June 5, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምትዋሰንባቸውን በሺህዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር ድንበርን “የማካለል ስራ”፤ “ተቋማዊ ቅርጽ ሰጥቶ” ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ አስታወቁ። ሀገሪቱ ካላት ድንበር “በአግባቡ የተሰመረ እና የተለየው” ከ50 በመቶ በታች መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የድንበር ማካለል ጉዳይ የተነሳው፤ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 28፤ 2017 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። በዚሁ ስብሰባ ላይ የውጭ ጉዳዮችን የተመለከቱ የተለያዩ ጥያቄዎች፤ በአምስት የፓርላማ አባላት ቀርበዋል።
ከጠያቂዎቹ አንዷ የነበሩት ገዢው የብልጽግና ፓርቲን በመወከል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጊዶሌ መደበኛ ምርጫ ክልል የተመረጡት ይፍቱ ጉዲሳ ናቸው። የፓርላማ አባሏ በጥያቄያቸው መንደርደሪያ ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ “ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት የሚሰጥ” መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ይሁንና አንዳንድ ጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነታችንን በመጣስ የገዛ መሬታችንን መያዛቸው ይነገራል” ያሉት ወ/ሮ ይፍቱ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን “እውነታ” እንዲያብራሩላቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል። ዶ/ር ጌዲዮን በምላሻቸው፤ በአፍሪካ ቀንድ ከሁሉም ሀገራት ጋር የምትዋሰን “ብቸኛ ሀገር” ኢትዮጵያ መሆንዋን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ በሺህዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር “በጣም ሰፊ የሆነ” ዓለም አቀፍ ድንበር እንዳላትም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሀገሪቱ በሰሜን ከኤርትራ፣ በምስራቅ ከሶማሊያ እና ጅቡቲ፣ በምዕራብ ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን፣ በደቡብ ከኬንያ ጋር ድንበር ትጋራለች። ሆኖም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ከምትጋራው ድንበር ውስጥ “በአግባቡ” “የተከለለ”፣ “የተሰመረ” እና “የተለየው” ከግማሽ በታች እንደሆነ አስረድተዋል።
“በካርታ በሚገባ ተለይቶ በሀገራት መካከል መግባባት ተፈጥሮበት ዴሪቬት የተደረገ፤ በአግባቡ የተሰመረ፣ የተለየ እና ችካል የተደረገበት ወሰን ያለን ከ50 ፐርሰንት የሚያንስ ነው” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮን ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከ“አንድ ጎረቤት ሀገር” ጋር “በደንብ የተለየ ወሰን” እንዳላት ሚኒስትሩ ቢገልጹም፤ የሀገሩን ማንነት በስም ሳይጠቅሱ ቀርተዋል።

ከአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው የድንበር እና የወሰን ጉዳይ፤ “ትኩረት” እና “ተጨማሪ ሰፊ ስራ” የሚፈልግ መሆኑን ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል። ድንበር ማካለልን በተመለከተ “በጣም ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ” ሲሉም አክለዋል።
“አንዳንድ ሀገራት ይሄንን የሚመለከት ኮሚሽን አቋቁመው፤ ከህግ፣ ከካርቶግራፊ፣ ከጂኦግራፊ፣ ከሶሾሎጂ፣ ከተለያዩ [ዘርፎች] multidisciplinary የሆነ የስራ ኃይል በማቋቋም፤ ከየሀገራቱ ጋር በዲፕሎማሲ ግንኙነት የተለየ፣ የታወቀ ድንበር እንዲኖር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ” ያሉት ዶ/ር ጌዲዮን፤ “በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ብዙ መስራት የሚጠበቅባት ሀገር ናት” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።
“በሺህዎች ኪሎሜትሮች የሚቆጠር ድንበራችንን የማካለል ስራ ገና አልሰራንም። ይሄንን ተቋማዊ ቅርጽ ሰጥተን ለመስራት በዝግጅት ላይ እንገኛለን” ሲሉም ስራውን ለማከናወን እቅድ መኖሩን ሚኒስትሩ አመልክተዋል። “መጀመሪያ መሰራት ያለባቸው ጥናቶች፣ መለየት ያለባቸው ነገሮች አሉ” ሲሉም ለስራው ቅደመ ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።

“መዘጋጀት ያለብን፣ መስራት ያለብን፣ የቤት ስራ አለ። የራሳችንን የቤት ስራ በሚገባ ከሰራን በኋላ ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ይሄንን ጉዳይ አጀንዳ አድርገን መነጋገር፣ መግባባት ይጠይቃል” ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሂደቱ በቀጣይ የሚጠበቀውን አስረድተዋል። “ስለዚህ ይሄንን በእቅድ ይዘን በቀጣይ ዓመታት መስራት ያለብን ነገር ነው” ሲሉም ሂደቱ በርካታ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።
በአግባቡ ያልተካለለ ድንበር፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባለ ግንኙነት ላይ “ክፍተት” እና “አለመግባባቶችን” እንደሚፈጥር የገለጹት ዶ/ር ጌዲዮን፤ ስራውን “በጥናት ላይ ተመስርቶ” “በተደራጀ ሁኔታ” ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የድንበር ማካለል ስራው “በመረጃ ላይ ተመስርቶ”፤ ታሪክን፣ ህግን እንዲሁም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን “በአግባቡ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ” መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
“የሀገርን ጥቅም፣ የሀገርን ድንበር እና ሉዓላዊነት የሚያስከብር ሰፊ ስራ ይጠይቃል። ግን ውዝፍ የሆነ እስካሁን ያልተሰራ የቤት ስራ ነው። እሱን መስራት አለብን” ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። የድንበር ጉዳይን በተመለከተ “ከየሀገራቱ ጋር ያሉትን ጉዳዮች የማላነሳው በምክንያት ነው” ያሉት ዶ/ር ጌዲዮን፤ ለተጠየቁት ጥያቄ በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ታቅበዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ከኤርትራ ጋር በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች ያሉ ስፍራዎች በሁለቱ ሀገራት የጦር ኃይሎች መያዛቸውን በተመለከተ በፓርላማ ጭምር ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል። የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቃባይ እና የፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዲና ሙፍቲ በዚህ ሳምንት “ሆርን ሪቪው” በተባለ ድረ ገጽ ላይ ባወጡት ጹሁፍ፤ የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲያስወጣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ መጠየቃቸውም መነጋገሪያ ሆኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)