ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ከ 4 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው “ዕድገት ሳይሆን ሚራክል [ተዓምር] ነው” ሲሉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ያሉት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ላይ በአራት ተከታታይ ክፍል እየተላለፈ በሚገኘው ቃለ ምልልሳቸው ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሙስ ምሽት በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው ላይ ስለ ምጣኔ ኃብት እና የሠራተኞች የደመወዝ ጥያቄን አንስተው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም መምህራን ያነሷቸውን የደመወዝ ጥያቄዎች “ሌጂትሜት [ትክክለኛ] ናቸው” ያሉ ሲሆን “ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች፣ ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ ሚኒስትሮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁላችንም የደሞዝ ጥያቄ አለን” ብለዋል።

በአገሪቱ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች የደሞዝ፣ የጥቅማ ጥቅም እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በርካታ የሕክምና ተቋማት እየተሰጠ ያለው አገለግሎት አሁን ድረስ መስተጓጎል እንደገጠመው ይታወቃል።

ባለሙያዎቹ ላሏቸው ጥያቄዎች ከመንግሥት ተገቢ ምላሽ አላገኘንም በማለት አሁንም ውይይት በማድረግ መፍትሄ እንዲፈለግ እየጠየቁ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዕድገት አንስተው በተናገሩበት ወቅት “እያደግን ነው ኢንፊሌሽን [የዋጋ ግሽበት] ለመግታት እየሠራን ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሰባት ዓመታት የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እያለ ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግበናል በማለት መጥቷል ያሉትን ዕድገት “ሚራክል” [ተዓምር] ሲሉ ጠርተውታል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሳይሆን፣ እኛ ለውጥ ልናመጣ ካሰብነው ፍጥነት እና ጥራት በላይ ነው ለውጥ የመጣው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን መጠበቅ ካልተቻለ “አደገኛ ጣጣ ሊያመጣብን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይኑ እንዲገለጥ ልቦናው እንዲከፈት ያገኘውን መልካም ዕድል፣ ያገኘውን የተከፈተ ብርሃን በማስተዋል እንዲጠቀምበት ከከፍተኛ ማሳሰቢያም ጭምር ነው አሁን የማነሳውን ሃሳብ የማነሳው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ላይ “ሚራክል” ላሉት ዕደገት ማሳያዎችን የጠቀሱ ሲሆን ከ1984 ዓ.ም. እስከ 1998 ዓ.ም. ባሉት 15 ዓመታት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የተገኘው ገቢ 7. 5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር ብለዋል።

“ዘንድሮ በአንድ ዓመት 8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ከኤክስፖርት [ኢትዮጵያ] ታገኛለች። በአንድ ዓመት 8 ቢሊዮን ዶላር የምታገኝ አገር 15 ዓመት ሙሉ ምን ትሠራ ነበር ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ዓመት ሲጀመር “የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ነው ብዬ ነበር” ያሉት ዐቢይ አሕመድ፣ “ዘንድሮ እኮ ከፍተኛ የማንሰራራት ዓመት ነው። ዘንድሮን አራት አምስት አስር ዓመት ከደገመች ኢትዮጵያ አበቃ። መከራዋ አበቃ” ሲሉም ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ ባለፉት 15 ዓመታት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው የቡና ምርት ያገኘችው ገቢ 3.5 ቢሊዮን ዶላር እንደነበረ እና “ዘንድሮ በአንድ ዓመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ሸጣለች። ምን ማለት ነው? በ2 ዓመት ውስጥ 5 ቢሊዮን ብትሸጥ በ15 ዓመት ውስጥ ከሸጠችው በብዙ የበለጠ ማለት ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይም 15 ዓመታት ውስጥ ከወርቅ ሽያጭ የተገኘውን ገቢ ለንጽጽር አቅርበው 508 ሚሊዮን ዶላር ከኤክስፖርት ተገኝቶ እንደነበረ እና “ዘንድሮ 3.2 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች” ሲሊ ከፍተኛ እመርታ መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይኼን የመሰለ ዕድገት እያመጣን በተመሳሳይ ‘የኢትዮጵያ ኢንፊሌሸን ከ30 ምናምን ገደማ 13.5 ወርዷል” ሲሉም ተናግረዋል።”

ባለፈው ዓመት የውጭ ምንዛሪ ተመን በገቢያ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የተዳከመ ሲሆን፣ ይህም በገበያ ላይ የምርት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማስከተሉ ሲነገር ቆይቷል።

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ወደ 54 ብር ገደማ የነበረው የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ በአሁኑ ወቅት በይፋዊው ገበያ ወደ 130 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ በትይዩው ገበያ ግን ወደ ከ150 በላይ መድረሱ ይነገራል።

በተመሳሳይ በየጊዜ ው መንግሥት ለነዳጅ የሚሰጠው ድጎማ ከመነሳቱ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት፣ የሸቀጦች እና የአገለግሎት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪን በማሳየቱ የኑሮ ውድነት እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኑሮ ውድነት እና ስለሚነሱ የደመወዝ ጥያቄዎች ሲያስረዱም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ “የኑሮ ዘያችን በግራም በቀኝም ተነካክቷል” ካሉ በኋላ “በዚያ ምክንያት የሚፈተኑ ሰዎች አሉ። የሚቸገሩ ሰዎች አሉ” ብለዋል።

በቅርቡ የሕክምና ባለሙያዎች ያነሱትን የደሞዝ ጥያቄ “ምንም ጥያቄ የለውም ከደሞዝ ጋር የሚያያዝ ችግር አለብን ‘ሌጂትሜት’ ነው።. . . ነገር ግን የተለየ አይደለም። ብዙዎቻችንን የሚነካ ነገር ነው” ብለዋል።

ይህንን የደመወዝ ጥያቄ ለመፍታት ግን “ማስተዋል፣ መስከን፣ ማሰብ ይስፈልጋል” በማለት ይህንን “ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም የሚፈልጉ” ሰዎች እንዳሉ ታይተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄያቸው ከምንም ዓይነት የፖለቲካ ጋር እንደማይያያዝ የጤና ባለሙያዎቹ በተደጋጋሚ ቢገልጹም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎችም ባለሥልጣናት ጥያቄው የሌሎች መጠቀሚያ ሆኗል ሲሉ ይከሳሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ባለፉት ሳምንታት በርካታ የጤና ባለሙያዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲዘገብ የነበረ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስም ወደ 50 የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች “ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ያበሩ” በሚል መያዙን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዓመት ደሞዝ ላይ ጭማሪ ያስፈልጋል በማለት 91 ቢሊዮን ብር መንግሥት መጨመሩን በመጥቀስ “91 ቢሊዮን ብር በዓመት ከመመደብ በላይ ኢትዮጵያ አቅም የላትም” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ደመወዝ በቂ አይደለም። የኔ ደሞዝ በቂ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዘንድሮ የፌደራል መንግሥት ሠራተኛ ደመዝ የሚከፍለው 450 ቢሊዮን ብር በልጧል። ከምናስገባው ገቢ አምና ሳይሆን ዘንድሮ ከምናስገባው ገቢ ግማሹ የሚውለው ለደሞዝ ነው። 900 ቢሊዮን ገደማ ብር እንጠብቃለን ግማሹ ደመወዝ ነው” ብለዋል።

መንግሥት ይህ ጥያቄ በጩኸት ይመለሳል ብሎ እንደማያምን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በሰከነ መንገድ አቅማችንን እያገናዘብን ምላሽ እየሰጠን መሄድ ያስፈልጋል። ይህንን ጉዳይ ግን ከስክነት ከውይይት ከምክክር ከየት እንደምናመጣው ከማሰብ ውጪ መልስ አይገኝለትም” ብለዋል።

“ብንጮህ እና ብናበላሽ እናጠፋዋለን እንጂ አናለማውም። የጀመርናትን ጭላንጭል እናወድማታለን እንጂ ውጤት አናመጣበትም” በማለት በውይይት እና ሁለቱንም ወገኖች አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ “መፍትሄ እያበጀንለት እንሄዳለን” ብለዋል።