ወደ አሜሪካ እየገቡ ያሉ መንገደኞች

ከ 49 ደቂቃዎች በፊት

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪካ ቀንድ አገራት የሆኑትን ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ናቸው ባሏቸው የአስራ ሁለት አገራት ዜጎች ላይ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎችን የሚከለክል ትዕዛዝ መፈረማቸውን ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

ከእነዚህም በተጨማሪም በሰባት አገራት ዜጎች ላይ ከፊል የጉዞ እገዳን ጥለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዝርዝሩ “ተጨባጭ ማሻሻያዎች” ከታዩ እንደሚከለስ እንዲሁም “በዓለም ዙሪያ ሌሎች ስጋቶች ከመጡ” ተጨማሪ አገራት ሊካተቱ ይችላሉ ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ የጉዞ ዕገዳዎችን ሲጥሉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው፣ በአውሮፓውያኑ 2017 ተመሳሳይ የጉዞ ክልከላዎችን የሚደነግግ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።

የጉዞ ዕገዳ የተጣለባቸው የትኞቹ አገራት ናቸው?

ትራምፕ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ናቸው በማለት ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ የከለከሏቸው አገራት 12 ናቸው።

በተጨማሪም ሰባት አገራት ከፊል የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን እነዚህም፦

የጉዞ ዕገዳው በመጪው ሰኞ፣ ሰኔ 1/2017 ዓ.ም. ሌሊት 6 ሰዓት ላይ ተግባራዊ ይሆናል።

ከስምንት ዓመታት በፊት ጊዜ ሳይጠቀስ ያለ ማስጠንቀቂያ የተጣለው የጉዞ እገዳ በአገሪቱ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ከፍተኛ ትርምስ መፍጠሩን ተከትሎ ቀኑ መጠቀሱ ያንን ቀውስ ያስቀረዋል ተብሏል።

የጉዞ እገዳው እስከ መቼ ድረስ እንደሚቆይ ያልተገለጸ ሲሆን፤ ሆኖም ያስተላለፉት ትዕዛዝ ወቅታዊ ግምገማ የሚያደርጉበት እንደሆነ ተገልጿል።

የጉዞ ዕገዳው ለምን ተጣለ?

ዋይት ሐውስ እነዚህ ገደቦች አሜሪካውያንን “ከውጭ አገራት አደገኛ አካላት” ይጠብቋቸዋል ብሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው በቅርቡ በኮላራዶ የተፈጸመ “የሽብር ጥቃትን” ዋቢ አድርገው የውጭ ዜጎች ወደ አሜሪካ በሚገቡበት ወቅት “በአግባቡ ማንነታቸው ሳይጣራ” ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ከፍተኛ አደጋ አጉልቶ ያሳየ ነው ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ በለጠፉት ቪዲዮ ተናግረዋል።

የኮሎራዶውን ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ለእስራኤል ታጋቾች ድጋፋቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ተቀጣጣይ ቁሶችን በመወርወር ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ 12 ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።

ጥቃቱን በመፈጸም የተወነጀለው ግለሰብ ግብፃዊ ዜግነት ያለው ሲሆን፤ ግብፅ ግን በዚህ የጉዞ ዕገዳ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም።

ትራምፕ ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም “የምመርጠው አምባገነን” በሚል ገልጸዋቸው ነበር።

የጉዞ ዕገዳው ከተጣለባቸው አገራት የማይመለከታቸው ዜጎች አሉ?

የጉዞ ዕገዳ የተጣለባቸው አገራት ዜጎች ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ክልከላ የማይመለከታቸው ወይም ነጻ የተደረጉ ዜጎች አሉ። እነዚህ ዜጎችም ወደ አሜሪካ ጉዟቸውን ማድረግ ይችላሉ።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ግለሰቦች ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም የሚያገለግሉ ከሆነ” እያንዳንዱ ጉዳይ ተለይቶ እንዲታይ እና ከጉዞ ክልከላው ነጻ ማድረግ እንደሚችሉም ተጠቁሟል።

ለጉዞ ዕገዳው ምን ምላሽ ተሰጠ?

የሕግ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት የሚጠበቀው የትራምፕ የጉዞ ክልከላ ትዕዛዝ በአገራቸው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምላሾች ተሰጥቶበታል።

ሶማሊያ ማንኛውንም የደኅንነት ሁኔታዎች ለመፍታት ከአሜሪካ ጋር እንደምትሠራ ቃል ገብታለች።

በአሜሪካ ተቀማጭ የሆኑት የሶማሊያ አምባሳደር ዳሂር ሐሰን አብዲ አገራቸው “ከአሜሪካ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት ከፍ ያለ ስፍራ ትሰጠዋለች” ብለዋል።

የቬንዙዌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዲዮስዳዶ ካቤሎ “በአሜሪካ ውስጥ መቆየት ለቬንዙዌላውያን ብቻ ሳይሆን ለማንም ትልቅ አደጋ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዲሞክራቶች ይህንን የትራምፕ እርምጃ አውግዘዋል።

“ይህ ዕገዳ ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ተግባራዊ ካደረጉት የሙስሊም አገራት ክልከላ የሰፋ እና በዓለም መድረክ የበለጠ የሚያገለን ነው” ሲሉ የዋሽንግተን የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ፕራሚላ ጃያፓል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።

ሌላኛው የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ዶን ቤር ትራምፕ የአሜሪካ መሥራቾች መርሆችን “የካዱ” ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የጉዞ ዕገዳውን ተችተዋል።

“አድሏዊ፣ ዘረኛ እና ጭካኔ የተሞላበት” ሲል ክልከላውን የፈረጀው ዓለም አቀፉ የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ዩኤስኤ ነው።

በአሜሪካ ተቀማጭነቱን ያደረገው ‘ሂውማን ራይት ፈርስት’ የተባለው ተቋም ደግሞ “ፀረ ስደተኛ እና በፕሬዝዳንቱ የተፈጸመ የቅጣት እርምጃ” ብሎታል።

የትራምፕ የመጀመሪያ ጊዜ ዕገዳቸው ምን ሆነ?

ትራምፕ የመጀመሪያ የጉዞ ክልከላን የጣሉት በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው፣ በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር።

በአሁኑ የጉዞ ዕገዳ የተጠቀሱት እንደ ኢራን፣ ሊቢያ እና ሶማሊያ በወቅቱም ተካተውበት ነበር።

በመጀመሪያው የጉዞ ዕገዳ አብዛኛው ሕዝባቸው ሙስሊም ከሆኑ አገራት የሆኑ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ በተቺዎቻቸው ዘንድ “የሙስሊሞች ዕገዳ” በመባል ይታወቃል።

ትዕዛዙ ከተላለፈ በኋላ ወዲያውኑ ነበር በመላው አሜሪካ ባሉ ፍርድ ቤቶች መከራከሪያ የሆነው።

ዋይት ሐውስ ፖሊሲውን አሻሽሎ ሁለት ሙስሊም ያልሆኑ አገራትን፤ ሰሜን ኮሪያን እና ቬንዙዌላን የጉዞ ዕገዳው ውስጥ አካቶ ነበር።

ይህም በአውሮፓውያኑ 2018 በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀባይነት እንዲያገኝ ሆነ።

ትራምፕን የተኩት ጆ ባይደን ዕገዳውን “ብሔራዊ ህሊናችንን ያጎደፈ” ሲሉ በአውሮፓውያኑ 2021 ሰርዘውታል።