
ከ 5 ሰአት በፊት
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝሮችን ይዟል።
በርካቶች የኬንያ መንግሥትን እና ባለሥልጣናትን በመገዳደር በደፋርነቱ የሚያውቁት ኬንያዊው ተሟጋች ቦኒፌስ ምዋንጊ በታንዛኒያ ወሲባዊ ስቅይቶች እንደተፈጸሙበት ለቢቢሲ ተናገረ።
በታንዛኒያ ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በደረሰበት እንግልት እና ወሲባዊ ጥቃቶች “ለመኖር እየታገልኩ ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“የተለያያዩ ቁሶችን ጭምር በመጠቀም አጸያፊ ተግባር መፈጸማቸው አሳፋሪ እና አሳዛኝ” መሆኑን የገለጸው ቦኒፌስ ዝም እንደማያሰኙት እና “የደረሰብኝን ስቃይ ለመናገር ወስኛለሁ” ብሏል።
ቦኒፌስ ወደ ታንዛኒያ ያቀናው በእስር ላይ ለሚገኘው ታንዛኒያዊው የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቱንዲ ሉሱ አጋርነቱን ለማሳየት ነበር።
በታንዛኒያ ከደረሰ በኋላም በቁጥጥር ስር መዋሉንም ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ከታሰረ በኋላም እርቃኑን እንዲቀር አድርገው፣ እጁ እና እግሩን አስረው፣ ተገልብጦ (ወፌ ላላ) ውስጥ እግሩን እንደገረፉት በናይሮቢ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እንባው እያዘራ ተናግሯል።
በመቀመጫው በኩል የተለያዩ ቁሶችን እንዲሁም አንደኛው እጁን በመጠቀም የተለያዩ ወሲባዊ ጥቃቶችን እንዳደረሰቡት ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ እና እያለቀሰ ለጋዜጠኞች አስረድቷል።
በወቅቱም ቪዲዮ እንደቀረጹት ገልጿል።
የታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም የፖሊስ ኃላፊ ቦኒፌስ የሰጠውን ምስክርነት ያልተቀበሉት ሲሆን፣ ክሱ ከአክቲቪስቶች የሚመጣ “አስተያየቶች” እና “የሰሚ ሰሚ” ነው ሲሉ ለቢበሲ ተናግረዋል።
“እዚህ ቢሆኑ ኖሮ፤ ምን እያሉ እንደሆነ እጠይቃቸው ነበር። በሕግ እነዚህ ነገሮች የሰሚ ሰሚ ወይም የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ይባላሉ” ሲሉ ጁማኔ ሙሊሮ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም ቦኒፌስ ምርመራ እንዲካሄድ ለባለሥልጣናት ሪፖርት ማድረግ አለበትም ብለዋል።
የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሑ ሐሰን አስተዳደር በቀጣይ ዓመት የሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ አፋኝነቱ መጠናከሩን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይከሳሉ።
የቀጣናው የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የታንዛኒያ ባለሥልጣናት በተሟጋቾቹ ላይ “ኢሰብዓዊ” ጥቃቶችን የፈጸሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ ሊያደርጉ ይገባል ሲል አሳስቧል።
ቦኒፌስ ከኡጋንዳዋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አጋታ አቱሃይሬ ጋር የታንዛኒያ ባለሥልጣናት ለቀናት አስረዋቸው እንደነበር ገልጿል።
አጋታ ቀደም ብሎ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ በታንዛኒያ ታስራ በነበረበት ወቅት መደፈሯን ተናግራለች። አጋታ፣ ባለፈው ሰኞ ናይሮቢ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገኝታ ነበር።
በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ቦኒፌስ በታንዛኒያ እስር ቤት የደረሰበትን በዝርዝር ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
ቦኒፌስ፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ በቁሶች በሚደፍሩት ወቅት የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ስም እየጠሩ በስዋሂሊ ቋንቋ “አሳንቴ” (አመሰግናለሁ) እንዲል ያስገድዱት እንደነበር እያነባ እና እየተንዘፈዘፈ ነው የገለጸው።
ፖሊሶቹ ሁሉንም ነገር እየቀረጹ እንደሆነ እና ስላጋጠመው ነገር ትንፍሽ የሚል ከሆነ ቪዲዮውን “እንለቀዋለን” በሚል እንዳስፈራሩት አክሎ ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ለቢቢሲ ኒውስደይ ፕሮግራም የደረሰበትን ስቅይት እና እንግልት ለአእምሮ ጭንቀት እንደዳረገው ነው የተናገረው።
“ብዙ ቅዠቶች፣ ብዙ ሃሳቦች አሉኝ። በጨለማ ውስጥ ብቻዬን ሆኜ እንደምገደል ሳስብ ነበር። ያ ሁሉ ሰቆቃ ከእኔ ጋር የሚኖር ነው” ይላል።

ቦኒፌስ የህክምና ሰነዶቹ በሙሉ ይፋ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ የተናገረ ሲሆን፣ ይህም “በእኔ ላይ የደረሰው በሌላ ላይ በፍጹም እንዳይደርስ” በሚል ነው።
“መላ ሰውነቴ ቆስሏል፤ የውስጥ አካሌ፣ ብልቶቼ ቆስለዋል፤ እግሬ ቆስሏል፤ ሁለት የእግር ጣቶቼ ተሰብረዋል። ስብራት በብዙ ቦታ አለ። እና አሁንም እየታገልኩ ነው” ሲል አክሏል።
ቦኒፌስ እና አጋታ በአገር ክህደት ወንጀል ለተከሰሰው ታንዛኒያዊው ተቃዋሚ ሊሱ አጋርነታቸውን ለማሳየት ወደ ታንዛኒያ ከተጓዙት በርካታ የመብት ተሟጋቾች መካከል ናቸው።
ሊሱ የቀረበበትን ክስ የማይቀበል ሲሆን፣ ቦኒፌስ እና አጋታም ከሁለት ሳምንት በፊት ወደዚያ ሲጓዙ በፍርድ ሂደቱ ላይ ለመገኘት ነበር።
ሊሱ አገሪቱ ያላት ሕግ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ የማይፈቅድ በመሆኑ ስር ነቀል ለውጥ ሊደረግበት ይገባል በማለት ሲሟገት ቆይቷል። የታንዛኒያ መንግሥት ግን ይህንን አይቀበለውም።
ሊሱ “ተሃድሶ ከሌለ፤ ምርጫ የለም” በሚል የድጋፍ ሰልፍ ማድረጉን ተከትሎ ከወራት በፊት፣ ሚያዝያ ላይ ነበር ለእስር ተዳረገው።
ቦኒፌስ እና አጋሮቹ ወደ ታንዛኒያ የሄዱት ሊሱ ላይ የቀረበውን “የማይረባ ክስ” ለማጉላት እንደሆነ ለቢቢሲ የገለጸው ቦኒፌስ፣ ይህም በታንዛኒያ ባለሥልጣናት “በቀላሉ አልታየም” ይላል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ከጎረቤት አገራት የመጡ አክቲቭስቶች በታንዛኒያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይፈቅዱ በወቅቱ አስጠንቅቀዋል።
ቦኒፌስ እና አጋታ በታንዛኒያ ታስረው በነበረበት ወቅት የነበሩበት ስፍራ አለመታወቁ በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሎ ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ቦኒፌስ “ታፍኖ የተወሰደው” በጣም ታዋቂ ከሆነ ሆቴል መሆኑን ጠቅሶ፣ ሁኔታውን በጣም አስደንጋጭ እና “ማን አለብኝነት ያለበት” ነው ይላል።
“በጠራራ ፀሐይ ታፍኜ ተወስጄ የት እንዳለሁ ሳይታወቅ ስቃይ እና እንግልት ተፈጽሞብኛል። ይህ ማለት የታንዛኒያ መንግሥት ሰዎች ስለ ጉዳዩ ምንም ቢያስቡ ግድ የለውም ማለት ነው” ሲል ነው ቦኒፌስ ለቢቢሲ የተናገረው።
አጋታ በበኩሏ አገሯ ኡጋንዳ “ፈላጭ ቆራጭ ብትሆንም” ከዚህ የከፋ የውጭ አገር፤ “የባሰ መንግሥት አገኛለሁ” ብላ እንዳላሰበች ተናግራለች።
ቦኒፌስ ይህ ስቅይት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሥርዓት “ምን ያህል እንደተንኮታኮተ” የሚያሳይ ነው ይላል።
“ይህ ትግል የበለጠ ፓን አፍሪካዊ ያደርገኛል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ሁለቱ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተፈጸመው የከፋ አያያዝ ሪፖርት በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል።
አጋታ በመሥሪያ ቤቱ “የ2024 ዓለም አቀፍ ደፋር ሴት” ሽልማት እውቅና እንዳገኘች ጠቅሷል።
የኬንያ የቀድሞ የፍትህ ሚኒስትር ማርታ ካሩዋ እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊ ሙቱንጋን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ወደ ታንዛኒያ አቅንተው የነበረ ቢሆንም፤ ዳሬሰላም አየር ማረፊያ ሲደርሱ ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ ተከልክለው ተባርረዋል።