

ማኅበራዊበአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችንና የሕክምና መሣሪያዎችን ከውጭ መግዛት በሕግ ተከለከለ
ቀን: June 4, 2025
መድኃኒቶች ወይም የሕክምና መሣሪያዎች በአገር ውስጥ አምራቾች የሚመረቱ ከሆነ በዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ከውጭ ግዥ መፈጸም ተከለከለ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በማዕከል የሚፈጸሙ የመድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎች የግዥ አፈጻጸም መመርያ ይፋ አድርጓል፡፡
ከትናንት ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ በሚሆነው መመርያ መድኃኒት ወይም የሕክምና መሣሪያ በአገር ውስጥ አምራቾች የሚመረት ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ግዥ መፈጸም እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡
መድኃኒቱ ወይም የሕክምና መሣሪያው በአገር ውስጥ አምራቾች የማይመረትም ቢሆን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ከሆነም፣ ከውጭ መግዛት እንደማይቻል መመርያው ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የአገር ውስጥ አምራቾች አቅም በቂ አለመሆኑ ወይም ግዥው በዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ መፈጸሙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ማስገኘቱ ሲረጋገጥ፣ ሊፈቀድ እንደሚችል መመርያው ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም የውጭ አገር ተጫራቾች ካልተሳተፉበት ውጤታማ እንደማይሆን ከታመነ እንደሚፈቀድ ያብራራል፡፡
በአገር ውስጥ የማይመረቱ መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎችን ከውጭ ለመግዛት የጨረታ ጥሪ ማስታወቂያውም ሆነ ሰነዱ የሚዘጋጀው በእንግሊዝኛ ቋንቋ መሆን እንዳለበት የሚደነግገው መመርያው፣ የጨረታ ጥሪው ከመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት በተጨማሪ በለጋሽ ወይም በልማት አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ከሆነ የድጋፍ ሰጪው አካል አሠራር በተከተለ መንገድ ሊደረግ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
የውጭ አገር ተጫራቾች የሚያቀርቡት የመጫረቻ ዋጋና የጨረታ ማስከበሪያ ዓለም አቀፍ ንግድ በሚሠራበት ገንዘብ ዓይነት ሊሆን እንደሚገባ፣ ነገር ግን በአገር ውስጥ የሚጠቀሙት አገልግሎት ወይም ግብዓት በሚኖርበት ጊዜ የሚከፈላቸው ክፍያ በብር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተጫራቾች መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያ ከውጭ ግዥ ለመፈጸም በግልጽ ጨረታ ሲወዳደሩ መድኃኒቱ ወይም የሕክምና መሣሪያው ከሚጫንበት አንስቶ እስከ አገልግሎቱ መጋዘን ለማድርስ የሚከፈሉ የታክስና የቀረጥ፣ የኢንሹራንስና የማጓጓዣ ወጪዎችን እንደ አስፈላጊነቱ በማካተት ውድድሩ እዲፈጸም ሊደረግ እንደሚገባ በመመርያው ተብራርቷል፡፡
በጨረታው ለመሳተፍም የውጭ አገር ተጫራቾች ከአጠቃላይ ዋጋቸው ውስጥ በውጭ ምንዛሪና በብር ሊከፈላቸው የሚገባውን መጠን በሚያቀርቡት የመጫረቻ ሰነድ በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚኖርባቸው፣ እንዲሁም በአፈጻጸም ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶች በኢትዮጵያ ሕግ እንደሚሆን በመመርያው ተደንግጓል፡፡
ከግዥ አስተዳደር ዘርፍ የሚቀርብለትን የጨረታ ግምገማ ሪፖርት መርምሮ የሚያፀድቅ የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴ እንደሚቋቋምና ኮሚቴው ሦስት አባላት እንደሚኖሩት፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኮሚቴውን እንደሚያቋቁሙትና ከሦስት ዓመት ያልበለጠ የአገልግሎት ዘመን እንደሚኖረው በመመርያው ተመላክቷል፡፡