June 5, 2025

የፌደራል መንግስት ለ2018 ያዘጋጀው በጀት፤ ከዘንድሮው አኳያ በግማሽ ትሪሊዮን ብር ገደማ ዕድገት ቢያሳይም በዶላር ሲሰላ ከፍተኛ ቅናሽ አስመዘገበ። ለሚቀጥለው ዓመት የተዘጋጀው በጀት፤ ሁለት ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

በጀቱን የያዘው የአዋጅ ረቂቅ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 28፤ 2017 በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል። የበጀት ረቂቁ “የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ”፣ “ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ” እንዲሁም “በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳት አንጻር”  የተዘጋጀ እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ በጀቱ ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ያለውን “የመካከለኛ ዘመን” የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ መግለጫው ጠቁሟል። ማዕቀፉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ሳምንት በተካሄደ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነበር።

የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ማዕቀፉ “የመንግስትን ገቢ መሰረት በማስፋት ወጪን ለመሸፈን” እንዲያስችል ሆኖ መዘጋጀቱ ተጠቅሶ ነበር። በኢትዮጵያ “የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ” የሚደረገውን ጥረት “የሚደግፍ ሆኖ የተዘጋጀ ነው” የተባለለት ይህ ማዕቀፍ፤ ከመንግስት ገቢ አሰባሰብ እና ሃብት አመዳደብ አኳያ ያሉ “የፖሊሲ አቅጣጫዎችን” የሚያመላክት እንደሆነም ተገልጿል። 

በዚህ ማዕቀፍ መነሻነት የተዘጋጀውን የ2018 በጀት ትክክለኛ መጠን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መረጃ ላይ አልገለጸም። ጽህፈት ቤቱ ይፋ ያደረገው “ሁለት ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ” የሚለው የገንዘብ መጠን፤ በዘንድሮው ዓመት በመደበኛነት እና በተጨማሪነት ከጸደቀው የበጀት መጠን ጋር ሲነጻጸር በ29 በመቶ ገደማ ዕድገት ያሳያል።

የ2018 በጀት ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በ500 ቢሊዮን ብር ገደማ ጭማሪ ቢኖረውም በዶላር ግን ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል።  በግንቦት 2016 ዓ.ም የጸደቀው የዘንድሮው 971.2 ቢሊዮን ብር መደበኛ በጀት፤ በወቅቱ ምንዛሬ 17 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህዳር 2017 ዓ.ም ያጸደቀው 581.98 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ደግሞ በዚያን ጊዜ በነበረው የዶላር ምንዛሬ ሲሰላ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል።

የሁለቱ ድምር የ2017ን አጠቃላይ በጀት ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ወይም 21.8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አድርሶታል። ይህ  አጠቃላይ በጀት ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለፓርላማ ከመራው የ2018 በጀት ጋር ሲነጻጸር፤ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ልዩነት ያሳያል።     

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካይ ዕለታዊ የምንዛሬ ጠቋሚ መሰረት፤ አንድ ዶላር በዛሬው ዕለት የተመነዘረው በ134 ብር ነው። በዚህ ስሌት መሰረት፤ ለ2018 የተዘጋጀው ሁለት ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት 15 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይሆናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)