
ከ 3 ሰአት በፊት
የዓለማችን ባለጸጋ እና ኃያል የፖለቲካ ሰው ፍልሚያ ሲገጥም የሚፈጠረው ምንድን ነው?
አሁን ዓለም እያየው ያለው ይመስላል፤ ግን ምንም የሚያስደስት ነገር የለውም።
ዶናልድ ትራምፕ እና ኤሎን መስክ ሁለት ጥብቅ ወዳጆች አሁን እርስ በእርስ እየተነቋቆሩ ነው።
አለመግባባታቸው ወደ ከረረ የቃላት ጦርነት ለመለወጥ ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም።
ትራምፕ መስክን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለውን የሥራ ውል፣ ለስፔስ ኤክስ የደም ስር የሆነውን የንግድ ስምምነት ለማቋረጥ አስፈራርተዋል።
“በበጀታችን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ገንዘብ ለመቆጠብ ቀላሉ መንገድ ለኤሎን የምንሰጠውን ድጎማ እና ውሎችን ማቋረጥ ነው” ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ትራምፕ መንግሥታቸው ፊቱን በመስክ ላይ ማዞር ከቻሉ ቢሊየነሩ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል።
ሐሙስ ዕለት እንኳ መስክ ከትራምፕ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ እያለ የቴስላ ድርሻ በ14 በመቶ ወርዷል።
የመጫወቻ ሜዳው ግን ለትራምፕ ብቻ ክፍት የሆነ አይደለም። መስክም በቻለው አቅም ያለውን የመከላከያ ቡጢ እየተጠቀመ ነው።
አሜሪካ ወደ ዓለም አቀፉ የህዋ ማዕከል የተለያዩ መሳሪያዎችን እና ጠፈርተኞችን ለማጓጓዝ አብዝታ ከምትጠቀምበት ስፔስ ኤክስ ጋር ያላት ውል አንዲቋረጥ እንደሚያደርጉ ሲዝቱ እርሱ ደግሞ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው ሲል ተናግሯል።
መስክ ሌላው በዚህ የቃላት ጦርነት ውስጥ ለውጊያ የሚጠቀመው በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ምርጫ የትራምፕ ተቀናቃኞችን ለመደገፍ ሀብቱን ማፍሰስ ነው።
በወሲብ ቅሌት ወደ ዘብጥያ ወርዶ ሕይወቱ በዚያው ካለፈው ጄፍሪ ኢፕስቴይን ጋር በተያያዘ ይፋ ባልሆኑ መዝገቦች ላይ የትራምፕ ስም እንደሚገኝ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ያለ በቂ ማስረጃ ተናግሯል።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮላይን ሌቪት ለመስክ ክሶች እና ውንጀላዎች የተቀዛቀዘ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ይህ በሕጉ [የግብር እና የወጪ ሕግ] ደስተኛ ያልሆነው የኤሎን አሳዛኝ ክስተት ነው። ምክንያቱም [ሕጉ] እሱ የሚፈልጋቸውን ፖሊሲዎች አያካትትም” ትላለች።
መስክ የትራምፕን መንግሥት ታግሎ ማሸነፍ አይችል ይሆናል። ነገር ግን ትራምፕንም ሆነ ሪፐብሊካን ፓርቲን ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል።
ትርምፕም ይህ የጠፋቸው አይመስልም።
ትናንት ሐሙስ በዋይት ሐውስ ፖሊሲዎቻቸውን በሚመለከት በተዘጋጀ የምስጋና እና የአድናቆት ዝግጅት ላይ ጉዳዩን ቀዝቀዝ አድርገው አስተያየት ከመስጠት በመቆጠብ ያለፉት ሲሆን፣ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸውም ላይ “በእርሱ ላይ ለመነሳት” ግድ የማይሰጣቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከወራት በፊት ግን በመንግሥታቸው ውስጥ መልካም ሥራ መሥራቱን ጠቅሰዋል።
ከዘያም አዲሱን የግብር እና የወጪ ሕግ ማድነቃቸውን ቀጥለዋል።
ይሁን እንጂ ሐሙስ ዕለት ከነበረው የተሟሟቀ ምልልስ በኋላ ቀጣዩ ጊዜ እንዲሁ እንደዋዛ የሚታለፍ አለመሆኑን አሳይቷል።
የስድብ እና የዛቻ ምልልስ
ፍጥጫው የጀመረው ባለፈው ሳምንት ሞቅ ባለ ፍጥነት ነበር።
ረቡዕ ዕለት መጋጋል ጀምሮ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት [ኦቫል ኦፊስ] ውስጥ ሙሉ በሙሉ ፈነዳ።
አዲሱ የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪክ መርትዝ ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት ዋሺንግተን መጥተው ምቾት በሚነሳ ዝምታ ውስጥ ተቀምጠው ሳለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ ጣል ጣል የተደረገ አፍቃሪ ይመስሉ ነበር።
መስክ በሕጉ ላይ ባቀረበው ትችት የተገረሙ ይመስላሉ። መስክ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ድጋፍ ባያደርግ ኖሮ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይሸነፉ ነበር ሲል የሰጠውን ሃሳብ አጣጥለውታል።
መስክ ወዲያውኑ እንደ ዘመኑ ልጆች 220 ሚሊዮን ተከታዮች ወዳሉት የኤክስ ገፁ በመምጣት “ምንም ይሁን” ሲል ለጥፏል።
አክሎም በሚያመርተው መኪናው ላይ ስለሚደረገው ድጎማ ግድ እንደማይሰጠው ገልፆ፣ የብሔራዊ ሕልውና አደጋ ሲል የጠራውን የብሔራዊ ዕዳን መቀነስ እንደሚፈልግ ተናግሯል።
ባለፈው ዓመት ያለእርሱ ድጋፍ ዲሞክራቶች ያሸንፉ እንደነበር ጠቅሶ “አመስጋኝ አለመሆን ነው” ሲል ለትራምፕ ምላሽ ሰጥቷል።

ቢሊየነሩ ከዚህ በኋላ ሐሙስ ከሰዓት ያልተለመዱ በርካታ የቃላት ጥቃቶችን ከሰነዘረ በኋላ ፍጥጫው በርትቷል።
መስክ እና ትራምፕ ኃይለኛ ግን የማያዛልቅ ጥምረት ፈጥረው ነበር።
ይህ ወዳጅነትም ቢሊየነሩ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የበጀት ቅነሳ ሥልጣን ላይ ቁልፍ ቦታ እንዲኖረው አድርጓል።
የመስክ የመንግሥት ቅልጥፍና መሥሪያ ቤት ወይም ዶጅ፣ ሁሉንምየመንግሥት ተቋማትን በመዝጋቱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን በማሰናበት በትራምፕ የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ አንዱ ትልቁ ስኬት ሆኖ ተጠቅሷል።
ብዙም ሳይቆይ፣ መቼ እና እንዴት እንደሆነ በቅጡ ባይታወቅም ሁለቱ ኃያላን ግለሰቦች መንገዳቸው እየተለያየ፣ ንግግራቸው እያልተታጣመ መጣ። ይህንን የታዘቡም የእነዚህ ኃያላን ጥምረት ንፋስ እየገባው ነው አሉ።
ለተወሰነ ጊዜ የእነዚህ ግለሰቦች ትንበያ እውነት ሳይመስል ቀረ።
ትራምፕ የሁለቱ ወዳጆች ፍቅር እያሽቆለቆለ በነበረበት ጊዜ እንኳ፣ መስክ ከአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ጋር ሲጋጭ እና በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ በበርካታ ቁልፍ ምርጫዎች ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፣ ከመስክ ጎን ቆመዋል።

ከዚህ ሁሉ እረፍት ይኖራል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ ሁሉ መስክ በኦቫል ኦፊስ ወይም ፕሬዝዳንቱ ወደ ማር-አ-ላጎ በሚያደርጉት በረራ ላይ ይገኛል።
የመስክ 130 ቀናት እንደ “ልዩ የመንግሥት ሠራተኛ” ያሳለፈው ሳምንት ሲያልቅ፣ ሁለቱ በኦቫል ኦፊስ በፈገግታ የታጀበ ሽኝት ነበር ያደረጉት።
ዋይት ሐውስ ለመስክ ምንጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን በመናገር አንድ ቀን ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው ነበር።
አሁን ግን ግብዣው ተሰርዟል፤ የዋይት ሐውስ በር መክፈቻ ቁልፍም ተለውጧል ብሎ መናገር ስህተት አይሆንም።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በንግግራቸው “ኤሎን እና እኔ ጥሩ ግንኙነት ነበረን” ሲሉ ያለፈ ጊዜ አገላለጽን ተጠቅመው ተናግረዋል።
ትራምፕ ረቡዕ ምሽት አዲስ የጉዞ እገዳ መጣላቸው፣ በሐርቫርድ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች ማስቀመጣቸው እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ላይ ምርመራ እንደሚደረግ በሚመለከት የሰጧቸው መግለጫዎች ጉዳዩን ከመስክ ትችት ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች ናቸው የሚል ግምት አለ።
በዋይት ሐውስ እና በኮንግረሱ ውስጥ ያሉ አጋሮቻቸው ከዚህ ቀደም ከሰጠው አስተያየት በኋላ እሱን የበለጠ ላለማግኘት ጥንቃቄ ያደረጉ ይመስላል።
ከዚያ ትረምፕ ተናገሩ. . . ብዙ!
የዜሮ ድምር ጨዋታ
አሁን ጥያቄው ክርክሩ ወዴት ይሄዳል የሚለው ነው። መስክ በሚያደርገው ንግግር፣ በሚደግፈው ገንዘብ የተነሳ የኮንግረሱ ሪፐብሊካኖች አባላቶቻቸውን ከትራምፕ ሕግ ጎን እንዲቆዩ ማድረግ ሊቸግራቸው ይችላል።
ትራምፕ መስክን ከመንግሥት ጋር ያሉትን ኮንትራቶች ለማቋረጥ አስቀድመው ዝተዋል።
ነገር ግን በአስተዳደሩ ውስጥ ባሉት የመስክን የዶጅ አጋሮች ላይ ሊያነጣጥሩ ወይም ባይደን በመስክ ላይ ጀምረዋቸው የነበሩት የንግድ ግንኙነቶች ምርመራን ዳግም ሊያንቀሳቅሱት ይችላሉ።
በዚህ ጊዜ ሁሉም ነገር በአማራጭነት በጠረጴዛው ላይ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዲሞክራቶች እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ በማሰብ ከዳር ቆመዋል።
ለፓርቲያቸው የቀድሞ ለጋሽ የሆነውን መስክን ወደ ቤታቸው ለመጋበዝ የፈለጉ ጥቂቶች አይደሉም።
ግን የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለው የድሮ አባባልም አለ።
የዴሞክራቲክ ስትራተጂስት ሊአም ኬር ‘ፖሊቲኮ’ ለተባለው ታዋቂ ድረ ገጽ እንደተናገረው “የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው። ወደ ዲሞክራቶች የበለጠ የሚጠጋ ማንኛውም ነገር ሪፐብሊካኖችን ይጎዳል።”
ቢያንስ፣ ዲሞክራቶች ዳር ቆመው ሁለቱ ሰዎች በቃላት ሲጠዛጠዙ በመመልከት እየተዝናኑ ይመስላል።
እናም ይህ ፍልሚያ እስኪያበቃ ድረስ የሁለቱ ወዳጆች ጠብ የአሜሪካን ፖለቲካ ሁሉንም ነገር ሊያሰጥም ይችላል።
ይህ ፍጥጫ በቅርቡ ያበቃል ተብሎ አይጠበቅም።
መስክ በኤክስ ገፁ ላይ “የትራምፕ ፕሬዝዳንትነት 3.5 ዓመታት ቀርተውታል፣ እኔ ግን ከ40 ከተጨማሪ ዓመታት በላይ እኖራለሁ” ሲል ጽፏል።
ዕድሜ ይስጠን ሁሉንም እናያለን!!