አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የምስሉ መግለጫ,አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ከ 5 ሰአት በፊት

የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲያስወጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረብ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የያዟቸውን ግዛቶችን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እነሱ ያውቋቸዋል” ሲሉ ተናገሩ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‘ሆርን ሪቪው’ በተባለ ድረ ገጽ ላይ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲያስወጣ መጻፋቸውን ተከትሎ ፤ ቢቢሲ የኤርትራ ወታደሮች በየትኞቹ ቦታዎች ውስጥ እንደሚገኙ ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው ይህንን ምላሽ የሰጡት።

አምባሳደሩ “ይህንን በዝርዝር ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሄ የቆየ ነገር ስለሆነ፤ ይሄንን በዚህ ደረጃ፣ እነሱ ያውቁታል ብሎ ማለፍ ይሻላል” ሲሉ ግዛቶቹን በስም ሳይጠቅሱ አልፈውታል።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር የተሰለፈው የኤርትራ ጦር የነበረውን ተሳትፎ በተመለከተ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና የመብት ድርጅቶች ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ሲያወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የነበሩት ዲና ሙፍቲን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ እየተሳተፉ ነው መባላቸውን “መሠረተ ቢስ” በማለት ሲያጣጥሉ መቆየታቸው አይዘነጋም።

በመንግሥት ደረጃ የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ሲባል የነበረውን ቢቢሲ ጠቅሶ “ከጊዜ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው ገብተው ይሆን?” የሚል ጥያቄ አምባሳደር ዲናን ጠይቋቸው ነበር።

በሰጡትም ምላሽ “መገፋፋት አለ። የቆየ ጉዳይ ነው። መግባት መውጣት ያለ ነገር ነው። ይሄንንም በዚያ ደረጃ ማየት ነው የሚሻለው” ብለዋል።

ቢቢሲ በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች መቼ እንደገቡ እና የያዟቸው ቦታዎች የትኞቹ እንደሆነ መጥቀስ አይቻልም? ወይ ሲል አምባሳደሩን ጠይቋቸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፤ ይህንን በተመለከተ ‘ስታቲስቲካሊ’ ምንም የለኝም” በሚል የኤርትራ ወታደሮች የትኞቹን ግዛቶች ስለመያዛቸው ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ሁለት ዓመታት ባስቆጠረው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ኃይሎች በትግራይ ውስጥ ፌደራል መንግሥቱን ደግፈው መሰማራታቸውን እና የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን በሚመለከት ከመብት ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ምዕራባውያኑ አገራት እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት የቋጨው በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው የፕሪቶሪያው ግጭትን የማቆም ዘላቂ ስምምነትን ተከትሎ’፤ ናይሮቢ ላይ በተፈረመው የስምምነት ማስፈጸሚያ ዝርዝር መሠረት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከትግራይ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ ሠራዊት በሕግ የተሰጠው ቦታ ላይ እንደሚገኝ እና ከዚያ ውጪ ያዛቸው ቦታዎች ካሉ የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረው ነበር።

ከአራት ዓመታት በፊት መመሥረቱን እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንተና የሚሰጥ መድረክ እንደሆነ በድረ ገጹ ላይ የጠቀሰው ‘ሆርን ሪቪው’ ላይ በወጣው ጽሑፋቸው፤ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛቶች ለቀው” ከመውጣት በተጨማሪ የኤርትራ መንግሥት ለታጣቂ ኃይሎች የሚያደርገውን ድጋፍ ጠቅሰዋል።

አምባሳደሩ በዚህ “At 34, Time to Tend to Matters at Home?” በሚል ርዕስ ባወጡት ጽሁፋቸው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ለኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎች ድጋፍ ከመስጠት እንዲታቀብ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ይደግፏቸዋል ያሏቸውን ታጣቂ ኃይሎች ማንነት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢቢሲ አምባሳደር ዲናን የጠየቃቸው ሲሆን እሳቸውም፤ “እነሱ ያውቁታል” የሚል አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተው ለሁለቱም አገራት ሰላም ነው የሚያስፈልጋቸው” በሚል ለሰላም አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ለሁለቱ አገራት ሰላም፣ መከባበር እና አብሮ መኖር ነው የሚያስፈልጋቸው። ነገር ግን ከዚህ ውጪ የሚሆነው ነገር መገፋፋት፣ መጣላት፣ መወጋጋት አያዋጣም። በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም መፍጠር የግድ ለሁለቱም አገራት፣ ሰላም፣ ለሕዝቦች ጠቀሜታ አለው” ብለዋል።

አምባሳደሩ በተጨማሪ የኤርትራ መንግሥት “የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛቶች እስከ ወዲያኛው ተቆጣጥሮ ሊቀጥል አይችልም” ሲሉ በዚሁ ጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ይህንንም አስመልክቶ ተጠይቀው “በደንብ በአጽንኦት መያዝ አለበት” ካሉ በኋላ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች ለማስወጣት ምንድን ነው መደረግ? በሚል የተጠየቁት ዲና ሙፍቲ ሁኔታው ለማንም አይጠቅምም ብለዋል።

“አሁን የሚያስፈልገው ሁሉም ተረጋግቶ፤ በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ በስተቀር በጉልበት፣ በጦርነት፣ በግፊት እና በመገፋፋት የሚደረግ ነገር አያዋጣም። ለሁለቱም አገራትም ሆነ ሕዝቦች አይጠቅምም” ሲሉ ስለ ሰላም አስፈላጊነት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚያደርጉት የቃላት ልውውጥ ከቀን ወደ ቀን እየተካረረ መምጣቱ ሁለቱ አገራት ያላቸው ግንኙነት መሻከሩን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ የኤርትራው ፕሬዝደንት በ34ኛው የነጻነት በዓል ላይ ኢትዮጵያን ጠቅሰው ከተናገሩ በኋላ “አገር ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ” አገራት “በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር መሞከራቸው የተለመደ ባህሪ እንደሆነ እናውቃለን” ብለው ነበር።

ለዚህም ምላሽ የሚመስል መልዕክት ያጋሩት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል “በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ደጋፊዎች/ተሳዳቢዎች ስለ ኤርትራ ማንኛውንም ነገር መተቸት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል” ብለዋል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአገሪቱ ነጻነት በዓል ላይ “የውጭ ኃይሎች በብልጽግና ወኪላቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ያወጁት ጦርነት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ የሚያሳይ ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

የባለስልጣናቱ ክሶች፣ ወቀሳዎች በአገራቱ መካከል ውጥረት መፍጠሩን ተከትሎ የጦርነት ስጋት ይኖር ይሆን ወይ? መሬት ላይ ወደ ጦርነት የሚያመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ ተብለው የተጠየቁት አምባሳደር ዲና በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም በደፈናው ጦርነት አያስፈልግም ብለዋል።

“ለዘመናት አይተነዋል፤ ሞክረነዋል። ከዚህ በኋላ ጦርነት ለዚህ አካባቢ አውዳሚ ነው፤ የፕሮፓጋንዳም ይሁን ወታደራዊ ጦርነት አያስፈልግም” ካሉ በኋላ ለሁለቱም አገራት የሚያስፈልገው ሰላም ነው፤ መረጋጋት ነው። ልዩነቶች ካሉም መደራደር ነው። ጦርነት ከዚሀ በፊት የጠቀመን ነገር የለም” ብለዋል።