

ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነርና አቶ አህመድ ሺዴ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር በፎረሙ ላይ በተሳተፉበት ወቅት
ቢዝነስ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ
ቀን: June 4, 2025
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍን በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሊደረግ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የኢትዮ ቤልጂየም ቢዝነስ ፎረም ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ፣ የኢትዮጵያ ‹‹የኢንቨስትመንት አቅም›› በሚል ርዕስ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተዘጋጀ ጽሑፍ የኮሚሽኑ አማካሪ ያቀረቡት አቶ ዳዊት ፈለቀ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
አገሪቱ ያካሄደቻቸውን የኢኮኖሚ ለውጦችና ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ከታቀዱ ዘርፎች በአዋጅ ቁጥር 1360/2017 መሠረት የባንክ ዘርፍ አንደኛው መሆኑንና ይህም በጋራ ለመሥራት፣ ቅርንጫፎች ለመክፈት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ እንዲኖራቸው እንደሚፈቅድ ተገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት ከተደረጉ የኢኮኖሚ ለውጦች መሀል ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ አሠራር አንዱ መሆኑን፣ በተጨማሪም ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተፈቅዶ የቆየው የንግድ ዘርፍ መከፈቱን አቶ ዳዊት በጽሑፍ አስታውሰዋል፡፡ በቅርቡ ክፍት ከሚደረጉ ዘርፎች መካከልም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሎጂስቲክስ ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የሕግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን በኮሚሽኑ በተዘጋጀው ጽሑፍ የተጠቆመ ሲሆን፣ መቼ ተግባራዊ ይደረጋል ለሚለው ጥያቄም ‹‹በቅርብ ጊዜ›› ውስጥ ተብሏል፡፡
መንግሥት ከዚህ ቀደም በሎጂስቲክስ ዘርፍ 49 በመቶ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ ሕግ ያወጣ ቢሆንም፣ ከአይኤምኤፍ ጋር በተደረገው ስምምነት እ.ኤ.አ. እስከ 2026 በዘርፉ ሙሉ በሙሉ የውጭ ባለሀብቶች ገብተው እንዲሠሩ ተፈቅዷል፡፡
በፎረሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የአዋጅና የመመርያ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸው፣ ይህም አገሪቱን ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል፡፡
የቤልጂየም ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በመሠረተ ልማት ዘርፎች መሰማራታቸውን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ በየዓመቱ 12 በመቶ እየጨመረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፣ መንግሥት የቤልጂየም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ ድጋፉን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገቻቸው ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የቤልጂየም ኢንቨስተሮች በትክክለኛው ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ብለዋል፡፡
ለሁለት ቀናት የሚቆየው የኢትዮ ቤልጂየም ቢዝነስ ፎረም የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ አሥር በጨርቃ ጨርቅ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፕላስቲክና በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች መሳተፍ የሚፈልጉ የቤልጂየም ባለሀብቶች ስምምነቶችን እንደተፈራረሙ ተነግሯል፡፡