
ከ 1 ሰአት በፊት
በጋዛ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ” የተኩስ አቁም እንዲደረግ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ አደረገችው።
ይህ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እና በጋዛ ላይ እስራኤል የጣለችው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ዕቀባ እንዲነሳ የሚጠይቁ ሐሳቦችን ያያዘው የተኩስ አቁም ጥሪ ረቂቅ በቀሪዎቹ የምክር ቤቱ 14 አባል አገራት ድጋፍ አግኝቶ ነበር።
በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ዶሮቲ ሻ የውሳኔ ሐሳቡ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚደረገውን “ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚያደናቅፍ ነው” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ሐማስን ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ አልሰየመም በማለት ወቅሰዋል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት ሐማስን በሽብር ቡድንነት መፈረጃቸው ይታወቃል።
አምባሳደሯ “ሐማስን በማውገዝ ትጥቁን እንዲፈታ እና ጋዛን ለቆ እንዲወጣ የማያደርግ የትኛውንም እርምጃ አንደግፍም” ሲሉ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር የሆኑት ባርባራ ዉድዋርድ በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ የደገፉት “የማንታገሰውን በጋዛ ያለው ሁኔታ እንዲያበቃ” ካላቸው ፍላጎት መሆኑን እና አገራቸው “ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት” ተኩስ አቁም የተሻለው አማራጭ መሆኑን ስለምታምን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
አምባሳደሯ ጨምረውም እስራኤል በእርዳታ አቅርቦት ላይ የጣለችው “ዕቀባ አሁኑኑ እንዲያበቃ” እንዲሁም “የተባበሩት መንግሥታት እና የእርዳታ ድርጅቶች ሕይወትን ለማዳን፣ ስቃይን ለመቀነስ እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን ለመጠበቅ” በጋዛ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደረግ አለባቸው ብለዋል።
ይህ የውሳኔ ሐሳብ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የቀረበው እስራኤል እርዳታ እና ሌሎች አቅርቦቶች ለ11 ሳምንታት ወደ ጋዛ እንዳይገቡ በማገዷ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል የሚል ስጋት ባየለበት ጊዜ ነው።
በጋዛ ውስጥ የሚካሄደው የእርዳታ አቅርቦት የተባበሩት መንግሥታትን እና ሌሎች ድርጅቶችን በመተካት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስራኤል እና በአሜሪካ የሚደገፈው የጋዛ ሂዩማኒቴሪያን ፋውንዴሽን በተባለው ቡድን አማካይነት ነው።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ግን በዚህ ድርጅት አማካይነት እርዳታ በሚቀርብበት ማዕከል አካባቢ የሰው ሕይወት የጠፋባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተችው ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በፈጸመው ጥቃት 1,200 የሚሆኑ ሰዎችን ከገደለ እና ሌሎች 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከዚያ ጊዜ ወዲህ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ጋዛ ውስጥ በእስራኤል በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።