June 5, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ
ወደፊት ለሚቋቋመው “የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ”፤ ከመንግስት እና ከግል ተቋማት ሰራተኞች ደመወዝ መዋጮ እንዲሰበሰብ የሚያስገድደው የአዋጅ ድንጋጌ ተሰረዘ። ድንጋጌው በዛሬው ዕለት በፓርላማ ከጸደቀው “የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አዋጅ” ውስጥ እንዲወጣ የተደረገው፤ በሰራተኞች ላይ “ተደራራቢ ጫና እንዳያስከትል” ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።
ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ይኸው አዋጅ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧቸው 15 አይነት አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” ገቢ እንዲሰበሰቡ የሚያስገድድ ድንጋጌ በውስጡ ይዞ ነበር። ፈንዱ “ለአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋም” ተግባራት የሚውል እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፤ ከጠቅላላ ዓመታዊ በጀታቸው ውስጥ የተወሰነ “ድርሻ” ለፈንዱ እንደሚያወጡ በአዋጁ ላይ ተደንጓል። ከለጋሽ አካላት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሚሰበሰብ እንዲሁም “የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰቢያ ስልቶችን” በመጠቀም የሚገኝ ገንዘብ የፈንዱ ሌላኛው የገቢ ምንጭ ይሆናል።
Post

ለአደጋ ስጋት ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል ለሚቋቋም ፈንድ፤ የመንግስትና የግል ተቋማት ገቢ
እንዲሰበስቡ የሚያስገድድ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ። ገቢ ያላስገባ ተቋም 10 በመቶ የባንክ ወለድ ቅጣት
ጨምሮ እንዲከፍል ይገደዳል።
https://ethiopiainsider.com/2025/15441
Translate post
1 3 8
በገቢ ምንጭነት በአዋጁ ተዘርዝረው ከነበሩት መካከል “የመንግስት እና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ ላይ” መዋጮ እንዲሰበሰብ የሚያስገድደው ድንጋጌ አንዱ ነበር። አዋጁ ለውይይት በቀረበበት ወቅት፤ ከደመወዝ ላይም ሆነ ከተለያዩ አገልግሎቶች ለፈንዱ ገቢ የሚሆን ገንዘብ መሰብሰብ “የግለሰቦችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር።
ለፈንዱ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ከሚጠበቁት ውስጥ፤ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ድምጽ እና ዳታ አገልግሎት፣ የዲጂታል ባንኪንግ፣ የበረራ ትኬት ሽያጭ፣ የፓስፖርት እና ቪዛ አገልግሎት ክፍያ፣ የንግድ ፈቃድ በሚወጣበት እና በሚታደስበት ጊዜ በቁርጥ የሚታሰብ ክፍያ ተጠቃሽ ናቸው። ባንኮች፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን የፋይናንስ ድርጅቶች ከሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የሚታሰብ ገንዘብም ሌላው የፈንዱ የገቢ ምንጭ ነው።
እነዚህን ከመሰሉ አገልግሎቶች የሚሰበሰብ ገንዘብ በተጠቃሚዎች ላይ ጫና ያሳድራል የሚል ትችት ቢቀርብበትም፤ እነርሱን በሚመለከተው አዋጅ ላይ ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግ አዋጁ ጸድቋል። ሆኖም በአዋጁ ተካትቶ የነበረው እና ሰራተኞች ከደመወዛቸው ላይ ለፈንዱ እንዲያወጡ የሚያስገድደው ድንጋጌ ግን ተሰርዟል።
Post

ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ የሚውል ገቢ፤ ከግለሰቦች እና ከሰራተኞች ደመወዝ እንዲሰበስብ የሚያስገድደው
የአዋጅ ረቂቅ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ መድረክ ጥያቄ ተነሳበት።የመዋጮ መጠኑ ወደፊት በሚወጣ ደንብ
እንደሚወሰን ተገልጿል።
https://ethiopiainsider.com/2025/15664
Translate post
4 3 13 1
አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ለፓርላማ የቀረበው “የውሳኔ ሃሳብ”፤ ድንጋጌው ከአዋጁ ላይ እንዲወጣ የተደረገው “የተጣራ ደመወዝ ላይ የሚቆረጥ መዋጮ፤ ሰራተኞች ላይ ተደራራቢ ጫና እንዳይስከትል ነው” ሲል ምክንያቱን አስቀምጧል። የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረበው፤ አዋጁን በዝርዝር እንዲመለከት ተመርቶለት የነበረው የፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው።
ቋሚ ኮሚቴው ካቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በኋላ አዋጁ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። አዲሱ አዋጅ የሚጠበቅበትን ገቢ ሰብስቦ ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ የባንክ ሂሳብ ያላስተላለፈ ድርጅት ወይም ተቋም፤ ሊያስገባው ይገባ ከነበረ ገንዘብ በተጨማሪ አስር ከመቶ የባንክ ወለድ ቅጣት እንዲከፍል ያስገድዳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)