
ከ 2 ሰአት በፊት
እስራኤል የሔዝቦላህ ሰው አልባ አውሮፕላን ምርት ላይ ያነጣጠረ ነው በማለት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ፈፀመች።
በኢድ አል አድሃ አረፋ ዋዜማ፣ ሐሙስ ምሽት ላይ ሔዝቦላህ በዋና ከተማው ይገኝባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በርካታ ሕንፃዎችን ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተከትሎ ጥቃቱ መፈጸሙ ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል “በኢራን አሸባሪዎች” የሚደገፍ “በሺህ የሚቆጠሩ” ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) የሚያመርት የሔዝቦላህ ክፍል ከምድር በታች መለየቱን አስታውቋል።
ጥቃቱ የተከሰተው በእስራኤል እና በታጣቂው ቡድን መካከል ላለፉት ስድስት ወራት የተኩስ አቁም ተደርሶ እያለ ነው።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ድብደባውን “በጽኑ አወገዛለሁ” ብለዋል።
ናዋፍ ሳላም በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ “በአገራችን በደኅንነት፣ በመረጋጋቷ እና በኢኮኖሚዋ በተለይም በበዓላት ዋዜማ እና በቱሪስት መገኛ ሰሞን ላይ ስልታዊ እና ሆን ተብሎ የተደረገ ጥቃት እንደሆነ እቆጥረዋለሁ” ብለዋል።
እስራኤል ነዋሪዎች ሕንጻዎቹን ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨናነቀው አካባቢ በተዘጋጉ መንገዶች መካከል ሲሸሹ ታይተዋል።
ከዚያም በእስራኤል አየር ኃይል ከተፈጸመው ጥቃት የተነሳ የአካባቢው ሰማይ በጭስ ተሸፍኖ ታይቷል።
የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ጥቃቱን “የተቀደሰ ሃይማኖታዊ በዓል በሚከበርበት ዋዜማ ላይ የተፈጸመ ሆን ተብሎ ዓለም አቀፍ ስምምነትን የጣሰ” ሲሉ አውግዘውታል።
የእስራኤል ጦር ሔዝቦላህ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን “በስፋት መጠቀሙ” በእስራኤል ላይ ለሚያካሂደው ጥቃት ዋና ማዕከል መሆኑን ገልጾ ድርጊቱን “በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል ያለውን መግባባት በግልፅ መጣስ ነው” ብሏል።
እስካሁን ከሔዝቦላህ የተሰጠ አስተያየት የለም።
የአየር ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከአንድ ሰዓት በፊት የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ በአረብኛ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የተወሰኑ ሕንጻዎችን የሚያሳይ ካርታ በመለጠፍ “በሂዝቦላህ ንብረትነት የተያዘ መሠረተ ልማት አጠገብ ናችሁ” ብሏል።
ከጋዛ ጦርነት በፊት በኢራን የሚደገፈው የሔዝቦላህ ቡድን እና እስራኤል ከአንድ ዓመት በላይ ጦርነት ውስጥ የቆዩ ሲሆን፣ እስራኤል ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት በመፈጸም እና የደቡባዊ ሊባኖስን የመሬት በመውረሯ ግጭቱ ተጠናቅቋል።
ጥቃቱ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ጨምሮ በሊባኖስ ወደ 4,000 የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ከ 1.2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው አፈናቅሏል።
እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ተልእኮ በድንበር አካባቢ ያለውን ጥቃት ማስቆም አልቻለም በሚል በድንበር አቅራቢያ የሚገኙትን የሔዝቦላህ ተቋሞችን ለማፍረስ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጻለች።
ዓላማውም በቡድኑ ጥቃት ምክንያት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተፈናቀሉ 60 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎችን ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረግ መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።
በኅዳር ወር መገባደጃ ላይ ሔዝቦላህ ባልተሳተፈበት በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም የተደረሰ ሲሆን፣ የሊባኖስ ጦር ደቡባዊ ሊባኖስን እንዲቆጣጠር ከስምምነት ተደርሷል።
ስምምነቱ በተጨማሪም “እስራኤልም ሆነች ሊባኖስ የገቡትን ቃል ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በተጣጣመ መልኩ ራሳቸውን የመከላከል መብታቸውን ከመጠቀም አያግድም” ብሏል።
እስራኤል በሊባኖስ ከሔዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው ዒላማዎች ላይ ከወራት በፊት የአየር ድብደባ ፈጽማለች።