
ከ 5 ሰአት በፊት
በየዓመቱ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ሳዑዲ አረቢያዋ ቅዱስ ከተማ መካ በመጓዝ ከእስልምና እምነት መሠረቶች አንዱ የሆነውን የሐጅ ሥነ ሥርዓትን ይፈፅማሉ።
ሐጅ በእስላማዊ የቀን መቁጠሪያ መሠረት የመጨረሻው ወር በሆነው ዱሁ አል ሂጃ ወቅት የሚካሄድ መንፈሳዊ ጉዞ ነው።
በዚህ ዓመትም ከግንቦት 27 ጀምሮ እስከ ሰኔ 2/2017 ዓ.ም. ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታዮች በጉዞው ላይ እየተሳተፉ መሆናቸው ይታመናል።
ሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ብቻ ሳይሆን ፈታኝ በሆኑ የአየር ጠባዮች እና መልከዓ ምድሮች መጓዝን የሚጠይቅ ነው። በሚጋረፈው የበረሃ ሙቀት፣ በሰው ብዛት በተጨናነቀ ሥፍራ ሥነ ሥርዓቱ በሚከናወንባቸው ቦታዎች ለመድረስ ረጅም ርቀት መጓዝ ሰውነትን የሚፈትን ነው።
በባለፈው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዓት ቢያንስ 1300 ሰዎች መሞታቸውን ሳዑዲ አረቢያ አስታውቃለች። አብዛኞቹም ሕይወታቸው ያለፈው በከፍተኛ ሙቀት ረጅም ርቀት ከተጓዙ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት የሐጅ ጉዞ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል ተብሎ ይገመታል።
ታዲያ በእንደዚህ ዓይነት እጅግ የተለየ የእምነት ሥፍራ ጤናችሁን ጠብቃችሁ ለመቆየት የሚያስችላችሁን የተወሰኑ ጠቃሚ ምክሮች እነሆ።

በሳዑዲ አረቢያ መሬት ላይ በባዶ እግራችሁ ከመረማመዳችሁ በፊት አስቀድሞ መዘጋጀት ወሳኝ ነው።
በተለይም አረጋውያን እንዲሁም እንደ ስኳር፣ አስም፣ ካንሰር እና የልብ በሽታ ያሉ ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ተጓዦች አስቀድመው ሙሉ አካላዊ ጤንነታቸውን እንዲመረመሩ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በሳዑዲ መንግሥት የሚጠየቀውን ሁሉንም አስገዳጅ ክትባቶች መውሰድ ያስፈልጋል። ይህም የማጅራት ገትር በሽታን ክትባት ይጨምራል።
ክትባቱ ሐጅ የሃይማኖቱ ተከታዮች ሳዑዲ ከመድረሳቸው በፊት ቢያንስ ከአስር ቀን ቀደም ብሎ መወሰድ ይኖርበታል- የኮቪድ -19 ክትባትም እንዲሁ።
የፖሊዮ እና የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ካለባቸው አገራት የሚጓዙ መንገደኞችም ክትባታቸውን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ከጉዞ በፊት
እጅግ በርካታ ሰዎች የሐጅ ጉዞ ስለሚያደርጉ በአካባቢው ያሉ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከአቅማቸው በላይ ይጨናነቃሉ። በመሆኑም በተቻለ መጠን ራስን መቻል ብልህነት ነው ይላሉ የጤና ባለሙያዎች።
በሐኪም የታዘዘለዎት መድኃኒት ካለ በቆይታዎ ወቅት የሚበቃዎትን ያህል መያዝዎን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
የህመም ማስታገሻዎች፣ የተቅማጥ መድኃኒት፣ ለቀላል ጉዳቶች የሚያገለግል የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ቁሳቁሶች፣ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ አልኮል እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መያዝ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በተለይም በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ረጅም ርቀት የእግር ጉዞ የማድረግ ልምድ የሌላቸው ተጓዦች አስቀድመው አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመከራል።
ሐጅ በመካ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ ቀናት በሚፈፀሙ የእምነቱ ሥነ ሥርዓቶች የሚከወን ነው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝም በአማካኝ በቀን ውስጥ ከ5 እስከ 13 ኪሎ ሜትር በእግር መጓዝን ይጠይቃል።
በመሆኑም አካላዊ እና አእምሯዊ ጥንካሬን ይዞ ለመቆየት እና ጉዳቶችን ለመቀነስ ቢያንስ ከሦስት ሳምንት ቀደም ብሎ ከቀላል እስከ መካከለኛ የሚደርሱ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሰውነትን ማለማመድ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ከፍተኛ ሙቀትን መቋቋም
የሳዑዲ አረቢያ የሙቀት መጠን እስከ 51 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል። ይህም ከጋለ ምድጃ (ኦቭን) ፊት ለፊት እንደመቆም ማለት ነው። በዚህ ከፍተኛ ሙቀት ሰውነት ራሱን ለማቀዝቀዝ ትግል ውስጥ ይገባል። ይህም የሰውነት መዛልን፣ ድካምን ሲከፋም የሙቀት ስትሮክ [ሂት ስትሮክ] ሊያስከትል ይችላል።
ምንም እንኳን የሳዑዲ የጤና ሚኒስትር “ራሳችሁን ለሙቀት አታጋልጡ፣ በቂ ፈሳሽ ውሰዱ” ሲል ማስጠንቀቂያዎችን ቢሰጥም፣ በርካታ ተጓዦች የሂት ስትሮክ ሰለባ ይሆናሉ።
በዚህ ዓመት የአገሪቱ መንግሥት የጤና ባለሙያዎቹን ቁጥር መጨመሩን እና 400 የሚሆኑ የውሃ ማቀዝቀዣዎችን እንዲሁም ተጓዦች ራሳቸውን በውሃ የሚያቀዘቅዙበት የውሃ ቱቦቾችን ማዘጋጀቱን ገልጿል።
የሳዑዲ አረቢያ የሕብረተሰብ ጤና መሥሪያ ቤት ምክትል ሚኒስትር አብዱላህ አስሪ “በዚህ ዓመት ትኩረታችን ከሙቀት ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ላይ ነው። ምክንያቱም የሐጅ ወቅት ከፍተኛ ሙቀት ካለበት ጊዜ ጋር ተገናኝቷል። በዚህ ዓመት የሙቀቱ መጠንም ከፍተኛ ነው” ሲሉ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በመሆኑም ተጓዦች ውሃ ባይጠማቸውም በተደጋጋሚ በቂ ፈሳሽ እንዲወስዱ እና ከፕላስቲክ ይልቅ በሚያቀዘቅዙ ኮዳዎች ውሃ እንዲይዙ ይመከራሉ።
ከቤት ውጪ የሚያሳልፉትን ሰዓት መምረጥም ሙቀቱ የሚያይልበትን ጊዜ ተጠልሎ ለማሳለፍ ይረዳል። በዚህም ከረፋድ 5፡00 እስከ 9፡00 ሰዓት ድረስ መጠለያ ውስጥ መቆየት ይመከራል።
የተጨናነቁ ቦታዎች ማስወገድ እና መጠለያ ጥላዎች (ሼድ) አሊያም በቂ አየር የሚያገኙ ቦታዎችን መምረጥም ከመተፋፈግ ያድናል።
የፀሐይ መከላከያ (ሰን ስክሪን) መጠቀም እና በየሁለት ሰዓት ልዩነቱ መቀባት ቆዳ በፀሐይ እንዳይቃጠል ይረዳል። አየር የሚያስገቡ እና ብርሃናማ ቀለም ያላቸው ልብሶችን መልበስም ፀሐይን አንፀባርቀው የመመለስ ባህርይ ስላላቸው ሰውነትን ለማቀዝቀዝ ይረዳሉ።
አየር የሚያስገቡ እና የሚመቹ ጫማዎች ማድረግ እንዲሁም ደማቅ ቀለም እና ፀሐይን አንፀባርቆ የሚመለስ ጃንጥላ መያዝም ይመከራል።
ሆኖም የድካም፣ የሰውነት መዛል እና የማቅለሽለሽ ስሜት ከተሰማ ችላ እንዳይሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ምልክቶች አደገኛ የጤና ሁኔታን የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ።
በተጨናነቀ ሥፍራ ደኅንነትን መጠበቅ

ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአንድ ላይ ሲሰባሰቡ የበሽታ መስፋፋት አደጋ ይጨምራል። የንጽህና ጉድለት አሊያም ቀላል ሳል ወደ ወረርሽኝ ሊቀየር ይችላል።
በሽታዎችን ለመከላከል ተጓዦች እጃቸውን በውሃ እና በሳሙና በደንብ መታጠብ አሊያም የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም አለባቸው።
የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግም በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳል። አብዛኞቹ ቤቶች እና መጠለያዎች የአየር ማቀዝቀዣ ስላላቸው ማስክ ማድረግ ያን ያህል ከባድ አይሆንም።
ከባለሥልጣናት የሚተላለፉ መልዕክቶችን መከታተልም ያስፈልጋል። የሳዑዲ ባለሥልጣናት አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ እና መጨናነቅ በሚፈጠርበት ወቅት የጤና እና የአየር ሁኔታ መረጃዎችን ለመስጠት ሥርዓት መዘርጋታቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህም ባሻገር የአደጋ ጊዜ ተጠሪ አድራሻ እና የሕክምና ታሪክዎን የሚያሳዩ መረጃዎች ሁልጊዜም እንዳይለይዎ ይመከራል። በአቅራቢያ ያለ የጤና ተቋም መገኛንም ማወቅ ወሳኝ ነው።
ሐጅ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚደረግ ሃይማኖታዊ ጉዞ ነው። በመሆኑም ተጓዦች ሥነ ሥርዓቱን እንድትፈፅሙ መንፈሳዊ የሆኑ ግፊቶች ቢኖሩም ሰውነታችሁን ማዳመጥ እና ለጤናችሁ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባችሁ ባለሙያዎች ይመክራሉ።