በቦይንግ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቀብር

ከ 2 ሰአት በፊት

ቦይንግ የ346 ሰዎችን ህይወት ለቀጠፉት የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋዎች በወንጀል እንዳይከሰስ በሚል 1.1 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ እና የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት የደረሱበትን ስምምነት የተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቆች “አጸያፊ” ሲሉ ኮንነውታል።

በቦይንግ 737 ማክስ የአውሮፕላን አደጋዎች ህይወታቸውን ያጡ 16 ተጎጂ ቤተሰቦችን የወከሉ የህግ ባለሙያዎች ናቸው ስምምነቱን የኮነኑት።

ኩባንያው በሁለቱ አደጋዎች የወንጀል ክስ እንዳይመሰረትበት በሚል ነው 1.1 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል የተስማማው።

በኢንዶኔዥያ ላየን አየር መንገድ አደጋ ተጎጂዎች መካከል ለተወሰኑት አማካሪ የሆኑት ሳንጂቭ ሲንግ

ስምምነቱ ቦይንግ “ከወንጀል ተጠያቂነት የሚያወጣ ነው” በማለት ተችተው በተጎጂ ቤተሰቦችም ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል ብለዋል።

ቦይንግ ከዚህ ቀደም “በደረሰባቸው ኃዘን የሚሰማን ጥልቅ ኃዘን ነው፤ የሚወዷቸውን ሰዎች ትዝታ ለማስታወስ በኩባንያችን ላይ የምናደርገውን ጥልቅ ለውጥ እንቀጥልበታለን” ብሏል።

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው ለአደጋዎቹ ተጎጂዎች ቤተሰቦች 444̋.5 ሚሊዮን ዶላር የሚከፍል ይሆናል። 455 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ደህንነቱ፣ ጥራት እና ቁጥጥርን ለማሻሻል ለሚያወጣው ፕሮግራም የሚውል እንደሚሆን ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ቦይንግ 487.2 ሚሊዮን ዶላር የወንጀል ቅጣት ለመክፈል ተስማምቷል።

“ቦይንግ በዚህ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ያለበትን ግዴታ ለመወጣት ቁርጠኛ ነው፤ ይህም ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት እና ተጨማሪ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እና ኢንቨስትመንቶችን ያካትታል” ሲሉ የኩባንያው ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ስምምነቱ በፌደራል ዳኛ ከጸደቀ ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በማጭበርበር ወንጀል ከመሰሰስ ይድናል።

“ኩባንያው በወንጀል እንዳይከሰስ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል” ሲል ቦይንግ አስታውቋል። ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ሲንግ ስምምነቱ ወደ ፌደራል ዳኛ በሚመራመት ወቅት የተጎጂ ቤተሰቦች ይግባኝ አንደሚሉ ተናግረዋል። ኩባንያው ለመክፈል ያቀረበው ገንዘብ ለተጎጂ ቤተሰቦች በቂ እንዳልሆነ ያምናል።

“ኩባንያው ለመክፈል ያቀረበው 1.1 ቢሊዮን ዶላር ከወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ 10 ዶላር የመክፈል ያህል ነው። ልክ የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ጥሰው ቲኬት ወይም አነስተኛ ነገር እንደፈጸሙ ያህል ነው” ብለዋል።

በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው አሰቃቂ በተባለው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋዎች በኢትዮጵያው 157 እንዲሁም በኢንዶኔዥያው አየር መንገድ 189 ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።

የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት በአውሮፕላንን አምራቹ ላይ ካደረገው የረዥም ጊዜ ምርመራ በኋላ ቦይንግ ለ737 ማክስ አውሮፕላኑ ፍቃድ ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ተቆጣጣሪዎችን እንዳሳሳተ ደርሸበታለሁ በሚል “አሜሪካን ለማጭበርበር በማሴር” በሚል ከአራት ዓመት በፊት ክስ መስርቶበት ነበር።

ቦይንግ ቺካጎ በነበረው የፍርድ ሂደት በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማምቶ በምላሹም የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ለአውሮፕላን አምራቹ ከ737 ማክስ ዲዛይን ጉድለት ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ሴራ በወንጀል እንዳይከሰስ ከለላ ሰጥቶት ነበር።

የአውሮፕላን አምራቹ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እና ተጠያቂነቱን ተቀብሎ ለአሜሪካ መንግሥት፣ አደጋ ለደረሰባቸው አየር መንገዶች እና ለተጎጂዎች የሚሆን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ ለመክፈል በወቅቱ ተስማምቷል።

በወቅቱም የፌደራል ዐቃቢያነ ሕጎች ቦይንግ ለመጪው ሦስት ዓመታት ያህል ለስምምነቱ ተገዢ ከሆነ የወንጀል ክሱን ለመተው ተስማምተው ነበር።

ሆኖም ስምምነቱ ጊዜው ከማለፉ በፊት በአላስካው አየር መንገድ የቦይንግ ማክስ 9 በር በአየር ላይ ተገንጥሎ መውደቁን ተከትሎ የምርቶቹን ደህንንት እና ጥራት ለማስጠበቅ የገባውን የቁጥጥር መርሃ ግብር ስምምነቱን መጣሱን ማሳያ እንደሆነም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማመላከቱ ባለፈው ዓመት ተገልጾ ሊከሰስ ይችላል ተብሎ ነበር።

መጋቢት 01/2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አሰቃቂው አደጋ የደረሰው።

በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል።

በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱት የኢትዮጵያው አየር መንገድ እና የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ ውስጥ በማስገባት እና ጥፋቱን ወደ ሌሎች በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።

ከስድስት ዓመት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር መሆኑን መገለጹ ይታወሳል።