
ከ 2 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አራት ዳኞች “ያለ አግባብ” እስራኤል እና አሜሪካ ላይ በማነጣጠራቸው ማዕቀብ እንደሚጥሉባቸው አስታወቁ።
ማዕቀቡ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቤንያሚን ኔታንያሁንን ጨምሮ የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ላወጣው የእስር ማዘዣ እና አሜሪካ በአፍጋኒስታን ጦርነት ፈጽመዋላች ለተባለው የጦር ወንጀል ምርመራ እንዲደረግ ማዘዙን ተከትሎ የሚጣል ነው።
ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያሉት አራት ዳኞች ሁሉም ሴቶች ናቸው።
የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኞቹ ኡጋንዳዊቷ ሶሎሚ ባሉንጊ ቦሳ፣ ሉዝ ዴል አከርመን ኢባኔዝ ካራንዛ ከፔሩ፣ ቤኒናዊቷ ሬኒ አዴላዴ ሶፊ አላፒኒ ጋነሶኡ እንዲሁም የስሎቫኒያ ዜጋ የሆኑት ቤቲ ሆህለር ናቸው።
አይሲሲ በአሜሪካ የተላላፈውን ውሳኔ በተመለከተ ማዕቀቡ “ነጻነቱን በግልጽ የመጋፋት ሙከራ” መሆኑን በመግለጽ “በጽኑ እንደሚቃወም” ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ዕቀባው ውሳኔ መሠረት ዳኞቹ በአሜሪካ ያሏቸው ንብረቶች እና ጥቅሞች በሙሉ ታግደው ለአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዲገለጽ ያዛል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሩቢዮን እና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በፍርድ ቤቱ ላይ ማዕቀቡን በመጣላቸው አመስግነው “ለእስራኤል መብት ቆማችኋል” ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
ሩቢዮ በመግለጫቸው ዳኞቹን በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ ያነጣጠረ “ሕገ ወጥ እና መሠረተ ቢስ ድርጊቶች” ላይ አተኩረዋል ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
“እነዚህ አራት ግለሰቦች በአይሲሲ ሕገ ወጥ እና መሠረተ ቢስ ድርጊቶች አሜሪካን ወይም የቅርብ አጋራችን በሆነችው እስራኤል ላይ ያነጣጠሩ ናቸው” ብለዋል።
ሩቢዮ አይሲሲን “ፖለቲካዊ” ሲሉ የገለፁት ሲሆን፣ የአሜሪካ እና የአጋሮቿን ዜጎች ለመመርመር “በሐሰት ውንጀላ ያልተገደበ ፍርድ” ይጠቀማል ብለዋል።
“ይህ አደገኛ እርምጃ እና ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም የዩናይትድ ስቴትስ እና የአጋሮቻችንን፣ እስራኤልን ጨምሮ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ደኅንነትን ይጥሳል።”
አይሲሲ በሰጠው ምላሽ “ሙሉ በሙሉ ከሠራተኞቻቸውን ጎን እንቆማለን” እናም ሥራችን “ሳይስተጓጎል” ይቀጥላል ሲል ገልጿል።
“ተጠያቂነት እንዲኖር በሚሠሩ ላይ ማነጣጠር በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎችን ለመርዳት ምንም አይፈይድም” ሲል ፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
“እነዚህ ማዕቀቦች የተጣሉት በተመረጡ ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤቱን በሚደግፉ ሁሉ ላይም ያነጣጠሩ ናቸው. . . እንዲሁም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤቱ በሚቀርቡ ሁሉም ንፁሃን ተጎጂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው።”
አይሲሲ በዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች እና በጦር ወንጀሎች ላይ ክስ የማቅረብ ሥልጣን ያለው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ነው።
ባለፈው ዓመት በጋዛ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ኔታኒያሁ እና የእስራኤል የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
የሐማስ ወታደራዊ አዛዥ መሐመድ ዴይፍ ላይም የእስር ማዘዣ አወጥቶ የነበረ ቢሆንም እስራኤል ባለፈው ዓመት ባደረገችው የአየር ድብደባ መገደሉ ተረጋግጧል።
ዳኞቹ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረገው ጦርነት ሦስቱ ሰዎች በጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ጥሰቶች “የወንጀል ተጠያቂነት” ያለባቸው “ተጨባጭ ምክንያቶች” እንዳሉ ተናግረዋል።
እስራኤልም ሆነች ሐማስ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።
በየካቲት ወር ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአይሲሲ ዋና ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካን ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥለው ፍርድ ቤቱ “ሥልጣኑን አላግባብ ተጠቅሟል” ብለዋል።
በሐሙሱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሁለቱ ዳኞች ቦሳ እና ኢባኔዝ ካርራንዛ አይሲሲ በአፍጋኒስታን በሚገኙ የአሜሪካ ሠራተኞች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ ፈቃድ ሰጥተዋል ብሏል።
ሌሎቹ ሁለቱ ዳኞች አላፒኒ ጋንሱ እና ሆህለር ለኔታንያሁ እና ጋላንት የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።