች አሠሪዎች በግዴታ ለፈንዱ ማውጣት እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡

ለቤቶች ልማት ፈንድ ከሠራተኞች ተቆርጦ ለፈንዱ እንዲውል የተደነገገው የደመወዛቸውን 1.5 በመቶ ሲሆን ከአሠሪውም በተመሳሳይ 1.5 በመቶ እንዲያወጣ የሚያስገድድ ነው፡፡

ይህንን ፈንድ የሚያሳስበውም የኬንያ ገቢዎች ቢሮ እንደሚሆን የሚያመለክተው ይህ የኬንያ ሕግ በአዋጁ በተደነገገው መሠረት ወርኃዊ ክፍያን ያልፈጸመ በየወሩ ሦስት በመቶ ቅጣት ይጣልበታልም ይላል፡፡

የኬንያ ቤቶች ልማት ፈንድ የሚተዳደረው ደግሞ ለዚሁ ሥራ በተቋቋመ ሲሆን አፈጻጸሙን ይከተታል፡፡ ፈንዱ ሥራ ከጀመረ በኋላ በየዓመቱ 250,000 ቤቶችን ለመገንባት ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚሰበሰበው ፈንድ የቤቶች ግንባታዎችን ከማከናወን ባሻገር ለሥራ ዕድል ፈራም እንደሚያግዝ ያመለክታል፡፡ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ስለመሆኑ ድንጋጌው የፈንዱን ጠቀሜታ በተመለከተ ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል ተካቷል፡፡

በኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ፈንድ ለማቋቋምና ፈንዱን የማስተዳደር ዙሪያ የተጠቆመው ፈንዱ የቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በሚል ስያሜ በሚጠቀሰው አካል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የጎህ ቤቶች ባንክ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ፀጋዬ ለቤቶች ልማት የሚል ፋይናንስ ለማግኘት ራሱን የቻለ የቤቶች ፈንድ ለማቋቋም መወሰኑንና ለዚህም ረቂቅ መዘጋጀቱ ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከስድስት ሚሊዮን በላይ የቤት ፍላጎት ባለበት አገር ውስጥ እንዲህ ያለ ፈንድ ተቋቁሞ መሥራት ካልተቻለ የቤት ችግርን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማቃለል አይቻልም ይላሉ፡፡ ሆኖም የቤቶች ልማት የሚለውን ፋይናንስ የማስተዳደሩ ሥራና ፈንዱ በብድር መልክ ለተጠቃሚ እንዴት መድረስ አለበት የሚለው ጉዳይ ግን ግልጽ መሆን አለበት፡፡

በቤቶች ፋይናንስ ዙሪያ በተደረገው ውይይት መገንዘብ የቻልኩት የፈንዱ ከብሔራዊ ባንክ ውጪ ባለአካል የሚተዳደር መሆኑን ነው ያሉት እኚህ ባለሙያ ይህንን ሐሳብ የማይደግፉት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ፈንዱ ፋይናንስ ነው›› ያሉት እኚሁ ባለሙያ ፋይናንስ ከሆነ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን መሥራት ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ፈንዱ በባንኮች በኩል ሥራ ላይ ይውላል ከተባለ ደግሞ ለባንኮች የተሰጠው ገንዘብ በአግባቡ ለተባለው ዓላማ መዋል አለመዋሉን፣ እንዲሁም በአግባቡ ስለመመለሱ ማረጋገጥና የመቆጣጠር ሥራው የብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ልምዶችም የሚያሳዩት ይህንን በመሆኑ፣ በዚሁ አግባብ ረቂቁ ቢዘጋጅ ተመራጭ ይሆናል ይላሉ፡፡ ለፈንዱ የሚውሉ መዋጮዎች ወይም ገቢዎች መካከል አንዱ ከአሠሪና ሠራተኞች ላይ ተቆራጭ እንዲሆን በረቂቁ ላይ መካተቱ አግባብ ቢሆንም ይህ መዋጮ አሠሪውና ሠራተኛው ላይ ጫና የሚፈጥር መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሕግ ለጡረታ ሠራተኞች ሰባት በመቶ አሠሪዎች ደግሞ አሥራ አንድ በመቶ የሚያዋጡ በመሆኑ በዚህ ላይ በተጨማሪነት ለቤት ልማት ፈንድ ሦስት በመቶ ከተጨመረበት ከታክስና ከጡረታ ተቆራጭ ሌላ ተጨማሪ ተቆራጭ የሚታከል ከሆነ አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ምን ያህል ተቀባይነት ያገኛል? የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ፣ ለቤቶች ልማት ፈንድ ከሠራተኞችና ከአሠሪዎች እንዲዋጣ የሚፈለገው ገንዘብ ለጡረታ እየተዋጣ ባለው መዋጮ ውስጥ አብሮ ቢካተት የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሁለቱም ወገን ለጡረታ ከሚሰበሰበው 18 በመቶ ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት በመቶው ለታሰበው የቤቶች ልማት ፈንዱ እንዲገባ ማድረግ የተሻለ መሆኑንም ይመክራሉ፡፡ 

የተሻለ አማራጭ የሚሆነው ግን ለቤቶች ልማት የሚውሉ በአነስተኛ ወለድ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ብድሮች ያሉ በመሆኑ እንዲህ ያሉ አማራጮች ላይ ማተኮር እንደሚሻል ጠቁመዋል፡፡ በተለይ አሁን ያለውን የቤት ችግር ወደፊትም ፍላጎቱ እያደገ ስለሚመጣ መንግሥት ከዓመታዊ በጀቱ ለዚህ ፈንድ ቋሚ በጀት መመደብ ይኖርበታል፡፡ 

አሁን ተሰናድቷል በተባለው ረቂቅ ሕግ መንግሥት ከዓመታዊ በጀቱ ቋሚ በጀት እንዲመድብ በረቂቁ ተካቷል መባሉ የሚደገፍና የሚበረታታ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

በፎረሙ ላይ ተሳታፊዎች ከተጠቀሱት አስተያየቶች ውስጥ የቤቶች ልማትን በተመለከተ አለ ተብሎ የሚጠቀሰው የፋይናንስ እጥረት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡

ስለቤቶች ልማት ሲነሳ ፋይናንስ ቢገኝ እንኳን የገንቢዎች የመፈጸም አቅም መታሰብ እንደሚኖርበትም ተጠቅሷል፡፡ የሚኒስቴሩ መረጃ ግን ፈንዱን ያስተዳድራል የተባለው ኮርፖሬሽን ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚያደርግበት የሚሆንና ይህንንም በዝርዝር የሚያመለክት ድንጋጌ እንደሚኖር የሚጠቁም ነው፡፡ የአቶ ግሩም ሐሳብ ግን ፈንዱ በቀጥታ በኢትዮጵያ ብሔራ ባንክ ቢተዳደር የሚል ነው፡፡

በቤት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር ለማመቻት እንዲቋቋም የሚደረገው ፈንድ ታሳቢ ያደረገው ቤት ግንባታን ብቻ አይደለም፡፡

ለቤት ዕድሳት የሚል ብድርንም መስጠት ታሳቢ አድርጓል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ቤቶች ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደረጃ በታች በመሆናቸው ፈንዱ የቤት ዕደሳት ብድርን እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ በረቂቁ ውስጥ ስለመካተቱ ተመልክቷል፡፡ የቤት ልማትን ለማስፋት ሌሎች አማራጮችም እየተተገበሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በማኅበር ተደራጅቶ ግንባታ ማካሄድ አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባንኮች የረዥም ጊዜ ብድር ለመስጠት የሚያስችላቸው ሁኔታ በጣም ጠባብ በመሆኑ የሞርጌጅ ብድር እጅግ አነስተኛ ድርሻ ያለው ሆኗል፡፡

ለሞርጌጅ ከሚሰጠው ብድር ውስጥ አብዛኛው እዚያው የባንክ ሠራተኞች ጋር የሚቀር ስለመሆኑ በውይይት መድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የሞርጌጅ ብድርን በተመለከተ በመድረኩ እንደተጠቀሰውም በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚጥ ብድር የሞርጌጅ ድርሻ 0.38 በመቶ ነው፡፡ ይህ ከአፍሪካ አማካይ የሞርጌጅ ብድር አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ በአፍሪካ የሞርጌጅ ምጣኔ ሦስት በመቶ ነው፡፡