
ከ 4 ሰአት በፊት
መንግሥት ለተጠቃሚዎች በነጻ ይሰጥ የነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በክፍያ እንዲሆን እና የግል ዘርፍ ተዋንያን እንዲሳተፉበት የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 19/2017 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ “ባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር” አዋጅ ይሰኛል።
ረቂቅ አዋጁ በስድስት ክፍሎች እና በአርባ አንቀጾች የተዘጋጀ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል ትርጓሜ እና የተፈጻሚነት ወሰንን ጨምሮ ጠቅላላ ድንጋጌዎችን ይዟል።
ረቂቅ አዋጁ ለ’የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት’ የሚሰጠው ትርጓሜ “የግብርና ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ፣ ማስፋፋት፣ ቢዝነስ ልማት የማማከር፣ መረጃ አቅርቦት፣ የሥልጠና አገልግሎት” የሚል ነው።
“የባለድርሻ አካላት ትስስር መፍጠር እና ማስተባበር፤ የግብርና ግብዓትና ምርት ገበያ ትስስር እና የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸት” እንዲሁ የአግልግሎቱ ትርጓሜ ነው።
በረቂቁ አዋጁ የትርጓሜ ክፍል “አነስተኛ ይዞታ ያለው አርሶ አደር፣ አርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር፣ የከተማ ወይም በመካከለኛ ወይም በሰፋፊ ግብርና ልማት ሥራ የተሰማራ አርሶ አደር” የዚህ አገልግሎት ‘ተጠቃሚ’ ተብለው ተዘርዝረዋል።
የረቂቁ ሁለተኛ ክፍል የአገልግሎት አቅራቢ፣ የአገልግሎት ዓይነት እና የክፍያ አሠራርን የተመለከቱ ስምንት አንቀጾችን ይዟል።
የመንግሥት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና መንግሥታዊ ያልሆነ አገልግሎት አቅራቢዎች እንዳሉ በዚህኛው ክፍል ሰፍሯል።
የቀበሌ ወይም ወረዳ ጽህፈት ቤት፣ ማዕከል፣ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት የግብርና ልማት ድርጅቶች፣ የመንግሥት አግልግሎት አቅራቢ ተብለው በረቂቁ ተዘርዝረዋል።
በረቂቁ መሠረት የመንግሥት አገልግሎት በግብርና ሚኒስቴር ወይም በክልል ቢሮዎች አስተባባሪነት እንደሚደራጅ ረቂቁ ያትታል።
በረቂቁ መሠረት በሚኒስቴሩ፣ በክልል፣ በወረዳ፣ በከተማ፣ በአርሶ አደር ወይም በአርብቶ አደር ወይም ከፊል አርብቶ አደር ማሠሰልጠኛ ማዕከል፤ በእንሰሳት ጤና አገልግሎት ማዕከል የመንግሥት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ይደራጃል።
ይኸው የረቂቁ ክፍል ሰባት መንግሥታዊ ያልሆኑ አግልግሎት አቅራቢዎችን ዘርዝሯል።
ከእነዚህ አቅራቢዎች መካከል ሀገር በቀል፣ አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፍ የምርምር ማዕከል፣ የግል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አቅራቢ፤ የዘርፍ ወይም የሙያ ማኅበር እና የሕብረት ሥራ ማኅበር ይገኙበታል። በተጨማሪም የሲቪክ ማኅበር፣ የግል የግብርና ምርት አምራች ወይም አቀነባባሪ ድርጅት እንዲሁም የግል የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትንም ያካትታል።
የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ሲሰጥ የነበረው በመንግሥት በሚመደብ በጀት” እንደነበር ያትታል።
ይህን ለማድርግ “ከመቶ ሺህ በላይ” የልማት ሠራተኞች ከተለያዩ የሙያ እና የትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች መመረቃቸውን የጠቆመው ማብራሪያው አሁን አገልግሎቱ “ከ60 ሺህ ባላነሱ የልማት ሠራተኞች” እየተሰጠ መሆኑን ያክላል።
ማብራሪያው “እያደገ ከመጣው የኤክስቴሽን አገልግሎት ፍላጎት እና ስትራቴጂክ ግቦች አንፃር በመንግሥት ብቻ የሚሰጠው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በቂ አንዳልሆነ እና ብዙ ተዋንያንን ያሳተፈ የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ [ነው]” ሲል መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት አገልግሎት እንዲያቀርቡ የተደረገበተን አመክንዮ ያብራራል።
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት “ሙሉ በሙሉ መንግሥታዊ እና በነጻ ይሰጥ የነበረ” መሆኑን ያስታወሰው ማብራሪያው፤ ነገር ግን “ሌሎች ተዋንያንም በተለያየ መልኩ ተጠያቂነትን በማያረጋግጥ መልክ ሊሰጡ እንደነበር” ጠቅሷል።
ከዚህ በኋላ ግን “ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ በክፍያም ጭምር አገልግሎቱ እንዲሰጥ ታምኖበት” አዋጁ መዘጋጀቱን ይክላል።
ረቂቁ ሌላው ያነሳው ጉዳይ የአገልግሎት አቅራቢ ስምሪት እና ኃላፊነትን ነው። በረቂቁ መሠረት የመንግሥት የአገልግሎት አቅራቢ በተሰማራበት አካባቢ ለሁሉም ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል።

የግል አገልግሎት አቅራቢዎች በበኩላቸው “ከመንግሥት ጋር በሚፈጸም የውል ሰምምነት መሠረት የመንግሥትን ፕሮጀክት ኤክስቴንሽን ተግባራዊ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ በራሳቸው ፋይናንስ የሚደገፍ ከሆነ “አዋጭነትን መሠረት በማድረግ እና የክልል ቢሮን በማሳወቅ ብቻ” በሚፈልጉት አካባቢ መሰማራት ይችላሉ።
ለግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የሚደረግ ክፍያን በተመለከተ ረቂቁ “የመንግሥት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለሁሉም ተጠቃሚ በሁሉም ቦታ ያለክፍያ ይሰጣል” የሚል ድንጋጌ ይዟል።
ነገር ግን በመንግሥት ለሚሰጡ እና “ከፍተኛ ኢንቨስትመነት ለሚጠይቁ፣ የዕውቀት እና የክህሎት ሽግግር ለሚፈልጉ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቶች የክፍያ ሁኔታ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ይወሰናል” ይላል።
ማብራሪያው ይህን ድንጋጌ የተካተተው “የክህሎት ባለቤት የሚሆኑ ተገልጋዮች ይህን ዕውቀት ወይም ክህሎት እንደ አንድ ገቢ ማስገኛ ሥራ ተጠቅመው ተጨማሪ ገቢ ሊስገኝላቸው [የሚችል በመሆኑ ነው]” ሲል ያስረዳል።
በሌላ በኩል መንግሥታዊ ያልሆኑ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አቅራቢዎች አግልግሎታቸውን በሦስት የክፍያ አማራጮች መስጠት ይችላሉ።
እነዚህ የክፍያ አማራጮች [በቀጥታ] ክፍያ፤ በክፍያ መጋራት፤ በሚቀርበው የግብርና ቴክኖሎጂ ወይም ግብዓት ተካቶ የሚከፈል መሆኑ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
ማብራሪያ “አሁን በሥራ ላይ ካለው የኤክስቴሽን አገልግሎት እና የሌሎች ተዋንያን ድጋፍ የተነሳ የተጠቃሚው ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት እያደገ በመምጣቱ አገልግሎቱን ከፍሎ ለማግኘት ፍላጎት እያሳየ ይገኛል” ይላል።
በተጨማሪም “በአገራችን የተካሄዱ አንዳንድ ጥናቶች የሚያመላክቱት አርሶ/አርብቶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ብቃታቸውን ለሚያሻሽል አገልግሎት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን ነው” ሲል ተጨማሪ አመክንዮ ያስቀምጣል።
በረቂቁ መሠረት መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎት አቅራቢዎች “የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ያለክፍያ መስጠት የሚፈልጉ አይከለከሉም።”
“መንግሥታዊ ባልሆነ አገልግሎት አቅራቢ ለሚቀርብ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተገቢ ያልሆነ አከፋፈል ከተከሰተ” መንግሥት “የማረጋጋት ተግባራት ማከናወን የሚያስችለውን አማራጭ መፍትሄዎችን” ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚችል ረቂቁ አመልክቷል።
“የግል ዘርፉ በሚሰጠው አገልግሎት የሚያስከፍለው ዋጋ እየጨመረ አንጂ እየቀነሰ አንደማይሄድ” የጠቆመው ማብራሪያው፤ “ለተጋነነ የክፍያ ሁኔታ እንዳይጋለጥ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ታምኖበታል። ስለዚህም መንግሥት ዋጋ ማረጋጊያ ተግባራትን ሊያከናውን አንደሚችል ተደንግጓል” ይላል።
በረቂቁ የሰፈረው ሌላኛው ጉዳይ ምዝገባ፣ የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ እና የአገልግሎት ጥራት ቁጥጥር ነው።
በአገልግሎት አቅራቢነት ከአንድ ክልል በላይ ለመሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን መመዝገብ እና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘት እንዳለበት ረቂቁ ያስገድዳል።
በአንድ ክልል ተወስኖ የሚሠራ አግልግሎት አቅራቢ በሌላ በኩል በክልል ባለሥልጣን መመዝገብ እና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘት አለበት።
ረቂቅ አዋጁ የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ የፕሮጀክት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የግብርና ኤክስቴንሽን ፈንድ እንደሚቋቋም ተጠቅሷል።
የፈንዱ የፋይናንስ ሃብት ከግል፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከበጎ አድራጊዎች፣ ከልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች እንደሚሰበሰብ ረቂቄ ላይ ሰፍሯል።
የፈንዱ ምንጮች የተለዩት “እስከአሁን በተገኘ ልምድ መሠረት” መሆኑንም የረቂቁ ማብራሪያ ያስረዳል።
ፈንዱ “የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች አገልግሎት ለመስጠት” ጥቅም ላይ አንደሚውል ተመልክቷል።
የኤክስቴንሽን መሠረተ ልማት፣ የሎጅስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅምን መገንባት እንዲሁም የኤክስቴንሽን ሥርዓቱን በቴክኒክ እና በአሠራር ማዘመን ፈንዱ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልባቸው ሌሎች ተግባራት ናቸው።
የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ፈንድን የሚያስተዳድር ጽህፈት ቤት በስሩ እንደሚያደራጅ ረቂቁ ላይ ሰፈሯል።