የጉዞ እገዳ ተቃውሞ

ከ 4 ሰአት በፊት

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤርትራን ጨምሮ የ12 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ የሚከለክለውን አዋጅ መፈረማቸውን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።

ፕሬዚዳንቱ የጉዞ እገዳ የጣሉባቸው አገራት የአፍሪካ ቀንዶቹ አገራት ኤርትራና ሶማሊያን ጨምሮ፣ ሱዳን፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራን፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሄይቲ፣ ሊቢያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ምንያማር እና የመን ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ “የብሔራዊ ደህንነት አደጋን በመጋረጥ” የወነጀሏቸውን የነዚህ አገራት ዜጎች ላይ የጣሉት የጉዞ እገዳ ከሰኔ 2/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

ከነዚህ ሙሉ የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው በተጨማሪ ሰባት አገራት፣ ብሩንዲ፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ሴራሊዮን፣ ቶጎ፣ ቱርኬመኒስታን እና ቬንዙዌላ ከፊል የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለዚህ የጉዞ እገዳቸው መነሻ የሆናቸው በቅርቡ በኮላራዶ የተፈጸመን ጥቃት ዋቢ አድርገው የውጭ ዜጎች ወደ አሜሪካ በሚገቡበት ወቅት “በአግባቡ ማንነታቸው ሳይጣራ” መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ በለጠፉት ቪዲዮ ተናግረዋል።

ግለሰቡ ለእስራኤል ታጋቾች ድጋፋቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ጥቃት ፈጽሟል ተብሏል።

ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለው ግብጻዊ ዜግነት ያለው ሲሆን፤ ግብጽ በዚህ የጉዞ እገዳ አልተካተተችም።

ትራምፕ በተጨማሪም በጊዜያዊ (ቱሪስት) ቪዛ ወደ አገሪቱ መጥተው የሚቆዩ ሰዎችንም በተመለከተ “አንፈልጋቸውም” ሲሉ ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስ እነዚህ ገደቦች አሜሪካውያንን “ከውጭ አገራት አደገኛ አካላት” ይጠብቋቸዋል ብሏል።

ምንም እንኳን አገራቱ ሙሉ የጉዞ እገዳ ቢጣልባቸውም በኢራን ውስጥ በእምነታቸው እና ጎሳቸው ጭቆና እየደረሰባቸው ላሉ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ ተፈቅዶላቸዋል።

በተጨማሪም ለትላልቅ ስፖርታዊ ዝግጅቶች የሚሳተፉ አትሌቶች እና ውስን ለሆኑ የአፍጋኒስታን ዜጎችም እገዳው እንደማይመለከታቸው ተጠቅሷል።

ይህ የጉዞ እገዳቸው ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ከሰባት በአብዛኛው ህዝባቸው ሙስሊም ከሆኑ አገራት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ጋር የሚመሳሰል ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት በጣሉት የጉዞ እገዳም በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የገቡትን ቃል የፈጸሙበት ሆኗል።

በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆነው የጉዞ እገዳ ህጋዊ ተግዳሮቶች እንደሚገጥመውም ይጠበቃል።

የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው አገራት ውሳኔውን ኮንነውታል። ቬንዙዌላ የትራምፕ አስተዳደርን ” ዓለም በኛ ዛቢያ ብቻ ትዞራለች ብለው የሚያስቡ እብሪተኞች” በማለት ገልጾታል።

ጎረቤት አገር ሶማሊያ በበኩሏ “የተነሱ ስጋቶችን ለመፍታት ውይይት እንደምታደርግ” ቃል ገብታለች።

ከዋይት ሐውስ የተሰማው ትልቁ ውሳኔ ይሄ ብቻ አይደለም፤ ትራምፕ በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለሚማሩ የውጭ አገራት ተማሪዎች ቪዛቸውን የሚገድብ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

በተጨማሪም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የጤናቸው ማሽቆልቆልን ለመሸፈን “ሴራ” ተፈጽሟል ባሉት ላይም ማጣራት እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።