
4 ሰኔ 2025
ላለፉት አራት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ተሰማ “ከእስር እንዲፈቱ” የሚያስችል ስምምነት በክልሉ መንግሥት እና በተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) መካከል መፈረሙ ተገለጸ።
በሁለቱ አካላት ስምምነት መሠረት አቶ ዮሐንስ ከእስር የሚፈቱት ሌሎች መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦች ትግበራ ሂደት ከታየበት በኋላ እንደሆነ ቦዴፓ እና ከአደራዳሪዎቹ አንዱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት እና ባለፉት ወራት ከክልሉ መንግሥት ጋር መካረር ውስጥ በገባው ቦዴፓ መካከል ንግግር የተካሄደው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ግንቦት 20 እና ሐሙስ ግንቦት 21/2017 ዓ.ም. እንደሆነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሰቢ አቶ ሰለሞን አየለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ንግግሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን፣ ምክትላቸው አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ የክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች የተገኙበት እንደሆነ አቶ ሰለሞን እና የቦዴፓ ሊቀመንበር አቶ አመንቴ ገሺ ተናግረዋል።
ቦዴፓ ደግሞ በሊቀመንበሩ አቶ አመንቴ ገሺ፣ በፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ እና የፓርላማ አባል ዶ/ር መብራቱ አለሙ እንዲሁም ሌሎች ሥራ አስፈጻሚ አባላት እንደተወከለ ተነግሯል።
ሁለቱን አካላት ለማነጋገር የቀረቡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፣ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማስተባበሪያ ማዕከል ሚኒስትር አቶ መለስ አለሙ እንዲሁም አቶ ሰለሞን ናቸው።
ሁለቱን አካላት የማደራደር ተግባር ተከናወነው በቦዴታ እና በክልሉ መንግሥት መካከል የተፈጠረውን “አለመግባባትን” በተመለከተ ለምርጫ ቦርድ እና ለፖቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቅሬታ ከቀረበ በኋላ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
አቶ ሰለሞን ከጠቀሷቸው አለመግባባት የፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እና የክልሉ ምክር ቤት አቶ ዮሐንስ መታሰር ይገኝበታል።
በየካቲት መጨረሻ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የታሰሩት የምክር ቤት አባሉ፤ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያነሳሳ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት እና መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከሚጥሩ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
አቶ ዮሐንስ የታሰሩት ከሌሎች ሁለት የቦዴፓ አመራር የሆኑ የምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን የክልሉ ምክር ቤት የጸቀደቁ የሕገ መንግሥት እና አዋጅ ማሻሻያዎች እንዲታገዱ እና ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አቤቱታ ካቀረቡ ከቀናት በኋላ ነበር።
አቶ ዮሐንስ ከታሰሩ ከሳምንት በኋላ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላም በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ አንስቶ ግን አቶ ዮሐንስ ላይ የተከፈተው መዝገብ አልተንቀሳቀሰም።
አቶ ዮሐንስ በሚያዝያ መጨረሻ ተቀጥሮ በነበረ የፍርድ ቤት ውሎ ላይ ሳይቀርቡ ቀናት ማለፉን ተከትሎ በድጋሚ ፍርድ ቤት ለመገኘት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይሁንና የምክር ቤቱ በ2012 ዓ.ም. ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበውበት የነበረ እና በነጻ የተለቀቁበት “የሊዝ መሬትን ያላግባብ የመያዝ” ክስ በድጋሚ ተቀስቅሶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል። ከአቶ ዮሐንስ ባሻገር ሌሎች የፓርቲው አመራር እና አባላት ታስረው ተለቅቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገው ንግግር ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት እና የቦዴፓ አመራሮችን ካከራከሩ ጉዳዮች መካከል “የአቶ ዮሐንስ ክስ ሕጋዊ ነው ፖለቲካዊ” የሚለው አንዱ እንደነበር አቶ አመንቴ እና አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
አቶ አመንቴ እንደሚናገሩት እሳቸው እና ቦዴፓን የወከሉ አመራሮች፤ አቶ ዮሐንስ “የፖለቲካ እስረኛ ስለሆነ ወደ ንግግር የምንገባው እሱን ያለቅድመ ሁኔታ ከፈታችሁ ነው” የሚል አቋም ይዘው እንደነበር አስረድተዋል።
የምክር ቤት አባሉ የታሰሩት “በፍትህ ጥያቄ” እንደሆነ የተከራከሩት የመንግሥት አመራሮች በበኩላቸው፤ “በሕግ የተጀመረው ጉዳይ በሕግ ማለቅ አለበት” የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
“በእኛ በኩል የነበረው ትልቁ ዕይታ ሁለቱንም ለማቀራረብ ነው” ያሉት አቶ ሰለሞን ሁለቱም አካላት “ከጥቃቅን ነገሮች ይልቅ የሕዝቦችን መስተጋብር የሚያስተሳስር እና ትልቅ ለውጥ ሚያመጡ” ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉን አስረድተዋል።
“በውይይት እየፈታን፣ እያነጋገርን፣ እነሱም እየተግባቡ ሲመጡ ወደ ስምምነት ሊገባ ችሏል” ብለዋል። በዚህም እስከ ረቡዕ ዕለት የዘለቀ ንግግር ከተደረገ በኋላ በተደረሰው መግባባት መሠረት በማግስቱ ሁለቱም አካላት ዘጠኝ ነጥቦችን የያዘ የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል በክልሉ ያለውን “የፖለቲካ ምኅዳር ከፍረጃ፣ ከወቀሳ እና ከክስ ነጻ ማድረስ” እንዲሁም “የፓርቲ ስምሪቶች አንዱ ፓርቲ ሌላውን ፓርቲ ከመውቀስ እንዲታቀብ” የሚሉት እንደሚገኙበት የቦዴፓ ሊቀ መንበሩ አቶ አመንቴ ተናግረዋል።
“የእኛ አካባቢ የፀጥታ ስጋት የበዛበት አካባቢ ነው። ይህንን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ብዝሃ ማኅበረሰብ የሚኖርበትም ስለሆነ እርሱንም ግምት ውስጥ ያስገባ የሚዲያ አጠቃቀም ይኑር” በሚልም በሁለቱም አካል መካል የሚታየውን “የሚዲያ አጠቃቀም ችግር” ለመፍታት ስምምነት ላይ መደረሱን አንስተዋል።
በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት እና ቦዴፓ በጋራ በመሆን እስከታች ድረስ የሚወርዱ የሕዝብ መድረኮችን ለማዘጋጀት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
በስምምነት ሰነዱ ላይ ተቀመጠው ዘጠነኛ ነጥብ በእስር ላይ የሚገኙትን የምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ተሰማን የሚመለከት እንደሆነ አቶ ሰለሞን እና አቶ አመንቴ ተናግረዋል።
አቶ አመንቴ እንዳሉት የምክር ቤት አባሉን መፈታት በተመለከተ በክልሉ መንግሥት በኩል የነበረው አቋም “ከፖለቲካ እና ዲሞክራታይዜሽን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን እየፈታን፣ ለውጥ እያየን፤ ለፕሮግረሳችን ጠቃሚ ሆኖ ካገኘነው እንፈታዋለን” የሚል ነበር።
በዚህ ወቅት አደራዳሪዎቸ “የሁለቱምን አቋም ወደ መሃል በማምጣት”፤ ” ይሄ ሰው የፖለቲካ ነው፣ የሕግ እስረኛ ነው የሚለውን በዚህ ሰዓት መወሰን ይከብደናል፤ ነገር ግን ቅን ልቦና ካለ ቢያንስ አንድ ሁለት ፕሮግረሶችን አይታችሁ፤ አንድ ሁለት መድረኮችን አይታችሁ እንዲፈታ አድርጉ” በሚል እንዲግባቡ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
ይህ ክርክር መደረጉን የሚያረጋግጡት አቶ ሰለሞን፤ “የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውም ካሉ በድርድር፣ በንግግር መፍታት እንዲችሉ፣ አብረው ለሕዝብ እንዲሠሩ የሚሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ችለዋል። ቀጥሎ አቶ ዮሐንስ የሚፈቱበት ሂደት ይፈጠራል ማለት ነው” ሲሉ የምክር ቤት አባሉን በተመለከተ መግባባት የተደረሰበትን ነጥብ አንስተዋል።
የቦዴፓ ሊቀመንበር አቶ አመንቴ እንደሚገልጹት ስምምነት ተደረሰባቸው ነጥቦች “በተወሰነ መጠን መተግበራቸው” አቶ ዮሐንስ ለመፍታት የተቀመጠ “ቅድመ ሁኔታ” ነው።
“የፖለቲካ ሁኔታውን ማስከን፣ በሁለቱ መካከል ያለውን ውጥረት መቀነስ፣ የጥላቻ ሁኔታዎችን ማስተካከል፣ ውዝግቦች አሉ እነሱን መቀነስ፣ የሚዲያ አጠቃቀሙን ማስተካል፣ የአባላት ሥነ ምግባርን ማስተካለል እነዚህ ሁኔታዎች እንደ ቅደመ ሁኔታዎች ሆነዋል ማለት ነው” ብለዋል።
እነዚህ ተግባራት የሚፈጸሙት ግልጽ የጊዜ ገደብ አለመቀመጡን የሚናገሩት አቶ አመንቴ፤ “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ለማከናወን ግን መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
“አጭር ጊዜ ማለት በእኛ መረዳት፣ በነበረው ንግግር ሳምንት ሁለት ሳምንት ብለን ነው ያነሳነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጡን እንገመግማለን ነው የተባለው” በማለት አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት እና ቦዴፓ የስምምነቱን ትግበራ በተመለከተ ለአደራዳሪዎቹ ሪፖርት እንደሚያቀርቡም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ስለ ተፈረመው ስምምነቱን ከክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን፣ ምክትላቸው አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ ሌላኛው ተደራዳሪ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሀሩን ኡመር እና ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መለስ በየነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።